
ከ 1 ሰአት በፊት
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከመሾማቸው በፊት በፍትህ ሚኒስትርነት እያገለገሉ ነበር።
ላለፉት ስምንት ወራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው ጌዲዮን (ዶ/ር) ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱን አንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሾሙት።
ጌዲዮን (ዶ/ር) የገዢው የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ወደ መንግሥት ኃላፊነት ከመጡ ወጣት ተሿሚዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ዶ/ር ጌዲዮን የቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶሪያ ተደረገው ድርድር የመንግሥት አንኛው ተደራዳሪ ነበሩ።
- የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው ስለሚደራደሩት ግለሰቦች ምን እናውቃለን?28 ሰኔ 2022
- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን (ዶ/ር) ከሃርድቶክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምን አሉ?24 ነሐሴ 2021
- እስራኤል የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን እንዴት አግኝታ ገደለችው?ከ 1 ሰአት በፊት
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህርነት ሰፊ ልምድ ያላቸው ጌድዮን (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በሴንትራል ዩሮፒያን ዩኒቨርስቲ፣ በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ እና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተለያዩ የሕግ ዘርፎችን አስተምረዋል።
በሕግ ዘርፍ ከሚጠቀሱ ምሁራን መካከል የሆኑት ጌዲዮን (ዶ/ር) ለረጅም ጊዜ ባስተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት የረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከጌዲዮን (ዶ/ር) በተጨማሪ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳን የቱሪዝም ሚኒስትር አድረገው ሲሾሙ፣ ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴን ደግሞ በጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ምትክ የፍትህ ሚኒስቴር በመሆን ተሾመዋል።
ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት በፋና ብሮድካስቲንግ እና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነት ሲሠሩ ቆይተዋል።
ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሠሩ ነበር።