
18 ጥቅምት 2024, 15:42 EAT
የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር ከመስከረም ወር መጨረሻ ወዲህ ባሉት ሁለት ሳምንታት 11 ዳኞች ያለ አግባብ ታስረዋል ሲል ገለጸ።
ባለመረጋጋት ውስጥ በሚገኘው የአማራ ክልል ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የሚገኙ ዳኞች “ያለ አግባብ ሲታሰሩ እና ሲዋከቡ” እንደነበር ማኅበሩ ገልጿል።
ባለፈው ዓመት ከ35 በላይ ዳኞች ያለ አግባብ ታስረው እንደነበር የጠቀሰው ማኅበሩ፤ “በወንጀል ምርመራ በአግባቡ አጣርቶ መያዝ ሲገባ ዳኞች በሕዝብ ፊት ችሎት ላይ እየተያዙ ነው” ብሏል።
የማኅበሩ ተወካይ ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አሳሳ ከመስከረም 26/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የወረዳ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ 11 ዳኞች እንደታሰሩ እና ሁለት ዳኞች ደግሞ “ባልታወቁ ሠዎች” እንደተገደሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከታሰሩት ዳኞች ውስጥ ሁለት የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍ/ቤት ዳኞች፣ ሁለት የባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ፍ/ቤት ዳኞች፤ በሰሜን ሸዋ ዞን የቀወት ወረዳ ፍ/ቤት የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሁለት ዳኞች እና አንድ የሸዋ ሮቢት ወረዳ ፍ/ቤት ዳኛ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን አንድ የደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
አቶ ብርሃኑ የዳኞችን እስር “ምክንያቱን ማወቅ አልቻልንም” ያሉ ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር ሲውሉም በምን እንደጠረጠሩ ለዳኞች አልተነገራቸውም ብለዋል።
“የሆነ የፀጥታ አካል ይመጣል፤ ትፈለጋለህ ብሎ ይዟቸው ነው የሚሄደው” ሲሉ የእስሩ ሕጋዊነት ላይ ጥያቄ ሚያነሱት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ፤ እስካሁንም ፍ/ቤት አለመቅረባቸውን ተናግረዋል።
“[ዳኞች] የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ሕገ ወጥ ሊሆኑ ይችላል። በተለያየ መንገድ የሰው መብት ሊጎዱ ይችላሉ” ሲሉ ዳኞች በወንጀል ቢጠረጠሩ እንኳ በሕጋዊ መንገድ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል።
- በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ18 ጥቅምት 2024
- የአማራ ክልል ቀውስ፡ መደምደሚያው የኃይል የበላይነት ወይስ ድርድር?14 ጥቅምት 2024
- በአማራ ክልል ያሉ የሱዳን ስደተኞች ለግድያዎች፣ ለእገታዎች እና ለግዳጅ የጉልበት ሥራዎች ተጋልጠዋል፡ ሂውማን ራይትስ ዋች17 ጥቅምት 2024
“ዳኛ ካለበት የሥራ ኃላፊነት አንጻር፤ በተለይ ደግሞ ችሎት ላይ እየሠራ እያለ አንስቶ መውሰድ ደግሞ ሌላ እራሱን የቻለ አደገኛ አካሄድ” መሆኑን ጠቅሰው፤ በወንጀል ተጠርጥረውም ከሆነ ሕጋዊ አካሂዱን በተከተለ መንገድ መጠየቅ አለባቸው ብለዋል።
ዳኞች ከኃላፊነታቸው እና ከሚሠሩት ሥራ ባህሪ አንጻር “የተለየ” ከለላ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያነሱት አቶ ብርሃኑ፤ የአማራ ክልል ዳኞች ያለመከሰስ መብት የላቸውም ብለዋል።
እስራቱ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 78 እውቅና ለተሰጠው የዳኞች ነጻነትን “እንቅፋት” መሆኑን ያመለከተው የዳኞቹ ማኅበር፤ ሁኔታው የዳኞችንም ክብር የሚነካ እንደሆነ ገልጿል።
ይህ ሁኔታ “በክልሉ በአጠቃላይ ዳኞች ላይ ፍርሃት እንዲሰፍን ያደርጋል” ሲሉ የእስሩን ተጽዕኖ ያነሱት አቶ ብርሃኑ፤ “የዳኝነት ነጻነትን እና ተቋማዊ ነጻነትን ያጠፋል” ብለዋል።
“በነጻነት ቁጭ ብሎ ችሎት እያስቻለ ያለ ዳኛ ጓደኛው በፀጥታ አካላት ‘ና ትፈለጋለህ’ ተብሎ ታስሮ ሲሄድ ካየ ሌላው ዳኛ ለነገ ምን ዋስትና አለው?” በማለት “ድርጊቱ አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓቱን ያናጋዋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ የዳኞች እስር በክልሉ ካለው ሰሞነኛ የዘፈቀደ እና የጅምላ እስር ጋር አይገናኝም ብለዋል።
“ዳኞች የታሰሩት በፖለቲካ ነው ብለን አናስብም። ምክንያቱም ከመሠረቱ ዳኛ እንደሚታወቀው ገለልተኛ ሆኖ የሚሠራ ነው። ሙያውም ይታወቃል። አብዛኞቹ ዳኞች በዚህ ፖለቲካ ውስጥ ይኖራሉ ብለን የምንጠረጥራቸውም አይደሉም” በማለት እስሩ ዳኞችን “ለማሸማቀቅ” ታስቦ የተካሄደ እንደሚሆን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
አማራ ክልል ካለው ፀጥታ ሁኔታ ባሻገር ዳኞች በተለየ የጥቃት ዒላማ መደረጋቸውን ያነሱት ተወካይ ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ሁለት ዳኞች “ባልታወቁ ሰዎች” መገደላቸውን ተናግረዋል።
ማኅበሩ ባወጣው መግለቻ መንግሥት ዳኞችን ከማሰር ወጥቶ ለዳኞች ጥበቃ ሊያደርግላቸው እንደሚገባም ተናግሯል።
አክሎም በእስር ላይ የሚገኙት አስራ አንድ ዳኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እና በዳኞች ላይ የሚፈጸም ያልተገባ እስርንም መንግሥት እንዲያስቆም ጠይቋል።