October 18, 2024 – Konjit Sitotaw

በአማራ ክልል በዳኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘፈቀደ እስር በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል›› የክልሉ ዳኞች ማህበር

በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለው የዳኞች አስር፣ ማዋከብና መሰል ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ካለፈው አንድ አመት ወዲህ ተባብሶ ቀጥሏል ያለው የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ድርጊቱን ባወጣው መግለጫ አውግዟል፡፡

የዳኞችን ነጻነት መጠበቅ ህገ-መንግስታዊ መብት ሆኖ የተደነገገ ቢሆንም ይህንን አክብሮ ከመንቀሳቀስ አኳያ መንግስት ዳተኝነት እየታየበት ነው ሲሉ የከሰሰው ማህበሩ ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኗል ሲል አስታውቋል፡፡

ማንኛውም ጥፋት ያለበት ግለሰብ በህግ አግባብ ተይዞ የማጣራት ስራዎች ይከናወኑበታል የሚለውን መሰረታዊ የህግ ሂደት በጣሰ መልኩም ዳኞችን በአደባባይ ማፈን አስሮም ያለፍርድ ማቆየት በክልሉ ተባብሶ የቀጠለ ጉዳይ ነው ሲል ወቀሳ አቅርቧል፡፡

አሁን ላይም 8 ያህል ዳኞች ያለምንም የፍርድ ሂደት ታስረው ይገኛሉ ያለው ማህበሩ ይህ አካሄድ ፍትህን ለማረጋገጥ በሚሰራው ስራ ላይ ጥላ የሚያጠላ ስለመሆኑም ጠቁሟል፡፡

የሰው ልጅ ነጻነት እንዲከበር ፣ዘላቂ ሰላምና የኢኮኖሚ እድገት እንዲመጣ የዳኝነት ነጻነትን መጠበቅ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማንሳትም የታሰሩ አባላቶቼ በአፋጣኝ እንዲፈቱ ሲል አሳስቧል፡፡