ባትሪ ተይዞላት ውሃ የምታፈላ ሴት

ከ 3 ሰአት በፊት

በኩባ በመላ አገሪቱ ኤሌትሪክ ተቋርጦ 10 ሚሊዮን ሰዎች በጨለማ ውስጥ መሆናቸው ተገለፀ።

በአገሪቱ የኤሌትሪክ መቋረጥ የተፈጠረው የአገሪቱ ዋነኛ ኃይል ማከፋፈያ በመበላሸቱ እንደሆነ ተገልጿል።

አርብ ዕለት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ጀምሮ የአገሪቱ ኃይል መቆጣጠርያ መበላሸቱን የኃይል ሚኒስትር በማህበራዊ ድረገጹ ላይ አስታውቋል።

የኃይል መቆጣጠርያው ኃላፊዎች በበኩላቸው ብልሽቱን ጠግኖ ዳግም ስራ ለማስጀመር ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ ማወቅ እንደማይቻል ተናግረዋል።

አገሪቱ ለወራት የዘለቀ የኃይል መቆራረጥ የገጠማት ሲሆን ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሙስ ዕለት “የኤሌትሪክ ኃይል አስቸኳይ ጊዜ” አውጀዋል።

አርብ ዕለት በመላ አገሪቱ ያጋጠመው የኃይል መቋረጥ በማታንዛስ የሚገኘው አንቶኒዮ ጉታሬስ የተባለው የአገሪቱ ትልቁ የኃይል ማከፋፈያ በመጥፋቱ ነው ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል ቤርሙዴዝ ጉዳዩን “ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚከታተሉት” ተናግረዋል።

“ኤሌትሪክ ዳግም ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ እረፍት የለም” ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

በአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ውስጥ የኤሌትሪክ አቅርቦት ኃላፊ ላዛራ ጉየራ የኤሌትሪክ ኃይል ዳግም እንዲመጣ የማድረግ ስራው ገና መጀመሩ መሆኑን መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ኃላፊዋ አክለውም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ “ የተወሰኑ ጄኔሬተሮች” እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አርብ ዕለት አስቀድሞ ሁሉም ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም አስፈላጊ ያልሆኑ ተብለው የተለዩ እንደ ምሽት ጭፈራ ቤቶች ያሉ አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ሰኞ ድረስ ዝግ እነዲሆኑ መꬅወሰኑ ተገልጾ ነበር።

የኤሌትሪክ አቅርቦትንም ለመቆጠብ በሚል አስፈላጊ ያልሆኑ የተባሉ የመንግሥት አገልግሎቶች ሲቋረጡ፣ የእነዚህ ተቋማት ሰራተኞችም ቤታቸው እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

ኩባውያን እንደ ፍሪጅ፣ ኦቭን ያሉ እና ከፍተኛ የኤሌትሪክ ፍጆታ የሚጠቀሙ መገልገያዎች የኃይል መጨናነቅ ባለበት ሰዓት እንዲያጠፉ ተጠይቀዋል።

በማዕከላዊ ሐቫና ነዋሪ የሆኑት የ80 ዓመቱ ጡረተኛ ኤሎይ ፎን “ይህ እብደት ነው” ሲሉ ለኤኤፍ ፒ ተናግረዋል።

“የኤሌክትሪክ ስርዓታችን ምን ያህል ለአደጋ ተጋላጭ እንደሆነ ነው የሚያሳየው. . . መጠባበቅያ የለንም፤ የአገሪቱን ኃይል ለማስቀጠል ምንም ዓይነት አማራጭ የለም፤ እንደዚያ ነው በየዕለቱ የምንኖረው”

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለዩ ቪድዮዎችን በመስራት እና በማጋራት የምትታወቀው የ47 ዓመቷ ባርባራ ሎፔዝ በበኩሏ “ለሁለት ቀናት በመከራ ነው መስራት የቻልኩት” ስትል ትናገራለች።

“በ47 ዓመቴ ካየሁት ሁሉ የባሰው ነው። አሁን ሁሉም ነገር መስመሩን ስቷል። ኤሌክትሪክም ሆነ የሞባይል ዳታ የለንም” ትላለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ማሬሮ ሐሙስ ዕለት በቴሌቪዥን ቀርበው ለአገሪቱ ሕዝብ ባደረጉት ንግግር የመሰረተ ልማቶች ማርጀት፣ የነዳጅ እጥረት መኖሩ እና የኤሌትሪክ ፍጆታ መጨመርን ለኃይል መቆራረጡ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

“የነዳጅ እጥረቱ ትልቁን ድርሻ ይይዛል” ነበር ያሉት በዚሁ ንግግራቸው ላይ።

የአገሪቱ ብሔራዊ ኤሌትሪክ ማሕበር ኃላፊ አልፍሬዶ ሎፔዝ ቫልዴስ አገሪቱ የኤሌትሪክ አቅርቦት ቀውስ እንደገጠማት አምነው፣ እጥረት ያሉትን በደፈናው ተጠያቂ አድርገዋል።

በኩባ የተራዘመ የኤሌትሪክ መቋረጥ፣ በተለይ እንደ አሁኑ ያለ፣ በመላ አገሪቱ ሲከሰት በኩባ ውጥረት ይፈጥራል።

መንግሥት በበኩሉ በተቻለው አቅም ኤሌትሪክ ወደነበረበት ተመልሶ ሕዝቡን ቢያረጋጋ ይመርጣል።

በአውሮፓውያኑ 2021 ሐምሌ ወር ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባውያን በአገሪቱ ለቀናት የዘለቀውን የኃይል መቋረጥ ተከትሎ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።

ፍሪጆች ባለመስራታቸው የሚበላሹ ምግቦች፣ አየር ማቀዝቀዣዎች ባለመስራታቸው በደሴቲቱ ሙቀት ለሚነዱት ዜጎች የኤሌትሪክ መቋረጥ ዋነኛ የቁጣ ምንጭ ነው።

በበርካታ ሕንጻዎች የኤሌትሪክ ፓምፖች ውሃ በመግፋት እንዲዳረስ የሚያደርጉ ቢሆንም ኤሌትሪክ በሚቋረጥበት ወቅት ውሃ አይኖርም ማለት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ፓምፖቹን ለማንቀሳቀስ ነዳጅ አለመኖሩ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ስራቸውን ለመስራትም ሆነ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መኪናቸውን አይጠቀሙም።

የኩባ መንግሥት ዜጎች በየዕለቱ ስለሚገጥማቸው ችግር አደባባይ ወጥተው ለመናገር እንደማያመነቱ እየተረዳው የመጣ ይመስላል።

አንዳንዶች ፀረ መንግሥት መፈክር ይዘው አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ለማሰማት አያንገራግሩም።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የኩባ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት በምትባለው ሳንቲያጎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በምግብ እጥረት እና በኃይል መቆራረጥ የተነሳ አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።

በሐቫና ጥቂት ሕንጻዎች ብቻ ኤሌትሪክ አላቸው