በጃባሊያ በእስራኤል የአየር ጥቃት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየሩ የመኖርያ ሕንጻዎች

ከ 4 ሰአት በፊት

የሐማሱ መሪ ግድያን ተከትሎ እስራኤል በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 21 ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 33 ሰዎች መገደላቸውን የሐማስ ባለስልጣናት ገለፁ።

እስራኤል ጦሯ በከበበው ጃባሊያ ስላደረሰው ጥቃት ያለችው ነገር የለም።

የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር በዚህ ሳምንት መገደሉን ተከትሎ ጦርነቱ ሊያበቃ ይችላል የሚል ተስፋ የጫረ ቢሆንም፣ የቡድኑ ምክትል ግን የመሪያቸው መገደል ሐማስን ያጠናክረዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በሊባኖስ ከሔዝቦላ የምታደርገውን ጦርነት በማቆም “ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለመስራት እድል እንዳለ” ገልፀው “በጋዛ ግን አስቸጋሪ” እንደሚሆን ተናግረዋል።

ባይደን ይህንን ያሉት የጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝ መሪዎቸን ለማግኘት ወደ ጀርመን ጉዞ ሲጀምሩ ነው።

ጋዛን ከሚያስተዳድረው የሐማስ መንግሥት መገናኛ ብዙኀን ቢሮ የወጣው መግለጫ እንደሚያስረዳው አርብ ዕለት የደረሰው የአየር ጥቃት ከ85 ሰዎች በላይ ጉዳት ሲደርስባቸው፣አንዳንዶቹ የከፋ፣ በመጠለያ ውስጥ የሦስት ሰዎች ቤት ዒላማ ተደርጎ ተመትቷል።

መግለጫው አክሎም የሟቾች ቁጥር 50 እንደሚደርስ ገልጾ ሰዎች በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ ገልጿል።

ቢቢሲ የቡድኑን መግለጫ በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

ከአካባቢው የተገኙ ምንጮች ግን ሰሜናዊ ጋዛ ከስልክ እና ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ መቆራረጣቸውን ይገልጻሉ።

ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን ያላረጋገጠው እና በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወር የተመለከተው ተንቀሳቃሽ ምስል በአል አውዳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ በነጭ ጨርቅ የተጠቀለሉ በርካታ አስከሬኖች ተጥለው ይታያሉ።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ለጋዜጠኞች በርካታ ቁጥር ያላቸው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ሆስፒታላቸው እንደሚመጡ ተናግረዋል።

“የአምቡላንስ ሰራተኞች በጃባሊያ የተገደሉ እና የተጎዱትን ለማንሳት ጥረት እያደረጉ ነው” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

“ሆስፒታላችን ሙሉ በሙሉ የሞላ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውን ሕክምና እንዲያገኙ እያደረግን ያለነው መሬት ላይ አስተኝተን ነው”

እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ከሆነ በጋዛ በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አርብ ዕለት በጃባሊያ እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት 39 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

በስደተኞች መጠለያ ጣብያው 400,000 ስደተኞች ላለፉት ሁለት ሳምንታት አነሰተኛ ምግብ እና ውሃ ብቻ እያገኙ በተጨናነቀ ሁኔታ እየኖሩ መሆኑ ተሰምቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ የሆኑት ጂኦርጂዮስ ፔትሮፖውሎስ ለቢቢሲ ኒውስ አወር ፕሮግራም እንደተናገሩት ከሆነ በጃባሊያ የሚኖሩ ቤተሰቦች “በሰቅጣጭ ሁኔታ” እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡባዊ ጋዛ ራፋ ሆነው “በዚያ ያለው ሁኔታ ለሰላማዊ ሰዎች የከፋ እና አደገኛ መሆኑን ለማሳየት ምንም ያህል ብንጮህ ገላጭ አይሆንም” ብለዋል።

እስራኤል አርብ ዕለት ወደ ጋዛ ምግብ፣ ውሃ የመጠለያ እና የሕክምና ቁሳቁስ የጫኑ 30 የጭነት መኪኖችን መላኳን የገለፀች ቢሆንም፣ የአካባቢው ባለስልጣናት ግን ለሮይተርስ ተልኳል የተባለው እርዳታ እንደ ጃባሊያ ባሉ ስፍራዎች አለመድረሱን ተናግረዋል።

እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ ከልክላለች የሚለውን ክስ በተደጋጋሚ ያስተባበለች ሲሆን አሜሪካ በበኩሏ እርዳታ ወደ አካባቢው እንዲገባ ካላደረገች የተወሰነ ወታደራዊ እርዳታ እንደሚቋረጥ ማስጠንቀቋ ይታወሳል።

የእስራኤል ሚኒስቴር የሆኑት አሚቻይ ቺክሊ ለቢቢሲ አገራቸው የሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያን ጨምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች “መዝጋቷን” ተናግረው ነበር።

“ሰላማዊ ዜጎች ደህንነቱ ወደተጠበቀበት ስፍራ እንዲሸሹ ፈቅደናል። ወደ ተዘጋው ስፍራ ደግሞ ምንም ዓይነት አቅርቦት እንዳይገባ አግደናል” ሲሉ ነበር ለኒውስ አወር ፕሮግራም የተናገሩት።

ሚኒስትሩ “ይህ በዓለም አቀፍ ሕግ ሕጋዊ” መሆኑን ተከራክረዋል።

ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከከፈተበት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በጋዛ ቢያንስ 42,500 ሰዎች መገደላቸውን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መቁሰላቸውን የሐማስ ባለስልጣናት ይናገራሉ።

በሐማስ እና አጋሮቹ 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ተወስደዋል።

አርብ ዕለት የሐማስ ምክትል መሪ ካህሊል አል ሀያ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት እስክታቆም እና አካባቢውን ለቅቃ እስክትወጣ ድረስ የታገቱ ዜጎቿ አንደማይለቀቁ ተናግረዋል።

አርብ ዕለት እስራኤል በሊባኖስ ከሔዝቦላህ ጋር የምታደርገው ጦርነት ቀጥሎ ውሏል።

የእስራኤል ጦር ሰራዊት 60 የሔዝቦላህ ተዋጊዎችን መግደሉን ሲያሳውቅ፣ ሔዝቦላህ በበኩሉ ወደ እስራኤል ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ገልጿል።