ያህያ ሲንዋር

ከ 1 ሰአት በፊት

እስራኤል ባለፈው ዓመት መስከረም መጨረሻ ላይ በተፈጸመው ጥቃትን በዋነኝት አቀነባብሯል ያለችውን የሐማሱ መሪ ያህያ ሲንዋርንን ለአንድ ዓመት ያህል ስታድነው ነበር።

የ61 ዓመቱ ያህያ ሲንዋር በጋዛ ሰርጥ ባሉ የሐማስ ዋሻዎች ተደብቋል እንዲሁም እስራኤላውያን ታጋቾችን እንደ ሽፋን እየተጠቀመ ይዘዋወራል ሲባል ነበር።

ሆኖም ያህያ የተገደለው ከእስራኤል ወታደሮች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ነው። ስፍራውም ዋሻ ውስጥ ሳይሆን በአንድ ህንጻ ላይ ነው።

ያህያ በተገደለበት ደቡባዊ ጋዛ ህንጻ ውስጥ ታጋቾች አልነበሩም። አብረውት የነበሩት ጠባቂዎች ወይም ታጣቂዎች ጥቂት ነበሩ እንዲሁም የለበሰውም ወታደራዊ ልብስ ነበር።

ግድያውን በተመለከተ ዝርዝሮች እየወጡ ቢሆንም እስካሁን ስለ ሲንዋር ግድያዎች የምናውቀውን እነሆ!

መደበኛ ጥበቃ

ጋዛን የወረረው የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ክፍል የሆነው 828ኛው ቢስላሜች ብርጌድ ረቡዕ ጥቅምት 6/ 2017 ዓ.ም. በራፋህ ከተማ የሚገኘውን ታል አል ሱልጣን ሰፈር አካባቢ መደበኛ ጥበቃ እያደረገ ነበር።

የእስራኤል ወታደሮች ሦስት ታጣቂዎችን ለይተው ገደሏቸው።

በታጣቂዎቹ እና በወታደሮቹ መካከል የተኩስ ልውውጥ የነበረ ሲሆን፣ ለየት ያለ ነገር ግን አልነበረም።

ወታደሮቹ ወደ ስፍራው ተመልሰው የመጡት በማግስቱ ሐሙስ፣ ጥቅምት 7/ 2017 ዓ.ም. ነበር።

የተገደሉትን ታጣቂዎች ሲመለከቱም የአንዱ አስክሬን ከሐማስ የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪ ያህያ ሲንዋር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ ተገኘ።

ሆኖም አስክሬኑ ላይ የተጠመደ ፈንጅ ሊኖር ይችላል በሚል እንዳይነሳ የተደረገ ሲሆን፣ የጣቱ ክፍል ተቆርጦ ለዘረ መል ምርመራ ተላከ።

በኋላ ላይም ስፍራው ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ እስራኤል አስክሬኑን አንስታ ወሰደች።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይ ዳንኤል ሃጋሪ ወታደሮቹ በስፍራው ሲንዋር እንዳለ ባያውቁም “እኛ ግን ሥራችንን እየሠራን ነበር” ብለዋል።

ሦስት ታጣቂዎች ከቤት ወደ ቤት ሲሯሯጡ በእስራኤል ወታደሮች መታየታቸውን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ዳንኤል ሐጋሪ ተናግረዋል።

የተኩስ ልውውጥ መካሄዱን ተከትሎ ሦስቱ ታጣቂዎች ተለያይተው ሲንዋር ብቻውን ወደ ህንጻ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።

ሲንዋር በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እገዛ ከታየ በኋላ መገደሉን ገልጸዋል። ሲንዋር እንደ ሽፋን ይጠቀምባቸው ነበር እያለች እስራኤል የምትናገርላቸው ታጋቾች በስፍራው አልነበሩም።

“ሲንዋር ተሸንፎ በሽሽት እየተሳደደ ነው የሞተው። ራሱን ባስቀደመ መልኩ እንጂ እንደ ጦር አዛዥ ሆኖ አልሞተም። ይህ ለጠላቶቻችን ግልጽ መልዕክት ነው” ሲሉ የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ተናግረዋል።

ሐሙስ አመሻሽ ላይ በእስራኤል ጦር የተለቀቀው በድሮን የተቀረጸ ቪዲዮ ሲንዋር ከመገደሉ በፊት ያሳለፈውን የመጨረሻ ጊዜ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ቪዲዮው በአብዛኛው በፈራረሰ ህንጻ ክፍት መስኮት አካባቢ እያንዣበበ ከነበረ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተቀረጸ ይመስላል።

በፍርስራሾች በተሞላው ህንጻ አንደኛ ፎቅ ላይ ባለ ወንበር ራሱን ተከናንቦ ወደተቀመጠ ግለሰብ ቀረብ ብሎ ያሳያል።

የተጎዳ የሚመስለው ይህ ግለሰብ ዱላ መሳይ ነገር ድሮኑ ላይ ሲወረውር ቪዲዮው ይጠናቀቃል።

በራፋህ ከተማ በእስራኤል ጥቃት የፈራረሰ ህንጻ
የምስሉ መግለጫ,በራፋህ ከተማ በእስራኤል ጥቃት የፈራረሰ ህንጻ

ሲንዋር ‘ተወግዷል’

ሲንዋር በጋዛ ተገድሎ እንደሆነ ለማረጋገጥ ምርመራ መጀመሯን እስራኤል ሐሙስ ከሰዓት በኋላ አስታውቃለች።

ይህን ባሳወቀች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሲንዋር ጋር ተመሳሳይ ገጽታ ያለው አስክሬን የሚያሳዩ ፎቶዎች መጋራት ጀመሩ። ግለሰቡ አስከፊ የጭንቅላት ጉዳት እንደደረሰብ የሚያሳይ ሲሆን፣ ፎቶዎቹም አሰቃቂ ይዘት አላቸው።

ሆኖም ባለሥልጣነቱ የተገደሉትን ሦስት ሰዎች ማንነት በዚህ ወቅት ማረጋጥ አይቻልም ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር።

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የእስራኤል ምንጮች ሲንዋር ሳይገደል እንዳልቀረ “የበለጠ እርግጠኛ” መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናረሩ። ሆኖም ፍጹም እርግጠኛ ለመሆን አስፈላጊ ምርመራዎች ሁሉ መደረግ እንዳለባቸው አክለዋል።

እነዚህ ምርመራዎች ረጅም ጊዜ ያልወሰዱ ሲሆን፣ ሐሙስ ምሽት ላይ እስራኤል ምርመራዋን ማጠናቀቋን እና ሲንዋርም “ተወግዷል” አለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ክፋት ድል ተነስቷል” ያሉ ሲሆን፣ በጋዛ ያለው ጦርነት ፍጻሜው ገና ነው ብለዋል።

ሲንዋር ኢላማ ተደርጎ በታቀደ ጥቃት ባይገደልም የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት ግን የሐማሱ መሪ በአካባቢው ስለመኖሩ የደኅንነት ጥቆማዎች አግኝቶ በስፍራው ሥራውን ሲያከናውን እንደነበር ገልጿል።

ሲንዋር ከአንድ ዓመት በላይ በሽሽት ላይ ነበር። እንደ መሐመድ ዴይፍ እና እስማኤል ሃኒያ ያሉ የሐማስ መሪዎች ሲገደሉ ሲንዋርም እንደማይቀርለት ጫናው ተሰምቶት እንደነበር ይገመታል።

የእስራኤል ጦር አዛዦች ሲንዋር በተገደለበት አካባቢ
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤል ጦር አዛዦች ሲንዋር በተገደለበት አካባቢ

መከላከያ ኃይሉ ባለፉት ሳምንታት በደቡባዊ ጋዛ ኣካሄዳቸው ዘመቻዎች እና ጥቃቶች “የያህያ ሲንዋርን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ ክትትሉን በማጠናከር በመጨረሻም እንዲወገድ አድርጓል” ብሏል።

እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ በምታደርገው የማያባራ እና የተቀናጀ ጥቃት ከ42 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መግደሏን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ ስር ካለው የጤና ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

ከመስከረሙ ጥቃት በኋላ ዋነኛ ኢላማ ሆኖ የቆየው ሲንዋር መገደሉ ለእስራኤል እንደ ትልቅ ድል ታይቷል። ሆኖም የእሱ መገደል የጋዛ ጦርነት ፍጻሜ እንዳልሆነ የእስራኤል ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኔታንያሁ “ብድር መልሰናል” ካሉ በኋላ በሐማስ ተይዘው ያሉ 101 ታጋቾችን ለመታደግ እና ከዚያም በኋላ ጦርነቱ ይቀጥላል ብለዋል።

“ለውድ የታጋቾች ቤተሰቦች፣ ይህ በጦርነቱ ወሳኝ ጊዜ ነው። የምትወዷቸው፣ እኛም የምንወዳቸው ቤተሰቦቻችሁ ቤት እስኪመለሱ ድረስ በሙሉ ኃይላችን እንቀጥላለን” ብለዋል።

በእስራኤል የታጋቾች ቤተሰቦች የተኩስ አቁም ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል እና ታጋቾች ሊመለሱ እንደሚችሉም ተስፋ አድርገዋል።

በእስራኤል ሠራዊት የተገደለው የ62 ዓመቱ ያህያ ሲንዋር በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ የስደተኞች ካምፕ ነው የተወለደው።

አብዛኛው ሕይወቱን በእስራኤል እስር ቤት ያሳለፈው ሲንዋር፣ በአውሮፓውያኑ 1988 ለሦስተኛ ጊዜ ሲታሰር አራት የዕድሜ ልክ አስራት ተፈርዶበት ነበር።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2011 በጋዛ በሐማስ ተይዞ በነበረው እስራኤላዊ ወታደር ጊላድ ሻሊት ልውውጥ ከ1 ሺህ26 ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን አረብ እስረኞች መካከል አንዱ የነበረው ሲንዋር ከእስር ተፈትቷል።

ያህያ ሲንዋር ከጥቂት ወራት በፊት ቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤት የተገደሉትን የሐማሱን መሪ ኢስማኤል ሃኒያን ተክቶ ነበር የሐማስን አጠቃላይ መሪነት ቦታውን የያዘው።