October 18, 2024 – Konjit Sitotaw
- ጥናቱ በኢትዮጵያ ከ86 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝብ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ብሏል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ባወጣው ሪፖርት በዓለም ከ1.1 ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በአስከፊ ድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ሀገራት ሲል ኦክስፎርድ የድህነት እና የሰብአዊ ልማት ኢኒሼቲቭ በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ከተጠቀሱት አምስት ሀገራት ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ድሆች መካከል ግማሽ ያህሉን እንደሚሸፍኑ የአለም ሁለገብ የድህነት መረጃ ሪፖርት አመላክቷል።
ይህን ተከትሎ ከአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ 86 ሚሊዮን በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን በመያዝ ቀዳሚ ስትሆን ፣ናይጄሪያ 74 ሚሊዮን እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 66 ሚሊዮን ዜጎችን በመያዝ ይከተላሉ፡፡
በመሆኑም የድህነት መጠን በጦርነት ውስጥ ባሉ ሀገሮች በሦስት እጥፍ ከፍ ያለ መሆኑን እና ሪፖርቱ የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ የአካባቢ ጽዳት፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ የምግብ ማገዶ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና የትምህርት ቤት ክትትልን የመሳሰሉትን መስፈርቶች እንደ ድህነት አመልካችነት መጠቀሙን አስታውቋል፡፡
በጥናቱ መሰረት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ህዝብ ዘርፈ ብዙ ድህነት ውስጥ እየኖረ ሲሆን፣ ከነዚህም 455 ሚሊዮን የሚሆኑት በግጭት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ተብሏል፡፡