
18 ጥቅምት 2024, 17:57 EAT
የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኻሊል አል-ሃያ የቡድኑ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አዛዥ የነበረው ያህያ ሲንዋር ጋዛ ውስጥ መገደሉን አረጋገጡ።
ሐሙስ እስራኤል ያህያ ሲንዋርን መግደሏን ይፋ ካደረገች በኋላ የሐማስ ምክትል መሪ በቪዲዮ በተላለፈ መልዕክት መሪያቸው መገደሉን ነገር ግን የእርሱ ሞት ቡድኑን የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል።
ባለሥልጣኑ ጨምረውም ሐማስ የፍልስጤማውያንን ምኞት እውን ለማድረግ የጀመረውን መንገድ የሚቀጥል መሆኑን እና እስራኤላውያን ታጋቾች የሚለቀቁት የእስራኤል ወረራ ሲያበቃ እንዲሁም ወታደሮቿ ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ሲወጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ኻሊል አል-ሃያ የእስራኤል ወታደሮች ጋዛ ውስጥ መደበኛ አሰሳ በሚያካሂዱበት ጊዜ መገደሉ ከተነገረው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ቀጥሎ የቡድኑ ከፍተኛው አመራር ናቸው።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት በርካታ አዛዦቹ የተገደሉበት የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው ቢገደልም “ፍልስጤም ነጻ እስክትውጣ ድረስ” ትግሉን እንደማያቆም ገልጿል።
- እስራኤል የሐማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን እንዴት አግኝታ ገደለችው?18 ጥቅምት 2024
- እስራኤል የገደለችው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነበር?17 ጥቅምት 2024
- “የሲንዋር መገደል ትልቅ ድል ቢሆንም የጦርነቱ ፍፃሜ አይደለም” ቤንያሚን ኔታንያሁ18 ጥቅምት 2024
አል-ቃሳም ብርጌድ የሚባለው የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ናወጣው መግለጫ ትግሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚጠይቅ መሆኑን እንደሚረዳ እና በትግሉ ሂደት ለሚከፈለው መስዋዕትነት ተዋጊዎቹ እና መሪዎቹ ዝግጁ መሆናቸውን አመልክቷል።
አል-ቃሳም ብርጌድ በመግለጫው “ለጠላቶች እንደማይገዛ” እና ትግሉ “ፍልስጤም ነጻ ወጥታ፤ የመጨረሻዎቹ ጽዮናውያን ከግዛቷ እስኪወጡ ድረስ የሚያቆም አይሆንም” ብሏል።
በኢራን የሚደገፈው ሐማስ ባለፈው ዓመት ሐምሌ የፖለቲካ መሪው ኢስማኤል ሃኒያ ኢራን ውስጥ መገደላቸው ይታወሳል።
እስካሁን እስራኤል ለግድያው ኃላፊነቱን ባትወስድም በርካቶች የእስራኤል ድርጊት መሆኑን ያምናሉ።
የሲንዋርን ግድያ ተከትሎ የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰኢድ አባስ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ሲንዋር “ሞትን ሳይፈራ በጀግንነት እስከመጨረሻው ተፋልሟል” ሲሉ አድናቆታቸውን በመግለጽ፤ የሲንዋር ሞት ፍልስጤማውያንን ለትግል የበለጠ ያነሳሳል ብለዋል።
የሐማስ አጋር የሆነው እና በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሔዝቦላህ በሲንዋር መገደል ማዘኑን ገልጾ “ለፍልስጤም ሕዝባችን የምናደርገውን ድጋፍ እንቀጥላለን” በማለት ቃል ገብቷል።
ሔዝቦላህ ያህያ ሲንዋርን “መታመን እና የመሪነት ችቦን” ከጥቂት ወራት በፊት በእስራኤል ከተገደሉት የቡድኑ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ የተረከበ “ሰማዕት” ነው ሲል አወድሶታል።
ከሳምንታት በፊት እስራኤል ከጋዛ ባሻገር ሊባኖስ ውስጥ እያካሄደች ባለው የአየር ኃይል እና የእግረኛ ጦር ዘመቻ የሔዝቦላህ መሪ ሐሳን ናስራላህን ጨምሮ በርካታ የቡድኑን መሪዎች መግደሏ ይታወቃል።