ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ አልፓቺኖ በ83 ዓመቱ አራተኛ ልጁን ከ29 ዓመቷ እጮኛው ኑር አልፋላህ የወለደው ባለፈው ዓመት ነበር።
የምስሉ መግለጫ,ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ አልፓቺኖ እና የ29 ዓመቷ እጮኛው ኑር አልፋላህ

ከ 5 ሰአት በፊት

ወልዶ መሳም የወጣቶች አልያም የጎልማሶች ብቻ አይደለም።

ምርኩዝ ይዘው ዓይናቸውን በዓይናቸው ያዩ እዚህም እዚያም ይጠቀሳሉ።

ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ አልፓቺኖ በ83 ዓመቱ አራተኛ ልጁን ከ29 ዓመቷ እጮኛው ኑር አልፋላህ የወለደው ባለፈው ዓመት ነበር።

በእርግጥ በስተርጅና የልጅ አባት በመሆን ብቸኛው ሰው አይደለም።

በቅርቡ ጓደኛው እና የሙያ አጋሩ ሮበርት ዴ ኒሮ በ79 ዓመቱ ሰባተኛ ልጁን ማግኘቱን አስታውቋል።

ዕድሜ ከገፋ በኋላ መውለድ በታዋቂ የሆሊውድ ተዋንያን፣ ሙዚቀኞች እንዲሁም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ዘንድ የተለመደ ነው።

በየዓመቱ በዕድሜያቸው አመሻሽ ላይ ሳሉ የልጅ አባት የሆኑ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

በአሜሪካ በ2015 በተደረገ አንድ ጥናት እኤአ ከ1972 እስከ 2015 ባሉት ጊዜያት ብቻ ወልደው የሳሙ አዛውንቶች ቁጥር በ3.5 ዓመት ጨምሯል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በርካታ ወንዶች 31 ዓመት ሆኗቸው የወለዱ ሲሆን፣ 9 በመቶዎቹ ደግሞ 40 ዓመት ሆኗቸው ነው ዓይናቸውን በዓይናቸው ያዩት።

በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ (ጊነስ ቡክ ኦፍ ዎርልድ ሪከርድስ) ላይ ደግሞ የ92 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ በዕድሜ የገፉ አባት ሆነው ተመዝግበዋል።

በእርግጥ መረጃዎች በአግባቡ ተሰንደው ባለመገኘታቸው እንጂ ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላ ወልደው የሳሙ በየአህጉሩ ይገኛሉ።

ለመሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ዘግይተው ልጅ ሲወልዱ ያለው አደጋ ምንድን ነው?

በአውሮፓውያኑ 2022 ታኅሣሥ ወር የዩታህ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ከሌሎች አጥኚዎች ጋር በመሆን በጋራ ያሳተሙት ጥናት “በዕድሜ ከገፉ በኋላ የልጅ አባት መሆን” ከወሊድ ጋር ያለውን ተጽዕኖ፣ በእርግዝና ላይ የሚያስከትለውን ችግር እንዲሁም በሕጻናቱ ጤና ላይ ያለውን አደጋ ዘርዝሯል።

በዚህ ዙርያ የተደረጉት ጥናቶች በአልፓቺኖ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወንዶችን ባያካትቱም፣ ዕድሜያቸው በአርባዎቹ እና በሃምሳዎቹ ውስጥ የሚገኙ ወንዶች የዘር ፈሳሽ ጥራት፣ ብዛት፣ ቁጥር፣ የመዋኘት አቅምም ሆነ የዘረ መል ለውጥ ዝቅተኛ ነው።

እነዚህ ለውጦች ታድያ ዕድሜ ከገፋ በኋላ አባት መሆን “መውለድ ካለመቻል ጋር ብቻ ሳይሆን ጽንሱ በተፈጥሯዊ መንገድ ከተጸነሰ በኋላ የመሞት ዕድሉ እጅጉን ከፍተኛ ነው” ሲሉ ተመራማሪዎቹ አስፍረዋል።

በርካታ ጥናቶች እንደለዩት ከሆነ በዕድሜ ከገፉ አባቶች የሚጸነሱ ሴቶች ለጽንስ መቋረጥ ወይንም ለጭንገፋ የተጋለጡ ናቸው።

ይህ ብቻም ሳይሆን ጨቅላዎቹ ከተወለዱ በኋላም የመሞታቸው ዕድል ሰፊ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 1950ዎቹ ጀምሮ ዕድሜያቸው ከገፋ አባቶች የሚወለዱ ሕጻናት አኮንድሮፕላሲያ (achondroplasia) ለተሰኘ የዘረ መል ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ነገር ግን ይህ የዘረ መል ችግር ከዚያ ጊዜ ወዲህ ከሌሎች የጤና ችግሮች ጋር ያለው ግንኙነት በስፋት እየታወቀ መጥቷል።

“በየጊዜው ግልጽ እየሆነ የመጣው እድሜ ከገፋ በኋላ የሚወልዱ አባቶች፣ ልክ በዕድሜ ከገፉ በኋላ እንደሚወልዱ እናቶች ሁሉ ከጨቅላዎቹ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች ያጋጥማቸዋል” ይላሉ የዩታህ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች።

አልፓቺኖ እና ሮበርት ዲ ኒሮ

ዝቅተኛ ኪሎ ይዘው የሚወለዱ ሕጻናት

ለምሳሌ የስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ዕድሜያቸው ከገፉ አባቶች የሚወለዱ ሕጻናት ዝቅተኛ ክብደት ኖሯቸው እንደሚወለዱ እንዲሁም በጨቅላ ሕጻናት መንቀጥቀጥ ይጠቃሉ።

ከአዛውንት አባቶች የሚወለዱ ሕጻናት ለተለያዩ የሕጻናት ካንሰሮች እንዲሁም ለልብ ህመም የተጋለጡ ናቸው።

የዕድሜ መግፋት እና የሚያጋጥሙ የጤና ቀውሶችን ምክንያቶች ጥናቶቹ እንደሚያገናኙት ሁሉ መነሻው ግን ግልጽ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

የወላጆቹ የሕይወት ዘዬ እንዲሁም የአየር ብክለትን የመሳሰሉ ሌላ ውስብሰብ የሆኑ ምክንያቶች ድርሻ ሊኖራቸው ይችላል።

ይህም ሆኖ ተመራማሪዎች ዕድሜ በገፋ ቁጥር በወንዶች ዘር ውስጥ ወደ ቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉ ዘረ መሎችን በተመለከተ፣ በህዋስ ውስጥ የዲኤንኤ መጎዳት እንዲሁም ዲኤንኤ ላይ የሚኖረው ለውጥ ሊጎዳ እንደሚችል አስተውለዋል።

ይህንን መሰል ጥናቶች መኖራቸው የሕክምና ባለሙያዎችም ሆኑ ተመራማሪዎች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ሊያስተውሏቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከዚህ ቀደም ጥንዶች መውለድ ሳይችሉ ሲቀሩ ሴቲቱ እና ዕድሜዋ ላይ ብቻ ማተኮር የተለመደ ነበር።

ለዚያም ነው በርካታ ከወሊድ ጋር የተያያዙ ጥናቶች ሴቶች ላይ ብቻ ያተኮሩት።

ነገር ግን በጊዜ ብዛት የወንዶች የመውለድ ሁኔታ ቀስ በቀስ እየቀነሰ ሲመጣ የወንዶች ዕድሜ ሊታይ የሚገባ ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።

ለአሁኑ የአል ፓቺኖ እና ዲ ኒሮ እንዲሁም ዕድሜያቸው በ70ዎቹ፣ 80ዎቹ እና 90ዎቹ የሚገኙ አባቶች ጉዳይ በጣም አነስተኛ ሆኖ ሊታይ ይችላል።

ነገር ግን በአጠቃላይ አባትነት የወጣቶች ወይንም የጎልማሶች ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።

ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ጀምሮ ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች ሆነው አባት የሆኑ አሜሪካውያን ቁጥር በ27 በመቶ ቀንሷል።

በተቃራኒው ዕድሜያቸው ከ45 እስከ 49 ያሉት አባቶች ደግሞ በ52 በመቶ ጨምሯል።

ይህ ጉዳይ በዚሁ ከቀጠለ መድኃኒቶች ይመረታሉ፤ እንዲሁም የማኅበረሰቡ አመለካከት ያለጥርጥር ይቀየራል።