የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በፒዮንግያንግ በወታደራዊ ትርዒት ላይ

ከ 4 ሰአት በፊት

ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ከሩሲያ ጋር ወግና ለመፋለም ወታደሮቿን መላክ መጀመሯን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት አስታወቀ።

ይህንን የሰሜን ኮሪያ እርምጃ “ከፍተኛ የደህንነት ስጋት” ስትል ደቡብ ኮሪያ ፈርጃዋለች።

ይህ የተሰማው የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ 10 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ጦርነቱን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ የደህንነት መረጃዎች ተገኝቷል ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዚዳንት ዩን ሱክ ዮል አርብ፣ ጥቅምት 8/ 2017 ዓ.ም በጠሩት የጸጥታ ስብሰባ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “በሁሉም መንገዶች” ምላሽ መስጠት አለበት ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ የስለላ ድርጅቱ ከሆነ እስካሁን 1 ሺህ 500 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ ገብተዋል። አጠቃላይ ለሩሲያ ወግነው የሚዋጉ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12 ሺህ ሊጠጋ እንደሚችል የደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎች ስማቸው ያልተጠቀሱ ምንጮችን ዋቢ አድርገው ዘግበዋል።

በዩክሬን ፖልታቫ ግዛት ውስጥ ከሚሳኤል ቁርጥራጭ በተገኘ መረጃ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ታቀርባለች የሚሉ ማስረጃዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ በቅርብ ወራት ውስጥ ትብብራቸውን እያሳደጉ መጥተዋል።

ለዚህም ማሳያዎች አንዱ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ልደት ዕለት ደውለውላቸው “የቅርብ ጓዴ” ሲሉ መጥራታቸው ተዘግቧል።

አርብ ዕለት በተካሄደው የጸጥታ ስብሰባ ላይ የደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ ደህንነት ቢሮ፣ የብሔራዊ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ የደህንነት መረጃ አገልግሎት የተውጣጡ ቁልፍ ባለስልጣናት መሳተፋቸውን የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

“ተሳታፊዎቹ ሁኔታውን ችላ ሳይሉ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ጋር ተጣምረው ያለውን አቅም ሁሉ በመጠቀም በጋራ ምላሽ ለመስጠት ወስነዋል” ብሏል መግለጫው

የደቡብ ኮሪያ የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ክስ የመጣው የዩክሬን ወታደራዊ መረጃ ምንጮች የሩሲያ መከላከያ የሰሜን ኮሪያ ጦር ክፍል እየመሰረተ መሆኑን ከገለጹ ከቀናት በኋላ ነው።

የዩክሬን የስለላ ድርጅት ኃላፊ ኪሪሎ ቡዳኖቭ በዩክሬን ለመዋጋት ወደ 11 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ እግረኛ ወታደሮች በምስራቅ ሩሲያ እየሰለጠኑ እንዳሉ በዚህ ሳምንት ተናግረዋል።

ከነዚህም ውስጥ 2 ሺህ 600 የሚሆኑት ወታደሮች ዩክሬን በነሐሴ ወር ወደ ወረረቻቸው የሩሲያ ምዕራባዊ ከርስክ ግዛት እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ፑቲን ከኪም ጋር በሁለቱም አገራት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለመቀልበስ ለመተጋገዝ የተስማሙበትን ወታደራዊ ስምምነት ለማጽደቅ ረቂቅ ሕግ አውጥተዋል።