ሐይቁ ላይ የሚታይ ጀልባ
የምስሉ መግለጫ,አንድ ጀልባ በሐይቁ ላይ

ከ 9 ሰአት በፊት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኘው ጫሞ ሐይቅ ላይ ሲጓዝ የነበረ ጀልባ ተገልብጦ ከአስር በላይ ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁ ተገለጸ።

ሐሙስ ጥቅምት 7/2017 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ከአርባ ምንጭ በጫሞ ሐይቅ ላይ ሙዝ እና 16 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረው ጀልባ ተገልብጦ 13 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን የጋሞ ዞን ፖሊስ ለቢቢሲ ገለጸ።

ሰዎች እና ምርት ጭኖ ሲጓዝ የነበረው ጀልባ የተነሳው ከኮሬ ዞን አቡሎ አርፋጮ ከሚባል አካባቢ ሲሆን መድረሻውም አርባ ምንጭ ከተማ እንደነበር ጋሞ ዞን ፖሊስ መመሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ረታ ተክሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጀልባው ላይ ሹፌሩን ጨምሮ 16 ሰዎች ሙዝ ጭነው ወደ አርባምንጭ ከተማ እየመጡ ነበር ያለው ፖሊስ፤ አደጋው ሲደርስ ሁለቱ ሰዎች ጀሪካን ይዘው በመንሳፈፍ ሕይወታቸውን ማትረፍ መቻላቸውን ይናገራሉ።

ተጨማሪ አንድ ሰው ወደ ሐይቁ ዳርቻ እየዋኘ ተሻግሮ በፍለጋው ወቅት በሕይወት መገኘቱን አክለው ገልጸዋል።

ኮማንደር ረታ ተክሉ ጀልባው የተገለበጠው ሐሙስ ዕለት ቢሆንም ስለአደጋው ለፖሊስ ጥቆማ የተሰጠው ግን ዛሬ አርብ ማለዳ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

አደጋውን ተከትሎ በሐይቁ ላይ ጄሪካን ይዘው በሕይወት መትረፍ የቻሉት ሁለት ሰዎችም ሆኑ ዋኝቶ መውጣት የቻለው አንድ ግለሰብ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ፖሊስ አስታውቋል።

የአደጋው መንስኤ ከጀልባው አቅም በላይ መጫን ሳይሆን እንዳልቀረ የተነገረ ሲሆን፣ በጀልባው ላይ የነበሩት ተሳፋሪዎች የቀን ሠራተኞች መሆናቸውን ኮማንደር ረታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን በበኩሉ 15ቱ የቀን ሠራተኞች ሙዝ ለመጫን ወደ ስፍራው የሄዱት ከአርባ ምንጭ ዙሪያ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን፣ ኮማንደር ረታ በበኩላቸው ማንነታቸውን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በጫሞ ሐይቅ ላይ አደጋው መድረሱን ለፖሊስ ከተገለጸ በኋላ ፍለጋ እየተደረገ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በሕይወት የተረፉም ሆነ የሞቱ ሰዎችን ማግኘት አለመቻሉን ፖሊስ አመልክቷል።

በጀልባ አደጋው ሐይቁ ውስጥ የሰመጡትን 13 ሰዎች የደረሱበትን ለይቶ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የአርባ ምንጭ ፖሊስ እና የከተማው ማኅበረሰብ በፍለጋው ላይ ተሰማርተው ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ኮማንደር ረታ ገልጸዋል።