
October 20, 2024
በምሥራቅ ደረጀ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ ሚዲባሶችና የከተማ አውቶቡሶች እጅግ ከፍተኛ የሚባል የአገልግሎት ታሪፍ ጭማሪ አድርጓል።
በአዲሱ ታሪፍ መሠረት 4 ብር ከ50 የነበረው የሚኒባስ ትራንስፖርት ታሪፍ 10 ብር፣ በተመሳሳይ 8 ብር ከ50 ሳንቲም የነበረውን 15 ብር፣ 13 ብር የነበረውን 20 ብር፣ 17 ብር የነብረውን 25 ብር፣ 30 ብር የነበረውን 40 ብር፣ 47 ብር የነበረውን 60 ብር፣ 51.5 ብር የነበረውን 65 ብር አድርጓል። በሌሎች የጉዞ ርቀቶችም እንዲሁም ተመሳሳይ የሆነ ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ በማድረግ ከጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል።
የተደረገው ከፍተኛ የታሪፍ ማሻሻያ ወቅታዊ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ያማከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ቢገልጽም፣ ውሳኔው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታና ምሬትን ፈጥሯል። ሪፖርተርም በተለያዩ አካባቢዎች በመገኘት የሕዝቡን አስተያየት ሰብስቧል።
በተለምዶ አርሴማ ከሚባለው አካባቢ ተነስታ ስድስት ኪሎ አካባቢ የሚገኝ አንድ ባለፀጋ ሰው ቤት በተመላላሽ የቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ በምታገኘው ገቢ ኑሮዋን የምትገፋው ፀሐይ የተባለች አስተያየት ሰጪ፣ በወር አምስት ሺሕ ብር እንደሚከፈላት፣ አንድ ሴት ልጇን በመንግሥት ትምህርት ቤት እንደምታስተምርና ለቤት ኪራይ ደግሞ ሦስት ሺሕ ብር እንደምታወጣ ትገልጻለች። በወር ከምታገኘው ገቢ ላይ ከዚህ ቀደም ለትራንስፖርት እስከ 900 ብር አወጣ ነበር፣ አሁን በተደረገው ጭማሪ ግን በወር ለትራንስፖርት የምታወጣው ወደ 1,200 ብር እንደሚሆን ተናግራለች።
‹‹በዚህ ደመወዝ የትራንስፖርት ወጪ፣ የቤት ኪራይ ሸፍኜ ለልጄና ለራሴ ሚያስፈልገንን ለማሟላት አልችልም። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ዋጋቸው ጨምሯል፡፡ ምኑን ከምን እንደምናደርገው አናቅም አማራጭም የለንም። ድሮ ታክሲ ሲወደድብን በአውቶብስ እንሄድ ነበር አሁን የአውቶብሱም ዋጋ በጣም ጨምሯል፤›› በማለት ምሬቷን ገልጻለች።
ሰሜ አይገለጽ ያለችን የዩኒቨርስቲ ተማሪ በበኩሏ፣ ‹‹የምኖረው ቡራዩ ነው ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የማታ እማራለሁ፣ በቀን እየሠራው ነው እራሴን ማስተዳደረው። የትራንስፖርት ወጪዬን ካሰላነው ከቡራዩ አስኮ፣ ከአስኮ ፒያሳ፣ ከፒያሳ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ድረስ በቀን ለትራንስፖርት 130 ብር ድረስ አወጣለው። በወር ሲሰላ እስከ 3,900 ብር ማለት ነው፤›› ብላለች።
የወር ደመወዟ ስድስት ሺሕ ብር እንደሆነ የገለጸችው ይችው ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች እንስት፣ በአዲሱ ታሪፍ ምክንያት ከወር ደመወዟ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ለትራንስፖርት ለማውጣት እንደምትገደድ ተናግራለች። ‹‹ከቤተሰብ ጋር ስለምኖር የቤት ኪራይ የለብኝም ቢሆንም ቤተሰብን መረዳት አይደለም ሌሎች ወጪዎቼን መሸፈን አልቻልኩም ተመልሶ ቤተሰብ ላይ ሸክም መሆን ነው፤›› በማለት ምሬቷን ገልጻለች።
በተመሳሳይ አስተያየታቸውን ያጋሩን ተመስገን የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ ‹‹የምኖረው ኮዬ ፈጬ፣ የሥራ ቦታዬ ደግሞ መገናኛ ነው። አንድ ኮሌጅ የምትማር ልጅ አለችኝ። የምትማረው ገርጂ መብራት ኃይል ነው። በቀን ለልጄ ትራንስፖርት እስከ 70 ብር አወጣለሁ፣ እኔም ወደ ሥራ ቦታዬ ደርሼ ለመመለስ በቀን 70 ብር አወጣለሁ፤›› ብለዋል።
በአጠቃላይ ለራሳቸውና ለልጃቸው በቀን 140 ብር የትራንስፖርት ወጪ እንዳለባቸው የገለጹት አቶ ተመስገን፣ የወር ደመወዛቸው 10,000 ብር እንደሆነና ከዚህ ላይም 6,500 ብር ለቤት ኪራይ እንደሚያወጡ ተናግረዋል። አወጣለሁ ሌሎች መጪዋችን መሸፈን አይታሰብም፡፡
የፅዳት ሠራተኛ የሆነችው ባለቤታቸው የምታገኘው ገቢ የተወሰነ ቢያግዛቸውም፣ ‹‹ለልጄ ማሟላት ያለብኝን ሳላሟላ ነው ወደ ትምህርት ቤት የምልካት፣ በየሴሚስተሩ ክፍያ በደረሰ ቁጥር ትልቅ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ምንባው። አሁን ደግሞ ዱብ ዕዳ ወረደብን፣ ከዚህ በኋላ የልጄን የትምህርት ቤት ወጪ ሸፍኜ ማስቀጠል መቻሌ ያሳስበኛል፤›› ሲሉ አዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ በችግር ላይ ሌላ ችግር ይዞባቸው እንደመጣ ያስረዳሉ።
በዚሁ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ ዙሪያ ያነጋገርናት ሌላዋ የአዲስ አበባ ነዋሪ ደግሞ፣ ‹‹ጭማሪም እኮ አይነት አለው። ሁለት ብርና ሦስት ብር ቢሆን እንኳ ይከብዳል ግን ይሁን ብለን ልንቀበለው እንችላለን። የሰሞኑ ጭማሪ ግን ለሰሚም ግራ ነው፣ መንግሥት በአንድ ጊዜ ይህን ያህል ጭማሪ ያደረገው እንዴት አስቦና አስልቶ እንደሆነ ጥያቄ ፈጥሮብኛል፤›› ብላለች።
በተለምዶ ብርጭቆ አካባቢ አዲስ ሠፈር ተብሎ ከሚጠራው መንደር ተነስው ሲግናል አካባቢ ወደሚገኝ የሥራ ቦታቸው በማቅናት ውለው የሚገቡት ሌላው አስተያየት ሰጪ፣ በአዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ መሠረት ወደ ሥራ ቦታቸው ደርሰው ለመመለስ በቀን 100 ብር እንደሚያወጡ ገልጸዋል።
‹‹በአዲሱ ታሪፍ መሠረት በቀን ለትራንስፖርት የማወጣው በወር ሲሰላ ሦስት ሺሕ ብር ይሆናል፣ እኔ በወር የማገኘው ደመወዝ 5,500 ብር ነው። ስለዚህ ደመወዝተኛ ነኝ ማለት አልችልም፣ ትርፉ ድካም ብቻ ነው፤›› ብለዋል።
ሪፖርተር የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አስተያየት ለመሰብሰብ በተለያዩ የከተማዋ ሥፍራዎች በተዘዋወርበት ወቅት ማኅበረሰቡ በተለያየ ሁኔታ ቅሬታውን፣ ብስጭቱን እንዲሁም ምሬቱን ሲገልጽ በግልጽ ተመልክቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎችም፣ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪው የተጋነነ ብቻ ሳይሆን ወቅትና ሁኔታን ያለገናዘበ መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አሚና መሐመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ አሳሳቢ አዝማሚያ ነው። በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ማንኛውም የኢኮኖሚና ተጨማሪ የወጪ ጫና ወደ ከባድ ችግርና ማኅበራዊ አለመረጋጋት ሊያመራ ይችላል፤›› ብለዋል
ሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለመግፋት እየታገለ ባለበት በዚህ ወቅት ይህን መሰል የኅብረተሰቡን ኑሮ ደረጃ ያላገናዘበ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪዎችን ማድረግ ማኅበረሰብን የሚያስደነግጥና ሥጋት ውስጥ የሚጥል ነው።
ማኅበረሰቡ ዘላቂ መፍትሔን ይሻልና በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ የመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል።