እኔ የምለዉ ሰው ከተማና ልማት

አንባቢ

ቀን: October 20, 2024

(ክፍል ሁለት)

በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ

ጸሐፊው ባለፈው ሳምንት በክፍል አንድ ጥቂቶችን ያማከለና ብዙኃኑን ያገለለ መሠረተ ልማት ተቀዳሚ ፍላጎቶቻቸው በማይጣጣሙ የአንድ አገር የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ልዩነት የመፍጠር ዕድል እንዳለው፣ እንዲህ ዓይነቱ ዕድገትና የልማት አካሄድ ከአካታችነቱ ይልቅ አግላይነቱ እንደሚያመዝን፣ በብዙኃኑና በጥቂት ዜጎች መካከል የኑሮ ደረጃ ልዩነትን የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው፣ በእርግጥ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ባለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ እየተስፋፋ የመጣ ጉዳይ መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩ፣ ሆኖም በበርካታ ታዳጊ አገሮች ልምድ አገሮቹ ለነፃ ኢኮኖሚና ለኒዮሊበራል ከበርቴዎች በራቸውን ሲከፍቱ በተለያዩ ምክንያቶች የኑሮ ደረጃ ልዩነቱ እየተባባሰ እንደሚሄድ፣ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶችን ማስቀመጥ እንደሚቻል በማስገንዘብ ሊነሱ የሚችሉ ጥቂት ምክንያቶችን ዘርዝረው ነበር፡፡ ቀጣዩና የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ዛሬ ታዳጊ አገሮች ገበያቸውን ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲከፍቱ የሚወተውቱ ያደጉት አገሮች፣ እነሱ ከማደጋችው በፊት በራቸውን ዘግተው የምርትና ምርታማነት አቅማቸውን ካሳደጉ በኋላ ነው ኢኮኖሚያቸውን መክፈታቸውን ‹‹Bad Samaritan›› በሚል የቻንግ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። በጨቅላ ደረጃ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን (Infant Industries) እንዲሁም የዳበረ አቅም ለሌላቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስና መንግሥታዊ የልማት ተቋማትን ከለላ ሳያደርጉና ተወዳዳሪነታቸውን ሳያረጋግጡ ለኒዮሊበራል ከበርቴዎችና ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶቻቸው የአገርን ኢኮኖሚ መክፈት ከዚህ ቀደም የነበሩ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶችን ይበልጥ ማስፋፋትና ጥቂቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ዕርምጃ ሊሆን እንደሚችል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

የኒዮሊበራል አካሄድ፣ በበርካታ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጉን እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከሥራቸው በማፈናቀልና ከመሬታቸው በማንሳት ለድህነት እንደዳረጋቸው ያሳያሉ። የእነዚህ ከበርቴዎችና ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶቻቸው ተቀዳሚ ዓላማ ትፍርና ውጤታማነት (Profit and Efficiency) በመሆኑ የሚገቡባቸውን አገሮች ሕዝብ የምርቶቻቸው ማራገፊያ፣ ገበያና ጉልበታቸውን በርካሽ ዋጋ ማግኛ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብታቸውን መበዝበዣ ዕድል አድርገው ይወስዳሉ። አካሄዳቸውም ሠራተኛን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን (Labour Displacing Technologies) የሚጠቀሙ ሲሆን፣ በጥቂት የሰው ኃይል በርካታ ሸቀጦችን በማምረትና አገልግሎቶችን በማቅረብ ትርፍ ማጋበስ ነው። ይህ ደግሞ በጥቂቶችና በብዙኃኑ መካከል የኑሮ ደረጃን ያባብሳል።

ለአብነት ያህል ፈርጉሰን የሚባል ተመራማሪ ‹‹Global Shadows›› በሚል መጽሐፉ ማዕድን አውጪ ኩባንያዎች በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያላቸው ልምድ በማንሳት ከዚህ ቀደም የነበሩት ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች ለአካባቢ ጥበቃ የሚጨነቁና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠቅሙ ሥራዎችን የሚሠሩ (Socially Tick የሆኑ) የነበሩ ሲሆን፣ በቅርብ ዓመታት የሚመጡት ግን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ (Socially Thin የሆኑ) እና ተቀዳሚ ዓላማቸው ትርፍን ማጋበስ መሆኑን አሳይቷል። በተመሳሳይ መልኩ በተፈጥሮ ዘይት፣ መሬት፣ እርሻና መሰል ሥራዎች ላይ የሚሰማሩ ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች ዋነኛ ዓላማ የተፈጥሮ ሀብትን መቀራመት፣ ርካሽ የሰው ሀብትን መጠቀምና ትርፍ ማጋበስ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ። በሪል ስቴት ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችም፣ ከነዋሪዎች ይልቅ ለመሬቱ ዋጋ ሊሰጡ ይችላሉ፣ ይህም የካፒታሊዝም ዓይነተኛ መገለጫ ነው። አዲስ አበባ ነባር መንደሮች ውስጥ እየበቀሉ ያሉ የሪል ስቴት ግንባታዎችን ለታዘበ፣ የነባር ነዋሪዎች ዕጣ ፋንታ ምን ይሆን ያሰኛል።

በዚህ ረገድ የኑሮ ደረጃ ልዩነትን ከሚያባብሱ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው የአገሮችን በር ለዓለም አቀፍ ከበርቴዎችና ለነፃ ገበያ መክፈት አንዱ ነው። መንግሥት በቅርብ ዓመታት እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ይህንን የሚያሳዩ ናቸው። ከላይ እንደተመለከተው (በኢኮኖሚው መዋቅርም ሆነ በባለሀብቶች ልማድ ወይም ሌላ ምክንያት) በእኛ አገር ዓውድ ሀብትና ዕድገትን ከላይ ወደታች የማስገር ዕድሉ አነስተኛ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በነባር የፊውዳሊዝም ንቀትና የሶሻሊዝም ድርቅና ላይ እያገጠጠ የመጣ የካፒታሊዝም ስግብግብነት ሲጨመርበት የሀብት ሥርጭቱን ይበልጥ አዳጋች ያደርገዋል። እነዚህ ላይ የተረኝነትና በአጭር የመበልፀግ ስሜቶች ሲጨመሩባቸው ከሀብቱም ሆነ ከልማቱ የሚጠቀሙት ጥቂቶች ናቸው። ይህም በአብዛኛውና በጥቂቶች መካከል የኑሮ ደረጃ ልዩነትን ይፈጥራል። ይህ ዓይነቱ የከፋ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ደግሞ ውሎ ሲያድር ጣጣ ይወልዳል። የኑሮ ደረጃ ልዩነትን በተመለከተ ነጋድረስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር በሚል መጽሐፉ ከመቶ ዓመታት በፊት እንዲህ ብሎ ነበር፡፡

‹‹የሚበላውንና የሚለብሰውንም ያጣ ደሃ የተወለደበትን አገር የሚወድበት ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግሥት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፣ ስለዚሁም መንግሥት የሚጠቀመው የአገሩ ሀብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ሲሰበሰብ አይደለም። ያገሩን ሀብት በመላው ሕዝቡ ሲከፋፈለው ነው እንጂ። የሀብታሞች አኗኗር እና የሠራተኛው ደሃ አኗኗር ዓይነቱ እንበለ መጠን የሚራራቅበት አገረ መንግሥቱ ከጥፋት አፋፍ እንደደረሰ ያስረዳል። የኢትዮጵያንም ሕዝብ ሁኔታ ብንመለከት እንደዚህ ያለ ጥፋት እንዳይደርስ ያስፈራል። በአንድ ፊት ነግደው የሚያድሩ የውጭ አገር ሰዎችና ለሕዝቡ አንዳች ጥቅም ሳይሠሩ ድካሙን እየቀሙ አንዳንድ ሹማምንቶች ደህና ደህና ቤት እየሠሩ የተመቸ ኑሮ ሲኖሩ እናያለን። ባንድ ፊትም የለት ጉርስና ያንድ ዓመት ልብስ እናገኛለን ሲሉ ብዙ ሺሕ ደሃዎች ወባና ችጋር ፈጅቷቸው ከድሬዳዋ አንስቶ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ከምድር ባቡር ጎን ለጎን አልፈው አልፈው ተቀብረዋል።››

እንዲህ ያለው የኑሮ ደረጃ ልዩነት ተመሳሳይ ዕርምጃ በወሰዱ የተለያዩ ታዳጊ አገሮች ውስጥ የመንግሥት መውደቅን ጨምሮ የሕዝቦች መደህየት ዓይነት በርካታ ማኅበራዊ ቀውሶችን ወልዷል። እኔ በቆየሁበትና ተዘዋውሬ ባየሁት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዋነኛው ማኅበራዊ ቀውስ ወንጀል ነው። ስደት (በተለይም ሕገወጥ ስደት) በተለያዩ አገሮች ውስጥ ለተፈጠሩ የኑሮ ደረጃ ልዩነቶች የተወሰደ ግብረ መልስ ነው። ከዚህ ለጥቀን ወንጀልና ስደትን በወፍ በረር እንቃኝ፣

4.1.1. ወንጀል

የማያጣጥሙትን ውበት መናፈቅና የማይኖሩት የሀብት መጎምዠት ያምማል። የማያጣጥሙት ውበት፣ ‹‹የማትበላ ወፍ›› ዓይነት ስሜት ላይ ይጥላል። የማይኖሩት ሀብትም እንደ እግር እሳት እያደር ይፋጃል። የሁለቱ ቅንጅት ሲውል ሲያድር ንዴትና ምሬትን ይፈጥራል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ የተጋነነ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ባለባቸው አገሮች ዝም ብሎ ውበትን ከማድነቅና ከማየት ባለፈ ማኅበራዊ ቀውሶችን ወልዷል። ውበትና ሀብትን እያዩ መከልከል የሰለቻቸው በርካታ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መጎምዠታቸው እያደር ወደ ጥብቅ ፍላጎትና የይገባኛል ጥያቄ አደገ። ጥያቄያቸው ምላሽ ሲያጣ በኃይል ወደ ማግኘት ተቀየረ፣ ማለትም ወንጀልን አማራጭ አድርገው ወሰዱት።

ጥቂት ሰዎች ብቻ የሚንደላቀቁባት ከተማ በነዋሪዎች መካከል መቃቃርን ይወልዳል። ውጤቱ እንደነዋሪው የኋላ ማንነትና አስተዳደግ ወደ ወንጀል ወይም ወደ ልመና ሊቀየር ይችላል። እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ነውጠኛ (Violent) በሆኑ ማኅበረሰቦች ዘንድ የወንጀል መበራከት ዓይነተኛው ግብረ መልስ ነው። በጥቂት ሀብታሞች መካከል የሚኖሩ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን አንደኛውን ሀብቱና ውበቱ ባቅራቢያቸው ባይኖርና ባይጓጉ እንደሚመርጡ ይናገራሉ፣ እያሳዩ መከልከል ግን ሲውል ሲያድር ንዴትና ብስጭትን አላብሷቸው ወደ ወንጀል መርቷቸዋል። ከዚህ አንፃር ደቡብ አፍሪካውያን ወንጀልን ያሞናሙኑታል፣ የሚያበላን የሚያጠጣን፣ የሚያደምቀን የሚያሞቀን ወንጀል ነው ይላሉ። ወንጀል መፈጸምን የተነጠቁትን እንደ ማስመለስና የሚገባቸውን እንደ ማግኘት ሲከፋም ኃላፊነታቸውን እንደመወጣት ይቆጥሩታል። ዝነኛው ደቡብ አፍሪካዊ ኮሜዲያን ትሬቨር ኖአህ ስለዚህ ጉዳይ ‹‹Born A Crime›› በሚል መጽሐፉ ‹‹Crimes Cares›› የሚል ጽንሰ ሐሳብ ያነሳ ሲሆን ሐሳቡ ከላይ የተቀመጠውን ድርጊትና ማኅበራዊ ሁነት የሚያብራራ ነው።

የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ባይወዳደርም እንኳን እኛም መንገዳችን ወደዚያው ይመስላል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በብዙኃኑ ጥቁሮችና በነጮች (ጥቂት ጥቁሮችን ጨምሮ) መካከል ያለ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ሁለቱ መደቦች በአንድ ዘመንና በአንድ ሥፍራ አብረው የሚኖሩ ሳይሆን የታችኞቹ የላይኞቹንና ኑሯቸውን በቴሌቪዥን የሚያዩ ያህል ይሰማል። ተመሳሳይ ነገር በአዲስ አበባ ከተማም በጥቂቱ እየታየ ይመስላል። በቀላል ባቡር፣ በቅጥቅጥ፣ በታክሲ፣ በሃይገር፣ በከተማ አውቶቡስና መሰል የመጓጓዣ ዘዴዎች ነዋሪዎች ተፋፍገው ሲጓዙ በዚያ ትፍግፍግና ጭንቅንቅ ውስጥ ሆነው በግራና በቀኝ ያለውን የኮሪደር ውበት አጮልቀው ሲመለከቱ ሰዎቹ በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ የልማቱ ተጠቃሚዎች ሳይሆኑ ከሌላ ቦታ የመጡና የሌላ ዘመን ልማት በቴሌቪዥን የሚያዩ ይመስላሉ። በእነዚህ የብዙኃን መጓጓዣዎች ውስጥ ተሳፍሬ ስጓዝና ጉዳዩን ስታዘብ ተመሳሳይ ነገር ተሰምቶኛል። በእነዚህ መጓጓዣዎች ውስጥ በሚከፈቱ የቴለቪዥን ተንቀሳቃሽ ምሥሎችና በተጓዦች ኑሮና ገጽታ መካከል ያለው ልዩነትም ከውጭ ካለው ልማት ጋር ተመሳሳይነት አለው።

በኢትዮጵያ ደሃዎችና በሀብታሞች መካከል ያለው የኑሮ ደረጃ ልዩነት ባለፉት ሃያና ከዚያ በላይ ዓመታት እየሰፋ መሄዱን የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል (See the WB Inequality Index)። ኢትዮጵያ የተያያዘችው የልማት አቅጣጫ የኑሮ ደረጃ ልዩነቱን ይበልጥ የሚያሰፋ ዓይነት ነው። ውሎ ሲያድር የኑሮ ደረጃ ልዩነቱ እያገጠጠ ሲሔድ፣ ልማቱን፣ ሀብቱና ውበቱ በተጠቃሚዎች ዘንድ ደስታን በጎምዢዎች ዘንድ ደግሞ ንዴትን ሊያጭር ይችላል። በቅርብ ዓመታት እንኳን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓቱ ውጤት የሆኑ ወንጀሎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እያቆጠቆጡ መሆናቸውን መታዘብ ይቻላል።

የኑሮ ደረጃ ልዩነት የሚፈጥረውን አደጋ ለመከላከልና ሀብትን ለመጠበቅ ጥቂት ጥቅመኞች አጥራምነት ይጠናወታቸዋል። ጥቂቶች ጥቅማቸውን ለማስከበር ወይም ሀብታቸውን ላለማጣት ራሳቸውንም ከተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች (በዋናነትም ከወንጀል) ለመከላከል ጥረት ማድረጋቸው አይቀርም። በደቡብ አፍሪካ የሆነውን ለማሳያነት ያህል፣ በርካታ ነጮች ረዣዥም ግንቦችን ገነቡ። ትልልቅ ውሾችን አረቡ። የኤሌክትሪክ ሽቦ ወጠሩ። ጥበቃ ቀጠሩ። መሣሪያ ታጠቁ። ካሜራ ገጠሙ። የነጮች ብቻ መንደሮችን ሳይቀር መሠረቱ። ደቡብ አፍሪካውያኑ ሀብታሞች እንዲህ ያሉትን የጥንቃቄ ዕርምጃዎች አደርጅተውና ኬላዎች አበጅተው ሲያበቁ፣ ራሳቸውን በ‹‹Maximum Security Prison›› ውስጥ አገኙት። በገዛ ግቢያቸው እስረኛ ሆኑ! ‹‹ወንጀለኞቹ›› ግን አጥሩን ዘለው፣ ኬላውን ጥሰው መሄድ አላስፈለጋቸውም። የናጠጡ ሀብታሞች መኪናቸውን እያሽከረከሩ ከግቢ ሲወጡ፣ ደጃፋቸው ላይ ማጅር-ግንዳቸውን፣ ግንባር-ቦቃቸውን፣ ወገብ-አገዳቸውን ይሏቸው ጀመር። ልጆቻቸውንም ከትምህርት ቤት፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎችና ከመገበያያ ቦታዎች እያደኑ በመያዝ ክፍያ (Ransom) ይጠይቁባቸው ጀመር።

የኑሮ ደረጃ ልዩነት ከሚፈጥራቸው ማኅበራዊ ቀውሶች መካከል የጎዳና ተዳዳሪዎችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልመናንና ወንጀልን አጣምረው የያዙ ለመሆናቸው ደቡብ አፍሪካ ሕያው ምሥክር ናት፣ ሲመቻቸው ይለምናሉ፣ ሲመቻቸው ማጅራት ይመታሉ። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ቀውስ እየተስፋፋ ነው። ይህን በተመለከተ ዶክተር በድሉ ዋቅጂራ የወንጀሉን አንድ ዘለላ መዝዞ ጎዳና ተዳዳሪዎች እንዴት ወደ ወንጀለኝነት እንደሚቀየሩ ሲያብራራ የመስታወት ጥላ በሚል ግጥሙ ውስጥ ይህን ስንኝ ቋጥሯል፡፡

«…ስሚ!

ይህ ወገን ይሉት አሸን፣

ራሱ ዘርቶ ሲሸሸን፤

አያውቀን!

ስንበቅል – ሲያቀጭጨን፤

አያውቀን! ስናብብ – ሲያጠወልገን፤

አያውቀን!

ስናፈራ – ሲመርዘን፤

አያውቀን!

የመስትዋት ጥላ ነን።

ስሚ፣ እማ!

መኖራችንን የሚያውቀው፣ ይህ ወገን ይሉት ነቀዝ

የዘራውን ሲያጭድ ነው፣ በመረዘው ፍሬ ሲመረዝ።»

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተገንና ከለላ የሌላቸው በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወይም ወገኖች (የእኔ ቢጤዎች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ጫኝና አውራጆች፣ ወዘተ) ይህ ነው የሚባል ጥበቃ ወይም ከለላ ስለማይደረግላቸው፣ በዚያው ዘርፍ ውስጥ በተሰማሩ ወገኖቻቸው ወይም በሌሎች አካላት ሊጠቁና ሊበዘበዙ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ብዝበዛና ጥቃት ‹‹የአራዳ ልጆች›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ተመልክቷል። እንዲህ ዓይነቱ ከለላ ማጣትና ያንን ተከትሎ የሚፈጠረው ብዝበዛና ጥቃት በሕገወጥ መንገድ ሰው አገር በገቡ ኢትዮጵያውያን ላይ የተለመደ ነው። ጎዳና ተዳዳሪዎችና ሌሎችም የኢኮኖሚ ሥርዓቱና ማኅበራዊ ቀውሱ የሚፈጥራቸው ወገኖችም በገዛ አገራቸው ለተመሳሳይ ብዝበዛና ጥቃት ይዳረጋሉ። ይህም መሬት ላይ የሚታይ ራሱን የቻለ ማኅበራዊ ቀውስ ነው።

የተጋነነ የኑሮ ደረጃ ልዩነት የሚወልዳቸው ወንጀሎች ለወሮበሎች አጓጊና አትራፊ ስለሚሆኑ በአጭር ካልቀጩት ጦሳቸው የትየለሌ ነው። ወንጀሎቹን ለአጭር ጊዜና ሳይበዙ በፊት በፖሊስና መሰል ተቋማት መከላከል ይቻላል። ልዩነቱ እየሰፋ ሲሔድና ወንጀለኞች ሲበራከቱ (እነሱም እየጣማቸው ስለሚሄድ) ወንጀልን በቋሚነት ለመከላከል ሎጂስቲክስን ጨምሮ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ደንብ አስከባሪዎችና ፖሊሶችም ወንጀሉን በትጋትና በዘላቂነት ሊከላከሉ የሚችሉት ራሳቸው የልማቱና ዕድገቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ነው። አለበለዚያ ወንጀል የሚከላከሉ ሰዎችም ከወንጀለኞች ጋር በመተባበር ከወንጀል በረከት ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ። የወንጀለኞች የገንዘብ አቅም እየዳበረ ሲሄድና ቁጥጥሩ ሲያይል ደግሞ ወንጀለኞች ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከውጭ አገሮች ጭምር በመሳብ ቀውሱን ድንበር ተሻጋሪ ሊያደርጉት ይችላል። የመንግሥት አካላትን በገንዘብ ኃይል በማማለል የወንጀሉን ሰንሰለት እንዲቀላቀሉ ያደረጉ አገሮችም አሉ።

በደቡብ አፍሪካ ከሥራ የተባረሩና ጡረታ የወጡ የቀድሞ ሕግ አስከባሪዎች አንዳንድ ፖሊሶችም ሥራቸውን በፈቃዳቸው እየለቀቁ ያላቸውን ሰንሰለትና መረጃ በመጠቀም የወንጀል ሥራ ላይ ሲሰማሩ ታይተዋል። ወንጀልን ለመከላከል የሚወጡ ሕጎችን ተገን በማድረግ ወንጀለኛ ያልሆነውን ጭምር የሚመዘብሩ ሕግ አስከባሪዎችም ታይተዋል። በኢትዮጵያም ቢሆን ተመሳሳይ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ከንግድ ባንክ ነው የምንደውለው የሚሉ አንዳንድ ሰዎች የደንበኞች ስልክ ቁጥርህ ብቻ ሳይሆን ስምም አላቸው፡፡ ለምን ንግድ ባንክ ብቻ ማጭበርበሪያ ሆነ ወደፊትስ ከሳይበር ሴኪዩሪቲ አንፃር ምን አደጋ ይዞ ይመጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል፡፡ በሌሎችም የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ተቀጣሪዎች ለወሮበሎችና አጋቾች መረጃ (ስምና ስልክ ቁጥርን ጨምሮ ሌሎችንም መረጃዎች) ለወንበዴዎች በማቀበል የወንጀሉ ተዋንያን እየሆኑ ያለ ይመስላል። ይህ ዓይነቱ ድርጊት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተለመደ ነው። አይደለም የባንክ መረጃ ማን ዕቁብ እንደደረሰው ለወረበሎች መረጃ አሳልፈው በመስጠት ከወንጀሉ በረከት የሚካፈሉ ጥቂት ኢትዮጵያውያን አሉ። ይህ ደግሞ የተጋነነ የኑሮ ደረጃ ልዩነት (High Inequality) ከወለደው የአገሩ ባህሪ የተለማመዱት አካሄድ ሲሆን፣ የስደት ሕይወታቸው ያልሰመረላቸው (Failed Migrants) አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የወገኖቻቸውን መረጃ ለወሮበሎች (Gangsters) አሳልፈው በመስጠት ከወንጀሉ በረከት የድርሻቸውን ይቃርማሉ።

የሚያሳዝነው ጉዳይ ለኃጥአን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል እንዲሉ አብዛኛውን ጊዜ የወንጀሉ ገፈት ቀማሽ የሚሆኑት ለወንጀሉ መፈጠር ምክንያት የሆኑት ወይም ከተጋነነው የኑሮ ደረጃ ልዩነት ተጠቃሚ የሆኑት አካላት ሳይሆኑ ከለላ የሌላቸው መደበኛ ነዋሪዎች መሆናቸው ነው። ‹‹ወንጀለኞቹ›› ዋነኞቹን ተጠቃሚዎች በቀላሉ ስለማያገኟቸው አብዛኛው ወንጀል የሚፈጸመው ተገን በሌላቸውና ለውጥንቅጡ እምብዛም አስተዋፅኦ ባላደረጉ መደበኛ ዜጎች ላይ ነው። ደቡብ አፍሪካ በስደት ሄደው ሀብት ያፈሩ ኢትዮጵያውያን (ሱቅ የሚሠሩ ሳይቀር)፣ እንዲህ ዓይነቱ ወንጀል በመበራከቱ፣ ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት ምንም ዓይነት ጥበቃ ወይም ከለላ ስለማይደረግላቸው በተደጋጋሚ ለጥቃት ተዳርገዋል። ራሳቸውን ከወንጀል ለመከላከል፣ እሾህን በእሾህ በሚል ለሌሎች ወሮበሎች (Protection Fee) በመክፈል ተገን መፈለግ ጀምረዋል። ይህ ድርጊታቸው ለጊዜው ከወንጀልና ከዘረፋ ቢታደጋቸውም በዘላቂነት ዘርፈ ብዙ መዘዝ እያመጣባቸው ያለ ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል የወንጀል መበራከት ከሚፈጥራቸው ማኅበራዊ ቀውሶች መካከል ዜጎች በከተማ ውስጥም ሆነ ከከተማ ውጪ በሰላም እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ነው። ከመሸ አዲስ አነባ ከተማ ውስጥ እንደ ልብ መንቀሳቀስ አዳጋች እየሆነ ነው። ወደተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለትምህርት፣ ለሥራ፣ ለንግድና መሰል ተግባራት መንቀሳቀስ ደግሞ ይበልጥ አዳጋች ሆኗል። ይህ ደግሞ ማኅበራዊ መስተጋብሩን ከማላላት ባሻገር ከአንደኛው የአገሪቱ ክፍል ወደሌኛው የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ በማዳከም ኢኮኖሚውንም ይጎዳል። የመንቀሳቀስ ነፃነትን ለይተን ብናይ፣ የወንዲ ማክ የሚባል ዘፋኝ ‹‹ሺ ሰማኒያ›› የሚል ምናባዊ ዘፈን አውጥቶ ነበር። ዘፋኙ ከአዲስ አበባ ተነስቶ አስመራ መሄድ እንደሚፈልግ ይመኝ ነበር። ይህ ምኞቱ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በኢትዮ-ኤርትራ የስምምነንት ወቅት ተሳክቷል። በዘፈኑ ከሚያነሳቸው ጉዳዮች ውስጥ ያለምንም ሐሳብ በአውቶቡስ መሄድ ዋነኛው ሲሆን፣

«በአውቶቢስ ሄጄ የምመለሰው፣

ባኮት ንገሩኝ ጋሼ መቼ ነው?!» ካለ በኋላ በአዝማቹ «አማረኝ» የሚለው አገላለጽ ይስበኛል።

አማረኝ የሚለው ቃል ይገርማል። ዘፋኙ መጓዝ እንደ ምግብ ያምረዋል፣ መሄድ እንደ ውኃ ይጠማዋል፣ መንገድ እንደሰው ይናፍቀዋል። አንድ ሺው ኪሎ ሜትር ቀርቶ ሰማኒያውን ኪሎ ሜትር ያለአንዳች መሳቀቅ በአውቶቡስ ሄደን የምንመለሰው መቼ ነው የሚል ጥያቄም ያጭራል! ዘንድሮ ይህን ዓይነቱን ሰላም እንደ ትዝታ ከማውሳት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስላል!

4.1.2. ልመና

  1.  

በአውቶቡስ መጓዝ ያምራል። ሌሊት በሚኒባስ መሄድ ይናፍቃል። ያለምንም ፍርሐት ጨንቻ፣ ወንጪ ወይም ዝቋላ ደርሶ መመለስ ውል ይላል።

Violent ባልሆኑ ማኅበረሰቦች ዘንድ የኑሮ ደረጃ ልዩነት እየሰፋ ሲሄድ ወንጀል ባይበራከት እንኳን ድህነት ይንሰራፋል። ድህነቱ ልመናን ይወልዳል። ልመናው ደግሞ መልከ ብዙ ነው። ከመንገድ ዳር ልመና እስከ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚደረግ ልመና እየተስፋፋ ይመስላል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል-በንግድና በተማፅኖ መሀል ያለ ልመና (ወጣቶች ነን፣ ተቸግረን ነው፣ ዕርዱን በሚል ዕቃዎችን ቤት ለቤት በማዞር መሸጥ)፣ በጎ አድራጎትንና ማጭበርበርን የቀላቀለ ልመና (ለወላጅ አጥ ሕፃናትና አረጋውያን መርጃ የሚሆን በሚል ትኬቶችን መሸጥ)፣ ቁጣና ተማፅኖን የቀላቀለ ልመና (ትኅትና የሌለው አንዳንዴም ስድብ፣ ዛቻና ማስፈራሪያን የቀላቀለ)፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ኹነቶችን ተገን አድርጎ የሚከናወን ልመና (በሐዘንና በዝክር አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ለበረከትና ለነፍስ ይማር ይደረግ የነበረው ጉብኝት አሁን ሆድ ወደ መሙላት እየተቀየረ ይመስላል)፣ ወዘተ።

ከዚህ ቀደም የተለመደው ትወናን የቀላቀለ የማስመሰል ዓይነት ለመናም ተጠናክሮ የቀጠለ ይመስላል። በየከተማው ጥግና በየጉራንጉሩ የእኔ ቢጤዎችንና የጎዳና ተዳዳሪዎችን መስፋፋት ሌላኛው የልመና ዓይነት ሲሆን፣ የኑሮ ደረጃ ልዩነቱ (Inequality) እየተስፋፋ የሚሄድ ከሆነ ይኸው ማኅበራዊ ቀውስ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በኢመደበኛ ኢኮኖሚ የታችኛው ደረጃ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ወትሮም ኑሯቸው በልመናና በሥራ መካከል የሚንዠዋዠው ነው። ሚዛን አስቀምጠው የሚሠሩም የሚለምኑም፣ ማስቲካ፣ ሶፍትና ሌሎች ዕቃዎችን እየሸጡ የሚለምኑ ልጆችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የሰዎች እንቅስቃሴ ሲቀንስ እንዲሁም በኢመደበኛው ዘርፍ የተሰማሩ ወገኖች ለልማት ሲነሱና በአቅራቢያው የሚገኙ ነዋሪዎች ከነባር መንደሮች ሲፈናቀሉ፣ በታችኛው የኢመደበኛ ኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩ እነዚህ ሰዎች ወደ ልመና መዞራቸው እሙን ይመስላል። በኮሪደሩ አቅራቢያ ባሉ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው ፈራተባ እያሉ የሚለምኑ ጀማሪ ጎልማሳዎችን፣ እናቶችንና አዛውንቶችን (አዳዲስ ለማኞችን) ማየት እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው። ‹‹ዳቦ ግዙልኝ›› የቆየ ልመና ሲሆን እየተስፋፋ የመሄድ አዝማሚያ አለው።

በሌላ በኩል በውጭ አገር ያሉ ወዳጅ ዘመዶችን በሰበብ አስባቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ዕርዳታ መጠየቅ እየተስፋፋ መሄዱን መታዘብ ይቻላል። በውጭ አገሮች የሚገኙ አንዳንድ ወገኖች ከአገር ቤት የሚመጣ ተማፅኖን ለመመለስ፣ ለሐዋላ እያሉ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት መጀመራቸውን ይናገራሉ። በዚህ ረገድ ሱማሌያውያን ላይ የተሠራ ‹‹Early Morning Call›› የሚል ጥናት በአገር ቤት በችግር ውስጥ ይገኙ የነበሩ ሶማሊያውያን፣ ውጭ አገር ከሚገኙ ወገኖቻቸው ገንዘብ እንዲላክላቸው የማያደርጉት ዓይነት የፈጠራ ሕመምና ችግር እንዳልነበረ ያሳያል – የመጽዋቾቹን ልብ ለማራራት። መጽዋቾቹን በስልክ ለማግኘትም በጠዋት (ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት) የመደወል ልምድ አዳብረዋል። የኑሮ መክበድን ተከትሎ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችም ላይ ልዩ ልዩ የልመና ዓይነቶች እየተስፋፉ ነው።

ይህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ቀውስ እየተስፋፋ ሲሄድ፣ ድሆች ሲበራከቱና ለማኞች ሲበዙ የሚያዩ ባለሀብቶችም ሆኑ መደበኛ ነዋሪዎች ጤነኛ ህሊና እስካላቸው ደስተኛ አይሆኑም። ይህ ዓይነቱ ማኅበራዊ ቀውስ እንደ ወንበዴዎች ማጅራትን ባይመታም፣ ከማጅራት መቺ ሴንጢ የተባ ሾተል በሰው ኅሊና ላይ ይሰነቅራል። ደቡብ አፍሪካ ላይ የላይኛውና የታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚያገናኙ መድረኮች የትራፊክ መብራት አንዱ ነው። መኪኖቹን መብራት ሲያስቆማቸው ድሆቹ በቃል ቀይም በጽሑፍ (Placard) ተማፅኗቸውን ያቀርባሉ። የናጠጡ ሀብታሞች ውልውል መኪናቸውን በጥቁር ቀለም ለብጠው የጎዳና ተዳዳሪዎች (ለማኞችና ማጅራት መቺዎች) እንዳልተፈጠሩ ይቆጥሯቸዋል። አንዳንዶቹም ክሬዲት ወይም ዴቢት ካርዳቸውን እያሳዩ ምንም ማረግ አልችልም በሚል ያላግጡባቸዋል።

ጥቂቶች ተመችቷቸው ቢኖሩም ሲወጡ ሲገቡ ወይም በተንጣለለው አስፋልት ውልውል መኪናቸውን ሲያሽከረክሩ በሰፊው ጎዳና በእግራቸው ሲመላለሱ አደጋ ባይደርስባቸው እንኳን የድህነቱን ጥልቀትና የልመናውን ስፋት በማየት ብቻ ህሊናቸው የሚወቅሳቸው አይጠፉም። ይህ ደግሞ ማኅበራዊ ሕይወታቸው ጠንካራ የሆነ የአኗኗ ዘይቤ ባላቸው እንደ እኛ ባሉ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተለመደ ነው። በእርግጥ በእኛም አገር ህሊናቸው የተደፈነና ልባቸው የደነደነ ምንም የማይሰማቸው ወገኖች ይኖራሉ፣ ወደፊትም ሊፈጠሩ ይችላሉ። እነዚህን በተመለከተ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሌላው ሁሉ ደህይቶ፣ ለብቻ ማደግና መበልፀግ ሊፈጥር የሚችለውን የህሊና ቁስል በአንድ ግጥማቸው እንዲህ አስቀምጠውታል፡፡

«ምን አለብኝ ብሎ፣ ማን አለብኝ ብሎ፣

የማይቆጠብ ሰው፣

ራሱን አታሎ፣ ሰውንም አታሎ፣

የውሸት የከበረው፣

የነፍሱን ኡኡታ የህሊናውን ድምፅ አፍኖ ሸንግሎ፣

ዕንቅልፍ የሚወስደው፣

ዓይንና ጆሮውን ከአእምሮው ገንጥሎ፣

ቅሬታ እማይገባው፣

ሌሎች ሲበሳጩ፣ ሌሎች ሲሸበሩ፣ ብዙ ነገር ጎድሎ፣

ሞልቶለት ደስ ያለው፣

ከዙሪያው መበስበስ፣ ከዙሪያው መሻገት እሱ ተገንጥሎ፣

የማይቆረቁረው፣

የሰው አውሬ እሱ ነው።»

4.1.3. ስደት

ከኑሮ ደረጃ ልዩነትና ከድህነት መስፋፋትጋር በተያያዘ ከሚፈጠሩ ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ አንዱ ስደት ነው። ይህም በአገር ውስጥ ወይም ከአገር ውጭ ሊከወን ይችላል። ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች በሚያደርጉት የልማት አካሄድ በአገር ወይም በከተማ ውስጥ መፈናቀልና ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ሊኖር ይችላል። የግል አልሚ ባለሀብቶችን ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪና ትልልቅ ድርጅቶች፣ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ መሬት የግል ባልሆነባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወገኖች፣ በመንግሥት በሚደረግ ልማት ምክንያት ወይም በገንዘብ ኃይል ቤትና ንብረታቸውን እየገዙ ወደ ከተሞች ጥግና ሌሎች ቦታዎች ሊሰዷቸው (Gentrification) ይችላሉ። በገጠርም የእርሻ መሬታቸውና የግጦሽ ቦታቸው እንዲሁም ለመጠጥና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቀሙባቸው ውኃቸው ለሰፋፊ የእርሻ ልማቶች (Large-Scale Commercial Farming) በየተሰጠባቸው አርሶ አደሮች ከገጠር ወደ ከተማ ተሰድደዋል።

በሌላ በኩል የኑሮ ደረጃ ልዩነት መባባስና የኑሮ መናር ከሚፈጥራቸው ግብረ መልሶች ውስጥ አንዱ ከአገር ውጭ የሚደረግ ስደት ነው። ከአገር ውጭ የሚደረግ ስደት በሁለት መልኩ ሊከሰት ይችላል። አንድም መሠረታዊ የኑሮ ፍላጎቶችን (ሥራ፣ ምግብ፣ መጠለያ፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት፣ ወዘተ) በአገር ውስጥ በማጣት። ሌላም በአንፃራዊ ድህነት (Relative Deprivation) ምክንያት፣ ማለትም ዕድገቱ ለብዙዎች ቢዳረስና የበርካቶች ኑሮ ቢለወጥ እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ የኑሮ ልዩነት ስላለ፣ ከሌሎች አገሮች የኑሮ ደረጃ አንፃር ኑሯቸው ላይጥማቸው ይችላል። ከዚህ በላይ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ጋር በተያያዘም በአገር ተስፋ በመቁረጥ ከአገር ለመሰደድ ሻንጣቸውን የሚያዘጋጁም አሉ። አዝማሪው፣

‹‹የገበታሽ ‘ራት ዓይነትም አልበዛው

ያው ተስፋሽ ነው እንጂ ፊቴን የሚያወዛው›› እንዳለው ተስፋ ያጣ ሰው በአገሩ ለመኖር ወኔ ያጣል። ልቡ ለስደት ይነሳል።

ሆኖም ለመሰደድ የሚችለው ጥቂት ሰው ነው። በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ለመሰደድ ገንዘብና ሌሎች አቅሞች (Capitals) ያስፈልጋሉ። በሕጋዊ መንገድ ለመሰደድ በርካታ ሰነዶችና መስፈርቶች ያስፈልጋሉ። ሰነዶችን ለማግኘት ጊዜና ገንዘብ ያስፈልጋል። ሒደቶቹ በርካታ ወጪዎችን ይጠይቃሉ። ፓስፖርት ለማውጣት ወይም ለማሳደስ አበሳ ነው። ቪዛ ለማግኘት መከራ ነው። ባህር ማዶ ከደረሱም በኋላ መቋቋሚያ ገንዘብ ወይም የሚቀበል ሁነኛ ሰው ማግኘቱም እንደዛው። በሌላ በኩል ከደኅንነት፣ ሽብርና ከአገሮች ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ድንበሮች እየጠበቁና ቁጥጥሮችም እየበረቱ ስለሄዱ በሕገወጥ መንገድ ለመሰደድ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ ሆኗል። በርካታ አደጋዎችም በመንገድ ላይ ያጋጥማሉ። እነዚህን ጋሬጣዎች ማለፍ የሚችለው ገንዘብ ያለው እንዲሁም አካሉ የጠነከረና አደጋ የሚቋቋም የኅብረተሰብ ክፍል ነው። ቤተሰብ የመሠረቱ፣ ልጆች ያሏቸው፣ ወይም አረጋውያንና ልጆች መንገዱን አይችሉትም። ዋጋውም ይጨምርባቸዋል።

ይህም ሁሉ ሆኖ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደትን እንደ አማራጭ እየወሰዱት ነው። የርስ በርስ ጦርነት፣ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ አጥነት፣ የተሻለ ኑሮና ነፃነት ፍለጋ ወዘተ በርካታ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ጥለው እንዲሄዱ እያደረጋቸው ነው። በሕጋዊ መንገድ ለመሰደድ ያለው በር ጠባብ በመሆኑ፣ በሕገወጥ መንገድ የመሰደዱ ጉዳይ ቀጣይነት ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ሁለት ዓበይት ምክንያቶችን ማስቀመጥ ይቻላል። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛትና የዲሞግራፊ ለውጥ ምክንያት (ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ) በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ሥራ ገበያው በየዓመቱ ይቀላቀላሉ። ሆኖም የአገሪቱ ሥራ የመፍጠር አቅም ከሥራ ፈላጊውና ከሰው ኃይል ብዛት ጋር አይመጣጠንም። በሌላ በኩል በተያዘው ዓይነት ዕድገትና የልማት አካሄድ የኑሮ ደረጃ ልዩነት የመጨመር እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ አያሳይም። በእርግጥ የኑሮ ደረጃ ልዩነት በዓለም አቀፍ ደረጃም እየተስፋፋ ነው (የዓለም ባንክ መረጃን ተመልከት)። ይህም በርካቶችን በአገር ተስፋ ለመቁረጥና አንፃራዊ ድህነት ውስጥ ለመውደቅ ይዳርጋል።

በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ስደት አገርን ሊጎዳ ይችላል። በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ ስደት ዜጎችን ለብዝበዛና ለጥቃት ከመዳረጉ በተጨማሪ የአገርን ገጽታ ያበላሻል። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሕገወጥ መንገድ የሚሰደዱባቸውን ሌሎች መስመሮች ወደ ጎን አድርገን ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ስደት ብንመለከት፣ በዚህ መስመር ውስጥ በሚገኙ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ዘንድ የኢትዮጵያ ስም እየጠለሸ፣ ገጽታዋ እየተበላሸ ነው። በእነዚህ መዳረሻ አገሮች ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎችም ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ማጠናከርና መሰል የዲፕሎማቲክ ሥራ ከማከናወን ይልቅ ብዙ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን የሚያውሉት ሕገወጥ ስደተኞችን ለማስፈታትና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመፈጸም ነው። በደቡብ አፍሪካም ያለው ተመሳሳይ ነው።

በሌላ ጎኑ በሕጋዊ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደተለያዩ ያደጉ አገሮች የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን አብዛኛውን ጊዜ አንጋፋ የሆኑና ለተቋማት መጠናከርና ለአገር መቆም ዓይነተኛ ሚና ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው። የእነዚህ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መሰደድ ለተሰዳጆቹ ጠቃሚ ቢሆንም አገርን ይጎዳል፣ በዋናነትም ተቋማትን በማዳከም። ከዚህ አንፃር ያደጉት አገሮች ብሩህ አዕምሮና ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን የታዳጊ አገሮች ዕንቁ ባለሙያዎችን መርጠው የመውሰድ ከፍተኛ ልምድ አላቸው።

  1. ኢመደበኛ ኢኮኖሚና የከተማ ማንነት

ከዚህ በላይ እንዲሁም በቀጣይ ክፍሎች ለመጠቆም እንደተሞከረው መንግሥት ለዕድገትና ለውጥ አስፈላጊ በሆኑ የኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ተቋማት መስፋፋትና በግብርና መሠረት ልማቶች ግንባታ ላይ ለማተኮር እንዲሁም ሰላምን ማጽናትና ፍትሕን ማስፈን በመሳሰሉ የሥርዓት ማስፈን ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ብዙ ገንዘብ በከተማ ኮሪደርና የአረንጓዴ ልማት (Green Legacy) ላይ ሲያውል ይታያል። ልማቱ ለከተማ ውበት ጥሩ ቢሆንም፣ ዘላቂ ልማትን ከማምጣት አንፃር ከዚህ በላይ የተመለከቱ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚደረገውን ትኩረት፣ አቅምና ገንዘብ ይሻማል። ከኮሪደሩ ልማት ጋር በተያያዘ የሚፈናቀሉ ዜጎችና የሚሳተፉባቸውን የምጣኔ ሀብት ዘርፎችም (በዋናነትም ኢመደበኛ ኢኮኖሚ) ይገዳደራል። በተለያዩ ምዕራፎች ወደተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚስፋፋ ከሆነ ደግሞ የከተማ ማንነትን ይቀይራል።

ኢመደበኛው ኢኮኖሚ ከውጭ ሆነው ሲመለከቱት የወንጀለኞች መጠራቀሚያና የአመፀኞች መናኸሪያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በዚህ ዕይታ ዘርፉ ዝብርቅርቅ፣ ቆሻሻና ለዓይን የሚስብ ላይሆንም ይችላል። በዚህ ምክንያት ዘርፉን በልማት ፕሮግራሞች ውስጥ አለማካተትና ሲልም ማስወገድ ተመራጭ አካሄድ የሚያደርጉ መንግሥታት አሉ። ሆኖም ብልጭልጩ ሁሉ ወርቅ እንደማይሆነው ሁሉ ዝብርቅርቁም ሁሉ ቆርቆሮ አይደለም። በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚከናወኑ ግብይቶችን በርቀትና ከውጪ ሆኖ ለሚመለከታቸው ዝብርቅርቅና አስቀያሚ መስለው ቢታዩም፣ ከውስጥ ሆነው ለሚመለከቷቸውና በግብይቱ ለሚሳተፉ ደግሞ የተለየ ትርጉም አላቸው። እነዚህ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለተሳታፊዎች የኑሮ መሠረትና የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር መንፈሳዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ማኅበራዊ ዋጋ አላቸው።

አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የሥራ-አጥነት እና የኑሮ ውድነት መስፋፋት አንፃር ኢመደበኛ ኢኮኖሚ ባደጉ አገሮች ጭምር አስፈላጊነቱ እየተለየ መጥቷል። በዚህ መሠረት አሁን ያለው ተመራጭ አካሄድ ኢመደበኛውንና መደበኛውን ኢኮኖሚ መሳ ለመሳ በማስኬድ ከተሞችን ኢኖቬቲቭ በሆነ መልኩ አካታችና ለነዋሪዎች የሚበጁ ማድረግ ነው። ሰማይጠቀስ ሕንፃና ሰፊ አስፋልት የሚበዛባቸው ከተሞች የቅኝ ግዛት ከተሞች (Colonial Cities) እስከመባል ደርሰዋል። ሰፋፊ መንገዶችና ትልልቅ ፓርኮች እያሏቸው የሰው እንቅስቃሴ የማይታይባቸውን ከተሞች ደግሞ ‹‹Dead Cities›› እስከ መባል ደርሰዋል። ትልልቅና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶችም ያለድሆችና ነባር ነዋሪዎች ውጤታማ ሥራ ሊሠሩ አይችሉም። ነባር መንደሮች በልማት ምክንያት የተነሱባቸው አካባቢዎች የሰውና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው ይታያሉ። ፒያሳ አካባቢ ያሉ የንግድ ቤቶች ጭር ብለው፣ ከአራት ኪሎ ወደ ቀበና መንገድ የሚገኙትም ተቀዛቅዘው ማየት እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እያደጉ ባሉ አገሮች ውስጥ ደግሞ የኢመደበኛ ኢኮኖሚው ሚና ከፍተኛ ነው። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ይዘት ብንመለከት ግብርና እና የአገልግሎት ዘርፉ (Service Sector) ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አላቸው። ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ ገና ጨቅላ ደረጃ (ከዓመታት በፊት ወደ አሥራ ሁለት በመቶ አካባቢ ነበር) ላይ ናቸው። በእርግጥ የአገልግሎት ዘርፉ ለምጣኔ ሀብት ያለው አስተዋፅኦ (ከዓመታት በፊት ወደ አርባ ሦስት በመቶ አካባቢ ነበር) ከግብርናው (ከዓመታት በፊት ወደ አርባ አምስት በመቶ አካባቢ ነበር) ዘርፍ ጋር መቀራረቡ ያደጉ አገሮች ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንፀባረቅ እውነታ ነው። ነገር ግን ካደጉት አገሮች በተቃራኒ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገሮች ውስጥ ከአገልግሎት ዘርፉ (Service Sector) ውስጥ አብዛኛውን ቦታ የሚይዘው ባንክና ኢንሹራንስ ጨምሮ መደበኛው የአገልግሎት ዘርፍ (Formal Sector) ሳይሆን በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚከናወኑ ጥቃቅንና አነስተኛ ንግድና መሰል አገልግሎቶች (Informal Businesses) ናቸው። የሥራ አጥነት ችግር ባለባቸውና የሕዝብ ብዛታቸው እየጨመረ በሚሄዱ አነሥተኛ ኢኮኖሚ ባላቸው አገሮች ውስጥ ኢመደበኛ ኢኮኖሚን ከልማትና ዕቅድ ውስጥ ማግለል ወይም በልማት ሥራዎች ውስጥ በበቂ ሁኔታ አለማካተት አዋጪ አይሆንም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ከተሞች ውስጥ ለኢመደበኛ ኢኮኖሚ ትኩረት እንዲሰጥ የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የሚከተሉት ዋነኞቹ ናቸው፡፡

ስለሆነም ከገጠር ወደ ከተማ በገፍ የሚጓዙ ሰዎችን ፍላጎት የሚያስተናግዱ ከተሞችን (ማለትም የኢንዱስትሪ፣ የማኑፋክቸሪንግና የመደበኛ አገልግሎት የኢኮኖሚ ዘርፎችን የያዙ ከተሞችን) በዘላቂነት መሥራት አስፈላጊ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ጊዜ ስለሚጠይቅ ወደ ከተማ የሚገቡ ብዙ ዜጎች ሥራ የሚያገኙትና ኑሮ የሚመሠርቱት በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ ነው። ይህንን ዘርፍ የዘነጋ የልማት አካሄድ ከተሞች ለጥቂቶ ብቻ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ በዜጎች መካከል የኑሮ ደረጃ ልዩነትን ማስፋት ይሆናል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለውጭ ባለሀብቶችና ለዓለም አቀፍ ከበርቴዎች የመክፈት አዝማሚያ እያሳየ በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ቀውስ ቢፈጠር ኢመደበኛ ኢኮኖሚው ለበርካቶች ጥላ ከለላ ስለሚሆን አስፈላጊውን ትኩረት መስጠት ይገባል። የተለያዩ ጥናቶች የሚያሳዩትም ሰዎች ኢመደበኛውን ኢኮኖሚ የሚቀላቀሉት በምርጫቸው ሳይሆን በመደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ያለው የሥራ ዕድል ጠባብ በመሆኑ ነው። በእርግጥ ትርፋማናቱን አይተው በፍላጎታቸው የሚቀላቀሉም አሉ።.

  1. ከቱሪዝም አንፃርም ቢሆን ያደጉ አገሮች ከተማዎችና የሚያቀርቧቸው አገልግሎቶች እምብዛም ተፈላጊ አይደሉም። የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ወይም ተመሳሳይ ታዳጊ አገሮች የሚመጡት እነሱ የሌላቸውን መስህብ ፍለጋ ነው። ብዙዎቹ ጎብኚዎች አስፋልቱም፣ ፓርኩም፣ ብልጭልጩም፣ ተወዛዋዡም ውኃ በገፍ ስላላቸው እንዲህ ያሉ ከተሞችና መሠረተ ልማቶች አብዛኞቹን ብዙም የሚስቡ አይሆኑም።
  2. ከጤና አንፃር በሱፐርማርኬትና መሰል የግብይት ቦታዎች ከሚገዙ የታሸጉ ምግቦች ይልቅ እንደጉልት፣ የሰንበት ገበያና መሰል የገበያ ቦታዎች ትኩስ (ፍሬሽ) እና ጤናማ የምግብ ግብዓትን ያቀርባሉ። ይህ ማለት ሱፐርማርኬቶች አይስፋፉ፣ ሞሎች አይገንቡ ማለት አይደለም። ይገንቡ ግን የኢመደበኛ ኢኮኖሚ ዘርፎችን በማዘመን (ጉልትና ባህላዊ የገበያ አሠራሮችን) በልማቱ ውስጥ በማካተት አብሮ ማስኬድ ይበልጥ አዋጪ ይሆናል።

ሆኖም በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚሰማሩ ተዋንያን፣ የሥራ ቦታቸው ወይም የግብይት ሥርዓታቸው ትክክል ነው ማለት አይደለም። በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለተመለከተ በኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴዎች የንጽሕና ጉድለት፣ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ብልሹነት፣ የቦታ ጥበትና የአሠራር ግድፈት እንዳለባቸው ለመረዳት ይችላል። በመሆኑም እነዚህ ሥፍራዎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረተ-ልማት ማሟላት እንዲሁም ከወንጀል፣ ከንጽሕና አጠባበቅና ቆሻሻ አወጋገድ፣ ከሕገወጥነትና ከመሠረተ ልማት አያያዝና አጠቃቀም አንፃር ያሉባቸውን ጉድለቶች አሟልቶ በልማት ፕሮግራምና ዕቅድ ውስጥ ማካተት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። የኢመደበኛ ኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሠረሮችን ቅጣትና ሽልማትን ባቀናጀ መልኩ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከተሞችን አካታች፣ ዘላቂ ሕያውና ሰዋዊ ማድረግ ይቻላል።

በምሳሌ ለማስረዳት ኬፕታውን አፍሪካ ውስጥ ካሉ ከተሞች በውበትም ሆነ በመሠረተ ልማት አቅርቦት ወይም በሌሎች የከተሜነት መለኪያዎች ግንባር ቀደም ናት። ሆኖም በከተማዋ ዙሪያና በውስጧ በርካታ የድሃ መንደሮች አሉ፣ ‹‹Shack›› ወይም ‹‹Township›› ይሏቸዋል። ገሚሱ ሕጋዊ፣ ገሚሱ ሕገወጥ ናቸው። በብልጭልጭና ረዣዥም ሕንፃዎች መካከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙና የየራሳቸው የኑሮ ዘይቤ ያላቸውን የከተማዋን ነዋሪዎች ያማከሉ ጥቃቅንና አነሥተኛ የንግድ ሥፍራዎች ይገኛሉ። እነዚህ ሥፍራዎች ከመደበኛው ኢኮኖሚ ጋር ተመጋግበው ለሀገሬውና በርካታ ስደተኞች የሥራ ዕድልና የኑሮ መሠረት ሆነዋል። ከርቀት ሲታዩ ዝብርቅርቅ ቢመስሉም ሲጠጓቸው የራሳቸው ሕይወትና ቀለም አላቸው። የቱሪስት መስህብም ናቸው። የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ጫና ተከትሎ የቤት ኪራይ መክፈል የተሳናቸው ደቡብ አፍሪካውያን ክፍት ቦታ ፈልገው ከእንጨት፣ ቆርቆሮና ሌሎችም ግብዓቶች ዳስ ጥለው፣ መንደር መሥርተው ይኖራሉ። ሌሎች ደግሞ በከተማዋ የመንገድ ዳር ፕላስቲክ ወጥረው ያድራሉ። የከተማው አሥተዳደር ሕገወጦቹን በቻለው አቅም ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ቤቶችን (Low-Cost Housing) እየሠራ ያሰፍራል እንጂ ቤታቸውን አያፈርስም። በሕገወጥ መንገድ ደቡብ አፍሪካ የገቡ ስደተኞች የመሠረቷቸው የመኖሪያ መንደሮች ጭምር እንዳሉ አሉ። መብራትና ውኃ እንዲሁም ተንቀሳቃሽ መፀዳጃ ቤት ያስገባላቸው መንደሮችም ይገኛሉ። በሌላ አነጋገር ኬፕታውን በርካታ የውበት መገለጫ ያላት ሲሆን አካታችነቷ (Inclusiveness) ዋነኛው ነው። ብዝኃነቷም መለያዋ ይመስላል፣ በዚህ ረገድ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የመጡ ስደተኞች ለከተማ ውበት፣ ሙቀትና ድምቀት የሚሆኑ የሥነ-ሥዕል፣ የመንገድ ዳር ሙዚቃ፣ የመጻሕፍት ቤቶች፣ የምግብ ቤቶች፣ የቅርፃ ቅርፃና የባህል ዕቃዎች በማቅረብ እንዲሁም የጥበብ መንደሮችን በመመሥረት ለኬፕታውን ተጨማሪ ጌጥ፣ ለዜጎችም ምቹ ሆነዋል። እነዚህም የቱሪስት መስህብና ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባሻገር ለከተማዋ ማንነት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ነው። የኮሪደር ልማቱም እንዲህ ያለውን አካሄድ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአዲስ አበባን ወይም ሌሎች ከተሞችን ማንነትና የነዋሪዎቹን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የልማት ፕሮግራም ቢነደፍ መልካም ነው። የአገሪቱን ታሪክ፣ ሥነ ልቡና፣ ባህል፣ የዕድገት ደረጃ፣ አየር ንብረት፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ወዘተ ያጣመሩና ብዝኃነት ያላቸው ከተሞች ነዋሪውን ያሳትፋሉ፣ ጎብኚዎችንም ይበልጥ ይስባሉ። ልዩ ልዩ ባህሎችን የሚወክሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ አልባሳት፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ አሮጌ መጻሕፍት ቤቶችን፣ ሙዚየሞችን፣ ልዩ ልዩ የሥነ-ጥበብ ዘርፎርችን፣ ወዘተ ያካተቱ ሥፍራዎች (Business And Public Spaces) የነዋሪውን አቅም ባገናዘበ መልኩ ኢኖቬቲቭ በሆነ መንገድ በልማቱ ውስጥ ቢካተቱ ይበልጥ አዋጪ ይሆናል።

  1. ማጠቃለያ

መነሻው ላይ እንደተመለከተው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በተነሣ ጉዳይ ዙሪያ አጠቃላይ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ወይም በጥልቅ መረጃ የተደገፉ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለመስጠት አይደለም። ካየሁት፣ ከሰማሁትና በጥቂቱ ካጠናሁት በመነሣት አንዳንድ ነጥቦችን ለመሰንዘር ነው። ይህም በእኔ የዕይታ አድማስ ልክ የተወሰነ ነው። ሌሎች ወገኖች በተመሳሳይ መልኩ ዕይታቸውን ቢያካፍሉ መልካም ይመስለኛል።

ከዚህ በላይ ግን ጉዳዩ ጥልቅና ውስብስብ በመሆኑ በተቋማት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት ቢጠና መልካም ነው። የኮሪደር ዓይነት የልማት ፕሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያ ተጽዕኗቸውን የሚያይ ጥናት (Social And Economic Impact Assessment) ማድረግ የተለመደ ነው። ይህ ዓይነቱ ጥናት ይደረግ አይደረግ መረጃው የለኝም። ካልተደረገ ግን አንዳንድ በጎ ዓላማ ያነገቡ ፕሮጀክቶች ያልታሰቡ (Unintended) ወይም ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ (Beyond Control) ውስብስብ ውጤቶች (አዎንታዊም አሉታዊም) ሊኖሯቸው ስለሚችል የኮሪደር ልማቱን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ጥናት ቢደረግ ባይ ነኝ። በተለይም ጉዳዩ ወደ ክልሎች እየወረደና በተለያዩ ምዕራፎች እየተከናወነ ስለሚገኝ፣ ጥናቱ ያ ከመሆኑ በፊት ቢደረግና ትሩፋቶቹና ጥፋቶቹ ታውቀው እንዲሽሻል ቢሆን የሚበጅ ይመስለኛል። በዚህ አንፃር ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመግሥት ተቋማት (ለምሳሌ EDRI)፣ ዩኒቨርሲቲዎች (ለምሳሌ የሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች የማስተርስና የፒኤችዲ ተማሪዎቻቸው ጉዳዩን እንዲያጠኑት ቢያደርጉ)፣ የሙያ ማኅበራት (ለምሳሌ የማኅበራዊ ጥናት መድረክና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ወዘተ) እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት ጥናት ቢያደርጉበት መልካም ነው። ከዚህ በመለስ በጥናት ሊዳብሩ የሚችሉ ይበጃሉ የምላቸውን አንድ ሁለት ነጥቦች ላስቀምጥ፣

አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ በኢመደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ የተሰማራ እንደመሆኑ መጠን በቀጣይ ምዕራፎች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማቶች ኢመደበኛ ኢኮኖሚውን (Informal Economy) ታሳቢ ያደረጉ መሠረተ-ልማቶችን በማካተት ልማቱን ሕያው፣ ዘላቂና ሰዋዊ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል። ለአብነት ያህል፣ በብዙ የኢመደበኛ ኢኮኖሚና የሰንበት ገበያዎች አካባቢ ተዘዋውሬ እንደተመለከትኩት፣ በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ የሚሸጡት ምርቶች ብዙዎቹ የግብርና ውጤቶች ወይም ከውጭ አገሮች የገቡ ርካሽ ሽቀጦች ናቸው። ከአጭር ጊዜ አኳያ በባህላዊ ገበያዎች (ሰኞ ገበያ፣ ቅዳሜ ገበያ)፣ ኢመደበኛ ኢኮኖሚ ውስጥ እና የሰንበት ገበያዎች (Sunday Markets) ውስጥ የሚሸጡ ምርቶችን ዓይነት እንዲሁም ወቅቶችን (ክረምትና በጋን) ታሳቢ ያደረጉ መሠረተ ልማቶችን በቀጣይ የኮሪደር ልማት ምዕራፎች ውስጥ በማካተት (Integrate በማድረግ) የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል። ያለቁት የኮሪደሩ ክፍሎችም እነዚህን መሠረተ-ልማቶች መልሶ ለማካተት (Reintegrate ለማድረግ) የሚያስችል ቦታዎች አሏቸው። ከረዥም ጊዜ አኳያ ከላይ በተመለከቱት ገበያዎች ውስጥ የሚሸጡ ርካሽ የውጭ አገሮች ምርቶችን በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ማምረት የሚያስችል አቅጣጫ በመቀየስ ግብርናና ኢንዱስትሪ ላይ በማተኮር ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚቻል ይመስለኛል። በዚህ በኩል ከውጭ አገሮች የሚገቡ ርካሽ ምርቶችን የሚሸጡ የአገራችን ወጣቶች፣ ምርቶቹን የሚያምርቱት እኩዮቻቸው ወይም ታናናሾቻቸው መሆናቸውን ልብ ይሏል።

መንግሥት የኮሪደር ልማቱን ለማከናወን የሄደበትን አስደናቂ ብቃትና አቅም ለነዋሪዎች የሚሆኑ አነስተኛ ወጪ ያላቸውን መኖሪያ ቤቶችን (Low-Cost Housing) በመገንባት እንዲሁም የገበያ ቦታዎችን ጨምሮ የነዋሪውን አቅም፣ ማንነትና ታሪክን ያገናዘቡ መሠረተ-ልማቶችን በኮሪደሩ ውስጥ በማካተት በቀጣይ ምዕራፎች ልማቱን ቢያከናውን የተሻለ ይሆናል።

ኢትዮጵያ በሯን ለዓለም አቀፍ ከበርቴዎችና ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች ከከፈተችና ካፒታሊዝም አፍጥጦና አግጥጦ ከመጣ ዘንድ የአገራችን ባለሀብቶች ‹‹ፋውንዴሽን›› በመመሥረት ያካበቱትን ሀብት ወደታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚያሰርጉበትን አሠራር ቢዘረጉ ሀብትን ከላይ ወደታች ለማውረድ ያግዛል። የንግድና ሌሎች ድርጅቶችም ገበያችሁን ለማስፋፋትና ወረት ለማካበት ዝነኛና ታዋቂ ሰዎችን አምባሳደር እያደረጉ መሾም አንድ ጉዳይ ቢሆንም ድህነትን ከመቅረፍና የኑሮ ደረጃን ከማመጣጠን አንፃር ፋይዳ የለውም። ከዚህ ይልቅ በምትወዷቸው ሰዎች (በራሳችሁ፣ በወላጆቻችሁ፣ በልጆቻችሁ፣ በጓደኞቻችሁ) ስም ፋውንዴሽን በመመሥረት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች መርዳት በተሻለ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ውስጣዊ ዕርካታና የህሊና ደስታ መገብየት የሚቻል ይመስለኛል። ከፈን እንደሁ ኪስ የለውም! ለምሳሌ ያህል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ነኝና ከዚህ በኋላ ትምህርት በገንዘብ ነው እያለ ነው። የማትሪክ ውጤት መጥቶላቸው አቅም የሌላቸው የደሃ ልጆች ስኮላርሺፕ በባለሀብቶች ቢሰጣቸው ሸጋ ነው።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በስደትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት የሚያደርግ የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያ፣ በኬፕታውን ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ጥናት ፕሮጀክት ላይ ከመሥራታቸውም በላይ ‹‹መንገደኛ›› እና ‹‹እላፊ›› በተሰኙ መጻሕፍት በአንባቢያን ዘንድ የሚታወቁ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራቸው  melkamgize@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡