ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ
የምስሉ መግለጫ,ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2017

ከ 7 ሰአት በፊት

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አሸንፈው ወደ ፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የሚመለሱ ከሆነ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ “እብድ” [ኃይለኛ] መሆናቸውን ስለሚያውቁ እንደማይፈታተኗቸው ተናገሩ።

ትራምፕ ለዎል ስትሪት ጆርናል እንደተናገሩት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ተመርጠው ወደ ዋይት ሐውስ ከተመለሱ፣ ቻይና ታይዋንን ለመክበብ የምትፈልግ ከሆነ ከፍተኛ ታሪፍ እንደሚጭኑባት አመልክተዋል።

“ወደ ታይዋን የምትሄዱ ከሆኑ፣ በምርቶቻችሁ ላይ ከ150 በመቶ አስከ 200 በመቶ ግብር እጥላለሁ፣ እላቸዋለሁ” ብለዋል ትራምፕ።

ትራምፕ እያካሄዱት ባለው የምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ፤ በእሳቸው በሚመራው በአዲሱ የሪፐብሊካኖች አስተዳደር የአሜሪካ ተቀናቃኞች ኃይለኛ እንዲሁም የማይገምቱት ምላሽ ስለሚጠብቃቸው ከአሜሪካ ጥቅሞች ተቃራኒ አይቆሙም ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ እንደተጋናሩት ቻይና በታይዋን ላይ ከበባ ብትፈጽም አሜሪካ ወታደራዊ ኃይልን መጠቀም እንደማያስፈልጋት ለዚህም ምክንያቱ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ “ያከብረኛል እንዲሁም ‘እብድ’ መሆኑኔን ስለሚያውቀ ነው” ብለዋል።

ከፕሬዝዳት ዢ ጋር “ጠንካራ ግንኙነት አለኝ” ያሉት ትራምፕ፤ “በእርግጥም በጣም መልካም ሰው ነው፤ . . . ጓደኛዬ ነበር ጥሩ ግንኙነት ነበረን” በማለት የቻይናው መሪ ኃይለኛ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ትራምፕ ከቻይናው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ስለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መልካም ነገሮችን የተናገሩ ሲሆን፣ ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸው አመልክተው በዩክሬን ላይ የተፈጸመውን ወረራ በመቃወም ድርጊቱ ጥቃትን እንደሚያስከትልባቸው ገልጸዋል።

ትራምፕ ከዎል ስትሪት ጆርናል ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ የምርጫ ቅስቀሳቸው ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የስደተኞች ጉዳይን በተመለከተ “ብዙ ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዲመጡ እፈልጋለሁ፣ ነገር ግን በሕጋዊ መንገድ መሆን አለበት” ብለዋል።

ሊካሄድ ከሦስት ሳምንት ያነሰ ጊዜ በቀረው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ዙር የምርጫ ዘመን ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ይወዳደራሉ።

ተፎካካሪያቸው የውቅቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ተክተው የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተወዳደሩ ሲሆን፣ ምርጫው በአሜሪካዊያን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም እየተጠበቀ ነው።