
ከ 4 ሰአት በፊት
እስራኤል ከአንድ ዓመት በላይ ስታድነው የነበረው የሐማስ የፖለቲካ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደልን ተከትሎ “መገደሉ ትልቅ ድል ቢሆንም የጦርነቱ መጨረሻ አይደለም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተናገሩ።
ከጥቂት ወራት በፊት ቴህራን በሚገኘው መኖሪያ ቤት የተገደሉት የሐማሱን መሪ ኢስማኤል ሃኒያን ተክቶ የመሪነት ቦታ የያዘው ሲንዋር በደቡባዊ ጋዛ መገደሉን እስራኤል አስታውቃለች።
ሐማስ ስለ መሪው ግድያ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወታደሮቻቸውን አወድሰው ለአገራቸው ትልቅ ድል መቀዳጀት ቢሆንም የጦርነቱ መጨረሻ እንዳልሆነ ግልጽ አድርገዋል።
“በሚጎዱን ላይ የሚከተለውን ዛሬ በድጋሚ ግልጽ አድርገናል። ዛሬ ክፋትን ጥሩነት እንደሚያሸንፍ ለዓለም አሳይተናል። ነገር ግን ጦርነቱ ገና አላላቀም፤ ከባድ ነው። ብዙ ዋጋ እያስከፈለንም ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዛ ታግተው ያሉ እስራኤላውያንን ወደየቤታቸው እንደሚመልሱ ለቤተሰቦቻቸው ቃል ገብተዋል።
ኔታንያሁ የሲንዋርን ግድያ የጦርነቱ ማብቂያ ባይሆንም “የፍጻሜው መጀመሪያ ነው” ብለውታል።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ በምታደርገው የማያባራ እና የተቀናጀ ጥቃት ከ42 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መግደሏን ከጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ከነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ ስር ካለው የጤና ሚኒስትሩ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ሲንዋር ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ የሐማስ ታጣቂ ክንፍን ይመራ የነበረ ሲሆን በእስራኤል የደረሰው የመስከረሙ ጥቃት ዋነኛ አቀናባሪ እና በበላይነት ያስፈጸመ ነው ሲሉ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና እስራኤል ይከሱታል።
በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ የእስራኤል ወታደሮች የተገደለው ሲንዋር በልዩ ሁኔታ በታቀደ ዘመቻ እንዳልተገደለ ተገልጿል።
- የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር መገደሉን እስራኤል አረጋግጫለሁ አለች17 ጥቅምት 2024
- እስራኤል ገድየዋለሁ ያለችው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነው?17 ጥቅምት 2024
- የእስራኤል ጥቃት ድምቀቷን ያደበዘዘባት ቤይሩት15 ጥቅምት 2024
ከስፍራው የተነሱ ምስሎች ሲንዋርን የሚመስል አስክሬን በታንክ በተመታ የህንጻ ፍርስራሽ ስር የትጥቅ ልብስ ለብሶ አሳይተዋል።
የግለሰቡ አስክሬን ጭንቅላት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋሩ አሰቃቂ ምስሎች ያሳያሉ።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት በወቅቱ ተገድሎ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ቢሰጥም ነገር ግን ከአንድ ዓመት በላይ ሲያድነው የነበረውን ግለሰብ ሞት ለማረጋገጥ ዲኤንኤ ምርመራ ማድረግ ነበረበት።
የእስራኤል ጦር ከዲኤንኤው ምርመራ በኋላ ረቡዕ ጥቅምት 6/ 2017 ዓ.ም በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተገደሉት ሶስት ታጣቂዎች መካከል አንዱ ሲንዋር ነው ብሏል።
ሶስት ታጣቂዎች ከቤት ወደ ቤት ሲሯሯጡ በእስራኤል ወታደሮች መታየታቸውን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃለ አቀባይ ዳንኤል ሐጋሪ ተናግረዋል።
ተኩስ መተኮሱን ተከትሎ ሶስቱ ታጣቂዎች ተለያይተው ሲንዋር ብቻውን ወደ ህንጻ ውስጥ ገብቷል ብለዋል።
ከዚያም በኋላ ሲንዋር ወንበር ላይ ተቀምጦ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) እገዛ መታየቱን አክለዋል። ወታደሮች ወደ ህንጻው ሲገቡ ሲንዋር የጥይት መከላከያ (ቬስት) ለብሶ፣ ሽጉጥ ይዞ እንዲሁም 40 ሺህ ሼክልስ ወይም 8 ሺህ 240 ፓውንድ ይዞ ነበር ብለዋል።
ሲንዋር መሆኑን ለማጣራት የዲኤንኤ (ዘረመል)፣ የጣት አሻራዎች እና የጥርስ ምርመራዎች በማስፈለጉ ዜናው ለበርካታ ሰዓታት ዘግይቶ ነበር።
እስራኤል ያህያ ሲንዋርን ከአውሮፓውያኑ 1988 እስከ 2011 አስራው በነበረበት ወቅት የወሰደቻቸው የዲኤንኤ ናሙናዎች አሏት።
ሲንዋር በተገደለበት ሕንፃ ውስጥ የእስራኤል ታጋቾች መገኘታቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳልታዩም ነው የተገለጸው።
ሲንዋር ለጥበቃ ሲባል ከእስራኤላውያን ታጋቾች ጋር እንደሚጓዝ ቀደም ብሎ ሲነገር ነበር።
የ62 ዓመቱ ሲንዋር በደቡባዊ ጋዛ በሚገኘው ኻን ዩኒስ የስደተኞች ካምፕ ነው የተወለደው።
አብዛኛው ህይወቱን በእስራኤል እስር ቤት ያሳለፈው ሲንዋር በአውሮፓውያኑ 1988 ለሶስተኛ ጊዜ ሲታሰር አራት የዕድሜ ልክ አስራት ተፈርዶበት ነበር።
ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2011 በጋዛ በሐማስ ተይዞ በነበረው እስራኤላዊ ወታደር ልውውጥ ከ1 ሺህ 26 ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን አረብ እስረኞች መካከል አንዱ የነበረው ሲንዋር ከእስር ተፈትቷል።