የማህበራዊ ሚድያ ስልተ ቀመርን የሚያሳይ መግለጫ

ከ 4 ሰአት በፊት

የማኅበራዊ ሚድያ መድረኮች ላይ የሚሠራጩ መረጃዎች እና ተጠቃሚዎችን የሚዋቀሩበት ቀመር የሆነው አልጎሪምዝ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ እነሆ 15 ዓመት ሞላው።

አሁን የምናውቀው የማኅበራዊ ሚድያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር) የተወለደው በፌስቡክ ምክንያት ነው። ፌስቡክ በአውሮፓውያኑ 2009 ነው ለተጠቃሚዎቹ የተቀረፁ ይዘቶችን ማቅረብ የጀመረው።

ባለንበት ዘመን ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚድያ ሱስ እያሰቃያቸው ነው። አዋቂዎችም ከአልጎሪዝም ሱስ ያመለጡ አይመስሉም።

እርግጥ ነው አልጎሪዝምን ለመቆጣጠር ብዙዎች ሞክረዋል። የዓለም መንግሥታት እንኳ የተሳሳተ መረጃ እና ጎጂ ይዘቶችን ለመቆጣጠር በሚል አልጎሪዝምን ለመነካካት ሙከራ አድርገዋል።

የብራዚል መንግሥት የቀድሞውን ትዊተር የአሁኑን ኤክስ ለተወሰነ ጊዜ አግዶት ነበር። በስተመጨረሻ የቢሊየነሩ ኢላን መስክ ንብረት የሆነው ኤክስ የተዛባ መረጃ ያሠራጫሉ የተባሉ ገፆችን እዘጋለሁ ማለቱን ተከትሎ የብራዚል መንግሥት ፈቃዱን መልሶለታል።

የብራዚል ባለሥልጣናት ኤክስ ይዘጋ ያሉት ባለፈው ምርጫ ወቅት ውጤቱን ያልተቀበሉ ገፆች ይዘጉ በማለት ነው።

የአውሮፓ ኅብረት ደግሞ ማኅበራዊ ሚድያዎች ምርጫ ላይ ጣልቃ የሚገቡ ገፆችን መቆጣጠር ካልቻሉ ከገቢያቸው 6 በመቶውን እንዲቀጡ ባስ ካለም ሊታገዱ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። ኅብረቱ ይህን የተመለከተ አዲስ ሕግም አውጥቷል።

የዩናይት ኪንግደም መንግሥት በበኩሉ በቅርቡ ያወጣው አዲስ ሕግ ማኅበራዊ ሚድያዎች የይዘት ቁጥጥራቸውን ጠበቅ እንዲያደርጉ ያስገድዳል።

ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ የቻይናው ቲክቶክ ኩባንያ ካልተሸጠ አሜሪካ ውስጥ ሊታገድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ይህን እያደረጉ ያሉት መንግሥታት የመናገር ነፃነት እና የኢንተርኔት መሠረታዊያንን እየናዱ ነው የሚል ወቀሳ እየቀረበባቸው ይገኛል።

አዳም ካንደብ የሕግ ፕሮፌሰር እና የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ አማካሪ ነበሩ። አዳም ራሳቸውን የመናገር ነፃነት አርማ አድርገው ነው የሚቆጥሩት።

ማኅበራዊ ሚድያ “ፅንፍ እየያዘ ነው። በተለይ ሕዝባዊ ውይይት ለማድረግ የማይመች መድረክ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ። ነገር ግን በርካታ መንግሥታት ማኅበራዊ ሚድያን ለመቆጣጠር እያደረጉ ያለውን ጥረት አይደግፉትም።

“ግልፅ እና አሁናዊ የሆነ አደጋ ከሌለ በቀር፤ ትክክለኛ የሚሆነው አካሄድ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲስተናገዱ ማድረግ ነው” የሚል አስተያየት ይሰጣሉ።

የማህበራዊ ሚድያ ስልተ ቀመርን የሚያሳይ ገላጭ ፎቶ

ኢላን መስክ በአውሮፓውያኑ 2022 የቀድሞውን ትዊተር ገዝቶ ኤክስ ብሎ ሲሰይመው ይህ ማኅበራዊ ሚድያ “ዲጂታል ታውን ስኩዌር ነው” አሊያም ሰዎች የሚሰበሰቡበት አደባባይ ነው ማለቱ ይታወሳል።

የዬል ዩኒቨርሲቲ መምህሯ አሻ ራንጋፓ “መስክ የረሳው ነገር ቢኖር በማኅበራዊ ሚድያ እና በአደባባይ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑን ነው” ይላሉ።

“እርግጥ ነው ሐሳቦች ያለምንም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መፋጨት አለባቸው” የሚሉት አሻ ነገር ግን እንደ ትዊተር ያሉ ማኅበራዊ ሚድያዎች በአካል እንደምናውቀው አደባባይ አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚሠራጩ ሐሳቦች በክብደታቸው ምክንያት ሳይሆን በአልጎሪዝም ምክንያት እንደሆነ የአሻ ይከራከራሉ።

አልጎሪዝሞች ባህርያችንን አጥንተው ወደ በይነ መረብ ስንመጣ ምን መመልከት እንደምንፈልግ ሞርደው አዘጋጅተው ይጠብቁናል። አንዳንድ ተጠቃሚዎች በአልጎሪዝም ምክንያት የተለያዩ ሐሳቦችን ከመመልከት ይልቅ ውሱን የሆነ ይዘት ነው የሚገጥማቸው።

ፌስቡክ አልጎሪዝምን ወደ ማኅበራዊ ሚድያ ካመጡ መድረኮች መካከል ቀንደኛው ነው። ሦስት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ፌስቡክ በጣም ትልቅ መድረክ ካላቸው ማኅበራዊ ሚድያዎች አንዱ ነው።

ከ15 ዓመታት በፊት ፌስቡክ አልጎሪዝምን ለገበያ ሲያቀርብ ተጠቃሚዎች የሚከተሏቸውን ሰዎች ይዘት በማየት ፈንታ ፌስቡክ እንዲያዩ የሚፈልገውን ነገር ነው የሚቀርብላቸው ማለት ነው።

የቲክቶክ ዋናው መሣሪያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር) ነው።

ይህ መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን ታሪክ ተመልክቶ የትኛውን ዓይነት ይዘት ይወዳሉ የሚለውን የሚለይበት ዘዴ ነው።

ወደ ቲክቶክ ሲገቡ ከላይ ሦስት ንዑስ ርዕሶችን ያገኛሉ። ፎሎዊንግ፣ ፍሬንድስ እና ፎር ዩ ይባላሉ።

ፎሎዊንግ እና ፍሬንድስ ተጠቃሚዎች ከሚከተሏቸው ሰዎች እና ከጓደኞቻቸው የሚያገኟቸው ይዘቶች ናቸው።

ፎር ዩ የተሰኘው ደግሞ ቲክቶክ በራሱ መርጦ እና መጥኖ ተጠቃሚዎች ይህን ይዘት ይወዱታል በሚል የሚለቀቅ ነው።

ተቺዎች ቲክቶክ ከሌሎች ማኅበራዊ ሚድያዎች በላይ የተጠቃሚዎችን መረጃ ይሰበስባል፤ ለዚህም ነው የተመረጡ ይዘቶችን የሚያቀርበው ይላሉ።

የማህበራዊ ሚድያ ስልተ ቀመርን የሚያሳይ ገላጭ ፎቶ

በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ይዘቶች በአልጎሪዝም ምክንያት ወደ በርካታ ሰዎች ሊደርሱ ይችላሉ። የአልጎሪዝም ተቺዎች እንደሚሉት ይህ ቴክኖሎጂ ነፃ ሐሳቦችን ከማንሸራሸር ይልቅ የተጋነኑ ይዘቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ይላሉ።

ማኅበራዊ ሚድያዎች መንግሥት የመናገር ነፃነትን እያፈነ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። ነገር ግን የራሳቸው አልጎሪዝም ለራሳቸው መጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆን ነው?

አሁን የምንኖርበት ዘመን ‘የአልጎሪዝም ዘመን’ የተባለ መጠሪያ ተሰጥቶታል።

የቢቢሲ አንድ ጥናት እንዳሳየው አንድ ታዳጊ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ ቲክቶክ እና ኢንስታግራም ላይ አመፅ እና ለሴቶች የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ይዘቶችን ማየት እንደማይሻ ቢያሳውቅም ደጋግሞ ይመጣለታል።

አልጎሪዝምን በተመለከተ ያለው አንድ ተስፋ ወደፊት በትላልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሳይሆን በተጠቃሚው እጅ ላይ ይወድቃሉ የሚለው እሳቤ ነው።

በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በአሜሪካ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች እንደቀድሞው ሕይወታቸውን በፎቶ እየመዘገቡ ማጋራት እያቆሙ ነው።

የፌስቡክ፣ የዋትስአፕ እና የኢንስታግራም እናት ኩባንያ የሆነው የሜታ ተጠቃሚዎች እንደ ቀድሞው ለሚያውቁትም ለመያውቁትም ፎቶ ማጋራት ትተዋል ሲል ቁጥሩን መቀነሱን ዘግቧል።