
ከ 4 ሰአት በፊት
የአውስትራሊያዋ ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ዕድሜያቸው 10 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሕፃናት ወንጀል ከፈፀሙ ሊታሰሩ ይችላሉ የሚል ሕግ አወጣ።
የአውስትራሊያ ግዛቶች ሕፃናት ማረሚያ ቤት የሚገቡበት ዕድሜ ከ10 ወደ 14 ከፍ እንዲያደርጉ ከተባበሩት መንግሥታት ጭምር ጫና እየተደረገባቸው ቆይቷል።
ባለፈው ዓመት የኤንቲ ግዛት ዕድሜውን ወደ 12 ከፍ አድርጎት ነበር። ነገር ግን ነሐሤ ላይ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ አስተዳደር ወጣቶች ከወንጀል እንዲቆጠቡ በማለት የዕድሜ ጣራውን ወደ 10 ዝቅ አድርጎታል።
አዲሱ ሕግ ሕፃናትን ለመጠበቅ የወጣ ነው ሲሉ ባለሥልጣናት ተከራክረዋል። ዶክተሮች፣ የመብት ተሟጋቾች እና የአውስትራሊያ የቀደምት ማኅበረሰብ አባላት ሕጉን ተቃውመውታል።
ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ሕጉ አቦሪጂናል እና ቶሬስ ሰትሬይት አይላንደር የተባሉት ቀደምት ማኅበረሰብ ሕፃናትን የበለጠ የሚጎዳ ነው።
ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ከሌሎች የአውስትራሊያ ግዛቶች ሲነፃፀር 11 እጥፍ ሕፃናት የሚታሰሩበት ግዛት ሲሆን አብዛኛዎቹ አቦሪጂናል ናቸው።
የአውስትራሊያ ግዛቶች በወጣቶች በሚፈፀሙ ወንጀሎች እየታመሱ ሲሆን በኤንቲ ግዛት አሊስ ስፕሪንግስ በተሰኘችው ከተማ ለወጣቶች ብቻ ሰዓት እላፊ ታውጇል።
- የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደሉን እስራኤል አረጋግጫለሁ አለች17 ጥቅምት 2024
- የኬንያው ምክትል ፕሬዝደንት ሆስፒታል ተኝተው ሳለ ከሥራቸው ተሰናበቱከ 4 ሰአት በፊት
- የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል? ከመከሰቱ በፊትስ መገመት ይቻላል?ከ 5 ሰአት በፊት
የግዛቱ ዋና ሚኒስትር ሊያ ፊኖቺያሮ “ሕፃናትን የመጠበቅ እና የማኅበረሰቡን ደኅንነት የማስከበር ግዴታ ስላለብን ነው” ሕጉን ያወጣነው ብለዋል።
አብዛኛዎቹ ሕፃናትና ታዳጊዎች ሰብሮ በመግባት እና ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ነው ወንጀል የሚፈፅሙት።
ኖርዘርን ቴሪተሪ ግዛት ሕፃናት ጥፋት አጥፍተው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በዋስትና የሚወጡበትን ሕግም ጠበቅ አድርጓል።
ነገር ግን አውስትራሊያ ውስጥም በመላው ዓለም የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሕፃናትን ማሰር የበለጠ ወንጀሎች እንዲሠሩ ከማበረታቱም በላይ ጤናቸው፣ ትምህርት እና ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል።
በመንግሥት የሚተዳደረው ገለልተኛው የአውስትራሊያው ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ዘገባ አዳዲሶቹ ፖሊሲዎች “ሕዝባዊ” በሆኑ እና “ጠንካራ ሕግ” በማውጣት በሚያምኑ አስተዳደሮች ነው ተግባራዊ የሚደረጉት ብሏል።
ኮሚሽኑ መንግሥት ሕፃናትን እስር ቤት ለማስገባት የሚያወጣውን ወጪ የድጋፍ አገልግሎት ላይ ቢያውለው መልካም ነው ብሏል።
በአውስትራሊያ የመጀመሪያዋ እና ብቸኛዋ ሴት አቦሪጂናል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሴሌና ኡይቦ ሕጉ መፅደቁን ተከትሎ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
“ሕፃናት መልካም ያልሆነ ባሕሪ ሲያሳዩ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ነገር ግን ወደ ትክክለኛው መንገድ ማምጣት እንጂ ማሰር የለብንም” ብለዋል።
የኤንቲ ፓርላማ በያዝነው ሳምንት አዲሱን ሕግ በተመለከተ ክርክር በሚያካሂድበት ወቅት 100 ገደማ ሰዎች ከፓርላማው ቅጥር ግቢ ውጭ የተቃውሞ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ነበር።
የኤንቲ ሕፃናት ኮሚሽን ኃላፊ ሻህሊና መስክ የአቦሪጂናል ሕፃናት ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው ወዲያውኑ ወደ ፍርድ ቤት ተውስደው ይበይንባቸዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።