
ከ 5 ሰአት በፊት
አፋር ክልል ውስጥ የሚገኘው አዋሽ ፈንታሌ ከሰሞኑ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እያስተናገደ ነው። በሥፍራው የሚሰከተው ርዕደ መሬት ንዝረት ሩቅ ቦታዎች ላይ በተለይ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እየተሰማ ይገኛል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (የዩኤስጂኤስ) ረቡዕ ጥቅምት 6/2017 ዓ.ም. ምሽት 5፡11 ገደማ አዋሽ ፈንታሌ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደተከሰተ ዘግቧል።
ርዕደ መሬትን የተመለከቱ አሁናዊ መረጃዎች የሚያወጣው ኦፊሴላዊ የአሜሪካ መንግሥት ድረ-ገፅ እንደዘገበው የመሬት ነውጡ በሬክተር ስኬል 4.6 ማግኒቲዩድ ነበረው።
ባለፈው እሑድ ጥቅምት 3/2017 ዓ.ም. ንጋት በዚሁ አካባቢ በተመሳሳይ መካከለኛ ጥንካሬ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱ ይታወሳል። የዩኤስጂኤስ መረጃ እንደሚጠቁመው ርዕደ መሬቱ 4.6 ማግኒቲዩድ ነበረ።
ከዚህ ክስተት አንድ ሳምንት አስቀድሞ መስከረም 27/2017 ዓ.ም. በተመሳሳይ በአዋሽ ፈንታሌ 4.9 ማግኒቲዩድ ጥንካሬ ያለው ርዕደ መሬት ተከስቷል።
የአሜሪካው በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሴስሞሎጂ [ርዕደ መሬት] ድረ-ገፅ በአውሮፓውያኑ መስከረም 30 በተመሳሳይ አካባቢ 4.5 ሬክተር ስኬል የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ መመዝገቡን አስፍሯል።
ለመሆኑ ርዕደ መሬት እንዴት ይከሰታል? ከመከሰቱ በፊትስ መገመት ይቻላል?

የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ይከሰታል?
መሬት የተዋቀረችው በሦስት ንብርብሮች ነው። የመሬት ማዕከላዊው ክፍል ‘ኮር’ ይባላል። ቀጥሎ የሚገኘው ‘ማንትል’ ነው። በመቀጠል ‘ክረስት’ ይመጣል። ይህ በዓይናችን የምናየው የመሬት ክፍል ነው።
ክረስት እና የማንትል የላይኛው አካል ቴክቶኒክ ፕሌትስ ከተባለው ድንጋይ የተሠሩ ናቸው።
‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ ዝግ ባለ መልኩ ሁሌም ይጓዛሉ። በዚህ መካከል ግጭት እና መተፋፈግ ይፈጠራል። ይህ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ ሆኖ በመሬት ገጽ ላይ ያሉ አካላትን የሚነቀንቀው እና የሚያፈራርሰው።
በቀላል አገላለጽ በዓይናችን ከምናየው መሬት በታች ያሉት ንብርብር አለቶች በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ እርስ በርስ ሲተፋፈጉ አሊያም ሲፋጩ መሬት ትንቀጠቀጣለች ማለት ነው።
‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ በየዓመቱ በጥቂት ሴንቲ ሜትሮች እንቀስቃሴ ያደርጋሉ። እነዚህ መሬት የተዋቀረችባቸው አለቶች በተለያየ አቅጣጫ ነው የሚንቀሳቀሱት። ፍጥነታቸውም የተለያየ ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ አለቶች እርስ በርስ ተፋፍገው ሊያልፉ ይችላሉ። ሌላ ጊዜ ደግሞ አንዱ ክፍል ከሌላኛው እየራቀ ሊሄድ ይችላል። እርስ በርስም የሚጋጩ አሉ።
በተለያየ አቅጣጫ የሚጓዙ ድንጋዮች ሲተፋፈጉ ርዕደ መሬት ያስከትላሉ። በመተፋፈጉ መካከል የሚከሰተው ኃይል ከፍተኛ ስለሆነ የመሬት ማዕበል ይፈጥራል።
የመሬት መንቀጥቀጥ የባሕር ጠለል ላይ ሲከሰት ደግሞ ከፍተኛ ማዕበል ይፈጠራል። ሱናሚ የሚባለውም ይህ ነው።
በዓለማችን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የመሬት ነውጦች ይመዘገባሉ። አብዛኛዎቹ ዝቅተኛ የሚባሉ እና በተለየ ቴክኖሎጂ የሚለዩ ናቸው። በጣም ከፍተኛ የሚባሉት ደግሞ ከተሞችን የማፈራረስ አቅም አላቸው።
ይህ የመሬት ውስጥ ንቅናቄ እና መንቀጥቀጥ ጥንካሬ የሚለካበት መሳሪያ ሬክተር ስኬል ይባላል። ይህ መለኪያ ርዕደ መሬቱ የፈጠረውን ማግኒቲዩድ ይመዝናል።
በዓለማችን ብዙ ጊዜ ተደጋጋሚ ርዕደ መሬቶች የሚከሰቱበት ሥፍራ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ነው። በዚህም ምክንያት በፓሲፊክ ውቅያኖስ አቅራቢያ የሚገኙ እንደ ጃፓን ያሉ አገራት ርዕደ መሬትን ተላምደውታል።
ጃፓን ውስጥ ሕንፃዎች ርዕደ መሬትን እንዲቋቋሙ ተደርገው ነው የሚገነቡት። ይህ ማለት በአገሪቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲከሰት አብዛኞቹ መዋቅሮች ይናጣሉ እንጂ የመፍረስ እድላቸው ጠባብ ነው ማለት ነው።
- እስራኤል ሳይገደል አይቀርም ያለችው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?17 ጥቅምት 2024
- ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ነፃነት ዝቅተኛ ነጥብ ማስመዝገቧ እና የመንግሥታት ቁጥጥር የደቀነው ስጋት17 ጥቅምት 2024
- በአማራ ክልል ያሉ የሱዳን ስደተኞች ለግድያዎች፣ ለእገታዎች እና ለግዳጅ የጉልበት ሥራዎች ተጋልጠዋል፡ ሂውማን ራይትስ ዋች17 ጥቅምት 2024

ርዕደ መሬት በታላቁ ስምጥ ሸለቆ
አዋሽ በታላቁ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ነው የሚገኘው። ይህ ስምጥ ሸለቆ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛምቢክ ድረስ የተዘረጋ ነው።
ይህ ስምጥ ሸለቆ በዓለማችን አህጉር የሚያቋርጥ ብቸኛው ሸለቆ ሲሆን፣ ሳይንቲስቶች እንዴት አህጉራት እንደሚመሠረቱ የሚያጠኑበት ነው።
እርግጥ ነው አፍሪካ ቀንድን ሰንጥቆ ወደ ደቡቡ የአህጉሪቱ ክፍል የሚያልፈው ስምጥ ሸለቆ ልክ እንደ ፓሲፊክ ውቅያኖስ ነውጠኛ ለሚባሉ ርዕደ መሬቶች የተጋለጠ አይደለም።
የናሳ መረጃ የሚያሳየው በምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ለመጨረሻ ጊዜ ከባድ የሚባል ርዕደ መሬት የተከሰተው በአውሮፓውያኑ 2005 ሲሆን የጥንካሬው መጠንም 6.8 ነበር። ይህ ታንጋኒካ ሐይቅ አካባቢ የተከሰተው ርዕደ መሬት ንዝረቱ 970 ኪሎ ሜትር ተጉዞ እስከ ኬንያ መዲና ናይሮቢ ተሰምቶ እንደነበር ይታወሳል።
ከ100 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባቀፈው ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ለዓመታት ይህ ነው የሚባል በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያስከተለ ርዕደ መሬት ባይኖርም አደጋው ግን የለም ማለት አይደለም ይላል የዓለም ባንክ ዘገባ።
ዓለም ባንክ በዘገባው የታላቁ ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ያሉ ሕንፃዎች ጥራታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ መካከለኛ የሚባሉት ከ5.0 እስከ 6.0 ያሉ ርዕደ መሬቶች ቢከሰቱ የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ ሲል ያስጠነቅቃል።
ባንክ ጨምሮም በዚህ የስምጥ ሸለቆ አካባቢ ባሉ ከተሞች ውስጥ በድህነት የሚኖሩ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ። ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2050 እጥፍ ሊሆን ይችላል።
በአውሮፓውያኑ 2016 በታንዛኒያ በተከሰተ 5.9 ሬክተር ስኬል ርዕደ መሬት ምክንያት 20 ሰዎች መሞታቸው እና 269 መቁሰላቸው አይዘነጋም።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ፣ በማላዊ፣ በሞዛምቢክ እና በኡጋንዳ የተለያዩ ርዕደ መሬቶች ተከስተዋል።
የአሜሪካው የጠፈር ምርመር ተቋም ናሳ እንደሚለው የታንጋኒካ ሐይቅ እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ‘ሥነ ምድራዊ ክስተቶች’ የሚቀጥሉ ከሆነ ወደፊት ምሥራቅ አፍሪካ ከተቀረው አፍሪካ ይገነጠላል፤ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ደግሞ ውቅያኖስ ይሆናል።
ከታላቁ ስምጥ ሸለቆ በተቃራኒ የአሜሪካዎቹ ካሊፎርኒያ እና አላስካ በጣም በርካታ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያስተናግዱ ሥፍራዎች ናቸው። እነዚህ የአሜሪካ ግዛቶች በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ርዕደ መሬቶች ያጋጥማቸዋል።

ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት መገመት ይቻላል?
ርዕደ መሬት ከመከሰቱ በፊት መገመት ከባድ ነው። ነገር ግን የመሬት ነውጥ በተከሰተበት አካባቢ ያለውን መረጃ በማየት አንዳንድ አመላካች ጥቆማዎች ሊገኙ ይችላሉ።
“ተፈጥሮ መገመት በሚከብዱ ክስተቶች የተሞላች ናት” የሚሉት በፔንሲልቬኒያ ፔን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ክሪስ ማሮን ናቸው።
የሥነ ምድር (ጂኦሎጂ) ባለሙያዎች ከ1960ዎቹ ጀምሮ ዘመናዊ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ርዕድ መሬት ከመከሰቱ በፊት ለመገመት ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
የዩኤስጂኤስ እንደሚለው ርዕደ መሬትን ለመገመት ሦስት ነገሮች መመሏት አለባቸው – የት ይከሰታል? መቼ ይከሰታል? እና ምን ያህል ማግኒቲዩድ (ጥንካሬ) ይኖረዋል? የሚሉት ናቸው። ነገር ግን እስከ ዛሬ ድረስ ማንም እነዚህን ሦስቱን ግምቶች ማሳካት የቻለ የለም።
የሥነ-ምድር ተመራማሪዎች በርካታ ጊዜ ርዕደ መሬት የሚያጠቃቸው ቦታዎች ሕንፃዎች ይህን የተፈጥሮ ክስተት የሚቋቋሙ ሆነው እንዲገነቡ ቢመክሩም ከመከሰቱ በፊት ትንበያ አስቀምጦ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ቴክኖሎጂን እስካሁን መፍጠር አልቻሉም።
በምዕራቡ ዓለም ሕንፃዎች የመሬት መንቀጥቀጥን እንዲቋቋሙ ሆነው እንዲገነቡ የሚያስገድድ ሕግ የወጣው በተለይ በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ እና 70ዎቹ ነው።
ሳይንቲስቶች ርዕደ መሬትን ለመተንበይ የመሬት መናጥን ከማጥናት ባለፈ የእንስሳትን ባሕርይ ሲከታተሉ ተስተውለዋል።
እንስሳት የመሬት መንቀጥቀጥ ከመከሰቱ በፊት ይደነበራሉ፣ ይፈረጥጣሉ የሚለው ሐሳብ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ይህንን ዘዴ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው።
አሁን አሁን ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ዕድገት ጋር በተያያዘ ርዕደ መሬትን መተንበይ ይቻላል የሚሉ ግምቶች አሉ።
ለምሳሌ አንድ የእስራኤል የአጥኚዎች ቡድን ‘ማሺን ለርኒንግ’ በመጠቀም ርዕደ መሬት ከመከሰቱ ከ48 ሰዓታት በፊት መገመት ይቻላል የሚል ሐሳብ አንስቷል። በተመሳሳይ የቻይና ሳይንቲስቶችም ቴክኖሎጂን በመጠቀም በዘርፉ ቀድመው ለመገኘት ጥረት እያደረጉ ነው።

ስለርዕደ መሬት አንዳንድ አስደናቂ እውነታዎች
በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ርዕደ መሬቶች በዓለም ዙሪያ ይከሰታሉ – ዩኤስጂኤስ እንደሚለው አብዛኞቹ መጠናቸው አናሳ ነው፣ አሊያም እጅግ በራቀ ቦታ ስለሚከሰቱ ሳይመዘገቡ ያልፋሉ።
ርዕደ መሬት የቀን ርዝመትን ሊያዛባ ይችላል – ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2011 ጃፓንን በመታት 8.9 ሬክተር ስኬል ርዕደ መሬት ምክንያት ምድራችን ከሌላው ጊዜ በ1.8 ማይክሮ ሰከንድ ፈጥና ነው የሾረችው። ይህ ደግሞ ቶሎ እንዲነጋ አድርጓል።
ሳን ፍራንሲስኮ ወደ ሎስ አንጀለስ እየተጠጋች ነው – በርዕደ መሬት ምክንያት የአሜሪካዋ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በየዓመቱ 2 ኢንች ወደ ሎስ አንጀለስ እየተጠጋች ትገኛለች።
ከርዕደ መሬት በፊት ውሃ ልዩ ጠረን ሊያመጣ ይችላል – ኩሬዎች፣ ሐይቆች እና ሌሎች የማይፈሱ ውሃዎች ከርዕደ መሬት አስቀድመው ከባድ ሽታ ሊያመጡ እና ሞቅ ሊሉ ይችላሉ።
ፓሲፊክ ውቅያኖስ የርዕደ መሬት ማዕከል ነው – ፓሲፊክ ውቅያኖስ ከዓለማችን ርዕደ መሬቶች 90 በመቶ የሚሆኑት የሚነሱበት ስፍራ ነው።
የቺሊዋ ከተማ በርዕደ መሬት ምክንያት 10 ጫማ ፈቀቅ ብላለች – በአውሮፓውያኑ 2010 ኮንሴፕሲዮን በተሰኘችው ከተማ በተከሰተ 8.8 ማግኒቲዩድ ርዕደ መሬት ምክንያት ከተማዋ 10 ጫማ ወደ ምዕራብ ፈቀቅ ብላለች።
እንስሳት ከርዕደ መሬት በፊት የባሕሪ ለውጥ ያሳያሉ – በተለይ በኢንዶኔዢያው ሱናሚ ወቅት በርካታ እንስሳት እና አእዋፋት ወደ ከፍታ ሥፍራ ሸሽተዋል። ሳይንቲስቶች እንደሚያምኑት እንስሳት ከሰዎች በተሻለ የመሬት ንዝረትን ቀድመው የማወቅ አቅም አላቸው።