
ከ 1 ሰአት በፊት
በምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ‘የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አላከበረችም’ በሚል ከዛፍ ጋር ታስራ በባለቤቷ የተደበደበችው እናት በአስጊ ጤና ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የቤተሰብ አባሏ ተናገሩ።
በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ሆስፒታል በህክምና ላይ የምትገኘው ኩሹ ቦናያ የተባለችው እናት በደረሰባት ግርፋት ክፉኛ ተጎድታ “የአካሏ ግራ ክፍል አይሰራም። የራስ ቅሏ ተሰብሯል” በማለት የቤተሰብ አባሏ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአካባቢው አቃቤ ሕግ በበኩላቸው ግርፋቱን መፈጸማቸው የተጠረጠሩ ባለቤቷን ጨምሮ ስምንት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መካሄዱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው እናት በኦሮምያ ምስራቅ ቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ የሽማግሌዎችን ትዕዛዝ አልተቀበለችም በሚል ከዛፍ ጋር ታስራ በባለቤቷ የተገረፈችው ግለሰብ በአሁን ሰዓት በሐዋሳ ሆስፒታል የሕክምና ክትትል እያደረገች መሆኑ ተገልጿል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች መካከል የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፈዋል የተባሉት ሽማግሌዎች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ሲለቀቁ ባለቤቷ ግን አሁንም በቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አቃቤ ሕግ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን ሴት ዋጪሌ ገበያ ላይ አስሮ የመግረፉ ድርጊት የተፈጸመው ባለፈው ወር መስከረም 9/ 2017 ዓ.ም. መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
ጥቃቱ የደረሰባት ሴት ዘመድ የሆኑት ጃርሶ ቡሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግርፋቱ የተፈጸመባት ግለሰብ ኩሹ ቦናያ የምትባል ስትሆን፣ ገራፊው ደግሞ ባለቤቷ ገልገሎ ዋሪዮ መሆኑን ተናግረዋል።
ኩሹ እና ባለቤቷ ገልገሎ በትዳር 12 ዓመት መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ጃርሶ፣ በኑሯቸው ችግር ውስጥ ሲወድቁ ባለቤቷ ወደ ውትድርና መግባቱን ይናገራሉ።
“በውትድርና አራት ዓመት ያህል ቆይቷል” የሚሉት አቶ ጃርሶ ባለቤቱ ልጆቿን ለማሳደግ ብቻዋን ስትጥር መቆየቷን ይመሰክራሉ።
ገልገሎ ከውትድርና ከተመለሰ በኋላ ግን ባለቤቱን መደብደብ መጀመሩን የሚናገሩት የሚስት ዘመድ፣ “በተደጋጋሚ ወደ ቤተሰቦቿ እየሸሸች ሁኔታዎች ሲረጋጉ ወደ ቤቷ ትመለስ ነበር” ይላሉ።
ገልገሎ ከውትድርና ከተመለሰ በኋላ ከባለቤቱ ጋር መስማማት አለመቻሉን፣ ዘወትር ባለቤቱን እና ልጆቹን የሚደበድብ እንደነበርም ጨምረው ተናግረዋል።
በአገር ባህል መሰረት ሽማግሌዎች በባለትዳሮቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተደጋጋሚ ለሽምግልና መቀመጣቸውን የሚጠቅሱት ግለሰቡ “ችግሮች ሳይፈቱ ሲቀሩ ወደ አባቷ ቤተሰብ ሸሸች። ሽማግሌዎች ተነጋግረው ባለቤቷ ጠባዩን እንዲያሻሽል እርሷም ወደ ቤቷ እንድትመለስ መከሯት። እርሷ ግን ነገሩን በደንብ እንዲያጤኑት ወደ ቤቷ ብትመለስ አንደሚገላት’ ተናገረች” ይላሉ።
የሽማግሌዎቹን ቃል እንዳላከበረች የተቆጠረችው ኩሽ ግን ሽማግሌዎቹ የወሰኑባት ታስራ እንድትገረፍ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዘመዷ ይገልጻሉ።
የሽማግሌዎቹ ውሳኔ የቦረናን ባሕል አይወክልም የሚሉት አቶ ጃርሶ፣ ይህ የጥቂት ሰዎች ውሳኔ ነው ሲሉ ያክላሉ።
“በሚኖሩበት አካባቢ ባለ ዛፍ ላይ አሰሯት። ይህንን ያደረጉት ልጇ እያለቀሰ፣ ሌሎች ቆመው እያዩ ነው” ሲሉ ያክላሉ።
በስፍራው ተገኝተው የነበሩ በሙሉ ፎቶ እንዳያነሱ፣ ቪድዮ እንዳይቀርጹ ተከልክለው አንደነበር የሚናገሩት ግለሰቡ “ስትገረፍ ከዋጪሌ ዱብሉቅ አንድ መኪና በድንገት መጣ። አንድ ልጅ ከመኪናው ወርዶ ቪድዮ መቅረጽ ጀመረ” ያሉት ጃርሶ በዚህም የተፈጸመውን ወንጀል ሌሎች ሊያዩት እንደቻሉ ያብራራሉ።
- በትግራይ ሙሽሪት ሰርጓ በተፈጸመ በአራተኛው ቀን በባለቤቷ መገደሏን ፖሊስ አስታወቀ18 ጥቅምት 2024
- በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ18 ጥቅምት 2024
- በኩባ በተፈጠረ የኤሌትሪክ መቋረጥ 10 ሚሊዮን ዜጎች ጨለማ ውስጥ መሆናቸው ተገለጸከ 3 ሰአት በፊት
የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ኩሹ በዛፍ ላይ ታስራ በባለቤቷ ግርፋት ከደረሰባት በኋላ ክፉኛ መጎዳቷን የቤተሰብ አባሏ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የአካሏ ግራ ክፍል አይሰራም። የራስ ቅሏ ተሰብሯል” ይላሉ።
የቤተሰብ አባላቶቿ የደረሰባትን ወድያውኑ አለመስማታቸውን አክለው ለሳምንት ያህል ሕክምና ሳታገኝ መቆየቷን ጨምረው ገልጸዋል።
“ወንጀሉ አንደተፈጸመ ወድያውኑ ቪድዮው አልተለቀቀም ነበር። ከሳምንት በኋላ ነው ሰው ያየው። ወላጆቿም የሆነውን ያዩት ከቪድዮው ላይ ነው” ብለዋል።
ኩሹ መጀመርያ በአሬሮ ሆስፒታል በኋላም ወደ ያቤሎ ሆስታል ሄዳ ሕክምና የተከታተለች ቢሆንም የተሻለ ሕክምና በማስፈለጉ ወደ ሐዋሳ ሆስፒታል ተልካለች።
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ባለቤቷ እንዲሁም የግርፋት ውሳኔውን ያሳለፉ ሽማግሌዎችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች መታሰራቸውን ይናገራሉ።
የዋጪሌ ወረዳ አቃቤ ሕግ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጉዮ አሬሮ ጥቃቱ በቃቃሎ መንደር መፈጸሙን እና ከተፈጸመ ከሳምንት በኋላ ሪፖርት መደረጉን ይናገራሉ።
“መረጃው እንደደረሰን የምርመራ ቡድን በማዋቀር መረጃ መሰብሰብ ጀምረናል” ሲሉም ያስረዳሉ።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ሽማግሌዎቹ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ሲለቀቁ ባለቤቷ ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ ጨምረው ተናግረዋል።
“ክስ ለመመስረት የሕክምና ማስረጃ እንፈልጋለን። አሁንም የሕክምና ክትትል እያደረገች በመሆኑ መረጃው ገና ተጠናክሮ አልቀረበልንም። ሕጋዊው ጉዳይ ግን ሂደቱን ጠብቆ ይቀጥላል” ብለዋል።
