October 19, 2024 – Konjit Sitotaw 

በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ልደታ ቅርንጫፍ የተከሰተ እውነተኛ ክስተት።

አለምነሽ የመኪና ቦሎ ለማደስ ወደ ልደታ ቅርንጫፍ ትራንስፖርት ቢሮ በማለዳ ተገኘች። አስፈላጊዎቹን ሰነዶች በሙሉ ይዛ እና ትክክለኛውን ክፍያ ከፍላ ቁጥር ወስዳ ለመጠበቅ ተቀመጠች። ሰዓታት አለፉ። ከእርሷ በኋላ የመጡ ሰዎች እንዴት እንደሆነ ሳይታወቅ ከእርሷ በፊት ወደ ቆጣሪው ተጠሩ።

በመጨረሻም ቁጥሯ ተጠራ። ተስፋ በማድረግ ወደ ቆጣሪው ቀረበች። አበበ የተባለው የደንበኛ አገልግሎት ባለሙያው ሰነዶቿን በጨረፍታ ተመለከተና አለምነሽ መኖርዋን ችላ በማለት ከሥራ ባልደረባው ጋር ስለ እግር ኳስ ጨዋታ መወያየት ጀመረ ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ወደ እርሷ ዞር ብሎ አንድ ፎርም እንደጎደላት ነገራት። አለምነሽ ሁሉም ነገር እንዳላት አጥብቃ ተናገረች፣ ነገር ግን የደንበኛ አገልግሎት ባለሙያው “ሁሉንም ነገር ይዘሽ ስትመጪ ተመለሺ” በማለት እጁን በማወናጨፍ ነገራት።
ግራ በመጋባት አለምነሽ ሰነዶቿን ደጋግማ አጣራች። “የጎደለውን” ፎርም አገኘችው ፣ ሰነዱ እያለ የለም ማለቱ አበሳጫት። ወደ ቆጣሪው ተመለሰች፣ ነገር ግን የደንበኛ አገልግሎት ባለሙያው ስህተቱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። አዲስ ቁጥር ወስዳ የመጠበቅ ሂደቱን እንደገና መጀመር እንዳለባት አጥብቆ ነገራት።

ይህ ምሳሌ የህዝብን መንገላታት ፣ ፍትህ ማጣትን እና ቁጣን የሚያባብሱ መሰል ጉዳዮችን ያሳያል፡-

• ረጅም የመጠበቅ ጊዜ እና ያልተደራጀ የደንበኞች አገልግሎት አሰራር ስርዓት ውጤታማ ሂደቶች አለመኖራቸውን ያመለክታሉ።
• በመንግስት መስሪያ ቤቶች ያሉ የደንበኛ አገልግሎት ባለሙያውች ለህዝቡ ያላቸውን ንቀትን ፣ አመለካከትን እና የህብረተሰቡን ጊዜ ችላ በማለት ለሚያገለግሉት ህዝብ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳያል።
• ተጠያቂነት ማጣት: የደንበኛ አገልግሎት ባለሙያው ስህተቱን አለመቀበሉ እና አለምነሽ ሁኔታውን እንድትፈታ ለመርዳት ፈቃደኛ አለመሆኑ ተጠያቂነት ማጣትን ያሳያል።

ይህ ዓይነቱ ተሞክሮ ዜጎች ለአላስፈለጊ እንግልት፣ አግልግሎትን መሰረት ያላደረገ ወጪ፣ተደጋጋሚ ምሬት እና ህዝባዊ ቁጣን በሚያስከትል እና ማህበረሰቡ አቅም እንደሌለው እናበተቋማት ተስፋ መቁረት እንዲሰማቸው ያደርጋል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች ህዝብን ከማገልገል ይልቅ በቢሮክራሲ እና በስልጣን ላይ የበለጠ ያተኮሩ ናቸው የሚለውን ግንዛቤ ያጠናክራል።

Andafta