October 17, 2024

የካናዳ መንግስት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የስራ እድል አመቻቸ በማለት ከሚፈጸም የማጭበርበር ድርጊት እንጠንቀቅ

የውጭ ሀገር የስራ እድሎችን እናመቻቻለን በሚል የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ ይገኛሉ።

እንደ ፌስቡክ እና ቴሌግራም ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች እና ፈጣን መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ደግሞ መሰል የማጭበርበር ድርጊት ለሚፈጽሙ አካላት አመቺ ሁኔታን ፈጥረዋል።

እነዚህ አካላት በግልጽ የስልክ ቁጥሮችን እና የባንክ ሂሳብ ቁጥሮችን በማጋራት የተሻለ ገቢ እና ህይወትን ተስፋ በማድረግ ወደነሱ የሚሄዱ ግለሰቦችን ያጭበረብራሉ።

ከሰሞኑም “የስራ ማስታወቂያ” የሚል ርዕስ ያለው እና የካናዳ መንግስት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የስራ እድል እንደሰጠ፤ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያንም ስልክ በመደወል እንዲመዘገቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት እየተጋራ ይገኛል።

ይህ ደብዳቤ የሁለቱ ሀገራት ባንዲራ፤ ‘CANADA EMBASSY’ የሚል አራት ማዕዘን “ማህተም” እንዲሁም የቃላት እና ይዘት ግድፈት ያለበትና ሀሰተኛ መሆኑ የሚያስታውቅ ክብ ማህተም አርፎበታል።

ኢትዮጵያ ቼክ መሰል የማጭበርበር ድርጊቶችን በተመለከተ በተለያዩ ወቅቶች መረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካላት በማጣራት ለተከታዮቹ ሲያቀርብ ቆይቷል።

በካናዳ መንግስት የተመቻቹ የስራ እድሎች እና ቪዛ ሎተሪ በሚል በግለሰቦች ስልክ ቁጥር እና የቴሌግራም አድራሻዎች አማካኝነት የሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶችም ከዚህ በፊት ከሰራንባቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

በወቅቱ ኢትዮጵያ ቼክ ከካናዳ ኤምባሲ መረጃን ጠይቆ በኢንተርኔት አማካኝነት የሚፈጸሙ በርካታ የማጭበርበር ድርጊቶች መኖራቸውን እና ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና መሰል መረጃዎችን በደንብ መመርመር እንዳለባቸው ኤምባሲው ገልጾ ነበር።

በተጨማሪም ኤምባሲው ሰዎች የሀገሪቱን ኢሚገሬሽን ፕሮግራሞች በተመለከተ ሁልጊዜ ትክክለኛ የሀገሪቱን ድረ-ገጾች እና ማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንዲመለከቱ መክሯል።

በዚሁ መሰረት “የካናዳ መንግስት ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የስራ እድል ሰጠ” በሚል እየተጋራ የሚገኘው ደበዳቤ ላይ ባደረግነው ማጣራት ደብዳቤው በራካታ የጽሁፍ ግድፈቶች ያለበት፤ ግልጽ ያልሆነ እና አጠራጣሪ “ማህተሞች” ያረፉበት መሆኑን ተመልክተናል።

በተጨማሪም የካናዳ ኢሚግሬሽን፤ ስደተኞች እና ዜግነት ተቋም ድረ-ገጽን የተመለከትን ሲሆን “ለ10 ሺህ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን የስራ እድል መሰጠቱን” የሚገልጽ ምንም አይነት መረጃ አለመኖሩን አረጋግጠናል፡ https://www.canada.ca/en/immigration-refugees-citizenship/news.html

የተቋሙን ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ የኤክስ (ትዊተር) አካውንትም የሀገሪቱን ኢሚግሬሽን ጉዳዮች የሚመለከቱ መረጃዎችን በየጊዜው የሚያጋራ ቢሆንም ስለ “10 ሺህ የስራ እድሉ” ምንም አይነት መረጃ አለማጋራቱን አረጋግጠናል፡ https://twitter.com/CitImmCanada?s=20&t=9JlcTQWzQhB6JyFrFKtJrQ

ስለዚህ አጓጚ የስራ እድሎችን እንደ ማታለያ በማቅረብ ለሚፈጸሙ የማጭበርበር ድርጊቶች እንዳንጋለጥ ህጋዊ መንገዶችን እንምረጥ፣ እንዲሁም ትክክለኛነታቸው የተረጋገጠ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንደ መረጃ ምንጭ እንጠቀም።

ኢትዮጵያ ቼክ