
ከ 9 ሰአት በፊት
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሁለት የአፍሪካ ፕሬዝዳንቶች ጤንነት ጉዳይ መነጋገርያ ሆኖ ሰንብቷል።
ምንም እንኳ ፕሬዝዳንቶቹ ‘በመልካም ጤና ላይ ይገኛሉ’ ቢባልም የርዕሰ ብሔሮቹ ጤንነት ጉዳይ እንዴት የአገር ምሥጢር ተደርጎ አንደተያዘ ሲታይ ግን አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።
ወሬው የጀመረው ከ91 ዓመቱ አዛውንት የካሜሮኑ ፕሬዝዳንት ነበር።
ፖል ቢያ መታመማቸውን ሚኒስትራቸው አስተባብሎ “በጣም ጥሩ በሆነ የጤንነት ሁኔታ ላይ” እንደሚገኙ ገልጿል።
ይኹን እንጂ በካሜሮን የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በፕሬዝዳንቱ ጤና ላይ አንዳች ትንፍሽ እንዳይሉ እግድ ተጥሎባቸዋል።
በሌላ ወገን ደግሞ የማላዊ ፕሬዝዳንት ላዛረስ ቻክዌራ ጤንነት አስጊ ሁኔታ ላይ ነው ተብሎ ሲወራ፣ ጽህፈት ቤታቸው ፕሬዝዳንቱ በዋና ከተማዋ ሊሎንግዌ በእግራቸው ሲንሸራሸሩ እና ስፖርት ሲሠሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምሥል ለቅቋል።
በአፍሪካ ፖለቲካ ላይ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማይለስ ቴንዲ የአፍሪካ መሪዎችን የጤና ሁኔታ ምሥጢራዊነት እና የሚናፈሱ ወሬዎችን በሚመለከት ሲያስረዱ “ፖለቲካው ላይ ገኖ እንዲቆይ የሆነ ብረት ሰውን መሳል ያስፈልጋል፤ ደካማነትን ወይም ተጋላጭነትን ማሳየት አይፈለግም” ይላሉ።
ቻክዌራ እና ቢያ ስለ እነሱ የጤና ሁኔታ የሚናፈሰውን ወሬ ለመቀልበስ የተጠቀሙት ብልሃት የተለያየ ቢሆንም ግባቸው ግን ተመሳሳይ ነው።
ይህም ጠንካራ እና ብርቱ የሆነ ምሥላቸውን ማሳየት እና እርሱን መጠበቅ ነው።
ከዚያ አለፍ ያለው እና ምናልባትም ዋናው ደግሞ ተቀናቃኞቻቸውን እና ተገዳዳሪዎቻቸውን “እዚያው ባላችሁበት አርፋችሁ ተቀመጡ” የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ ይመስላል።
- በሰሜን ጎጃም ዞን ድሮንን ጨምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ18 ጥቅምት 2024
- በጫሞ ሐይቅ ላይ ጀልባ ተገልብጦ 13 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ፖሊስ ገለጸ18 ጥቅምት 2024
- በሁለት ሳምንት ውስጥ በአማራ ክልል 11 ዳኞች መታሰራቸው ተነገረ18 ጥቅምት 2024

የተደበቀ ህመም እና ህልፈት
የጤናቸው ሁኔታ እና ህልፈታቸው ሲስተባበል እና ሲድበሰበስ ከቆዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች መካከል በኢትዮጵያ የሥልጣን መንበር ላይ ከሃያ ዓመታት በላይ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንዱ ናቸው።
በፓርቲያቸው እና ከፓርቲያቸው ውጪ የነበሩ ተቀናቃኞቻቸውን በእስር እና በስደት ገለል አድርገው በጠንካራ ክንዳቸው አገሪቱን ሲመሩ የቆዩት መለስ ዜናዊ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ተደማጭ መሪ ነበሩ።
የምዕራባውያኑ ወዳጅ የነበሩት መለስ በ2004 ዓ.ም. ከተለያዩ መድረኮች እና የመገናኛ ብዙኃን መጥፋታቸውን ተከትሎ የጤንነታቸው ሁኔታ ላይ ጭምጭታዎች ቢሰሙም መንግሥታቸው ግን ዝምታን መርጦ ቆይቶ ነበር።
የተቃዋሚ የመገናኛ ብዙኃን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው ማረፋቸውን የሚገልጽ ዜና ሲያሰራጭ፣ ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸው መታመማቸውን አምነው እያገገሙ እንዲሁም ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸው ነበር።
ነገር ግን ነሐሴ 14/2004 ዓ.ም. ማለዳ ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ57 ዓመታቸው ማረፋቸውን ለኢትዮጵያ እና ለዓለም ሲያረዳ ለሳምንታት ሲናፈስ የነበረው የህልፈታቸው ዜና ዕውን መሆኑ ተረጋገጠ።
በተለያዩ ጊዜያት አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች ስለጤናቸው ሁኔታ ሲጠየቁ በዝምታ ያልፉታል አልያም በቁጣ ይመልሰሉ።
በ2010 (እአአ) የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሮበርት ሙጋቤ ስለጤንነታቸውን የሚወራውን አሉባልታ አስመልክተው “በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የተቀነባበረ ርቃኑን የቀረ ውሸት” ሲሉ ነበር ያጣጣሉት።
የመሪዎች ጤና እንደ የአገር ጤና
ፕሮፌሰር ቴንዲ እንደሚሉት ከሆነ የፖለቲካ ጨዋታው ኃይልን ጠብቆ ለማቆየት የሚደረግ “የወንዶች ጥንካሬ መፈታተሻ” ነው።
አክለውም ፖለቲካው የወንዶች የበላይነት የተጫነው በመሆኑ ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ እና ወደፊት እንዲመጡ ማድረግ ላይ ጉልበቱ ይዝላል።
በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ አንዲት ሴት ርዕሰ ብሔር ብቻ መኖሯን የሚጠቅሱት ምሑሩ፣ የታንዛኒያዋ ሳሚያ ሱሉሁ ሐሰን፣ እርሷም ወንድ አለቃዋ ሲሞት ምክትል ስለነበረች ሥልጣኑን መረከቧን ያስታውሳሉ።
በአፍሪካ እና በሌሎች አገራትም የፖለቲካ መሪዎች የጥንካሬ እና ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ የመዝለቅ ምሳሌ ሆነው እንዲታዩ ይጠበቃል።
በዚህ ዓመት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ተያይዞ እንደታየው መሪው እያረጁ ሲሄዱ፣ የጤና ሁኔታቸው አሳሳቢ ብሔራዊ ጉዳይ ሆኗል።
በጆሃንስበርግ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት አዴኬዬ አዴባጆ በአህጉሪቱ ያሉ መሪዎች “የአገራቸው ጤንነት ከእነርሱ ጤንነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ እንዲሰማን ያደርጋሉ” ይላሉ።
ለዚያም ነው እነርሱ ባሳላቸውም ሆነ ባስነጠሳቸው ቁጥር የብሔራዊ ደኅንነት እና ምሥጢር እንዲሆን የሚደረገው።
ርዕሰ ብሔሮቹ አንድ ነገር ቢሆኑ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት፣ ገበያው፣ የፖለቲካውን ምኅዳርን ያቆመው ዓምድ በሙሉ ይብረከረካል የሚሉት ደግሞ በዚምባብዌ የደኅንነት ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ግለሰብ ናቸው።
ለዚያም ነው በመሪዎች ዙሪያ ያሉ አፋሽ አጎንባሾች ምንም ዓይነት ወሬ እንዳይሾልክ ተጨማሪ ጥንቃቄ የሚያደርጉት።
የፖለቲካ ተቋማት ደካማ በሆኑባቸው አገራት፣ የፖለቲከኞች መተካካት ያለ ተግዳሮት መካሄድ እንዲችል የተጣለ መሠረት የለም፤ ያም የትኛውም የሚፈጠር የሥልጣን ክፍተት ሽኩቻ እና ግጭት መቀስቀሱ አይቀርም ተብሎ ይሰጋል።
ከሁለት አስርታት በፊት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ያስተዳድሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ላውረንት ካቢላ በግል ጠባቂያቸው ተገደሉ።
ባለሥልጣናት መገደላቸውን ለመናገር ተቸግረው ነበር። ከዚያ ይልቅ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እስኪወስኑ ድረስ ለሕክምና ወደ ዚምባብዌ መሄዳቸውን ይናገሩ ነበር።
በኋላም ልምድ ያልነበረው የፕሬዝዳንቱ ልጅ የአገሪቱ ቀጣይ መሪ ሆኖ ተሾመ።
እኤአ በ2012 በማላዊ ደግሞ የፕሬዝዳንት ቢንጉ ዋ ሙታሪካ ሞት ምክትላቸው የነበሩት ጆይስ ባንዳ እንዳይተኳቸው ለማድረግ ያለመ ነው የሚል ጥርጣሬዎችን ባጫረ መልኩ ሳይነገር ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቷል።
ነገር ግን በጎረቤት አገር ዛምቢያ ሁለት ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ላይ እያሉ ሲሞቱ፣ በጋና በ2012 ፕሬዝዳንት የነበሩት ጆን አታ ሚልስ ሲሞቱ የአገሪቱ ሕገመንግሥት ያለ ችግር መተካካቱን ማሳካት ችሏል።

የዘገየ መርዶ
ከሦስት ዓመታት በፊት የታንዛኒያው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ መሞታቸው የተሰማው መታመማቸው ሲስተባበል ከቆየ ከሳምንታት በኋላ ነበር።
በወቅቱ ስለ ፕሬዝዳንቱ ጤንነት ሐሰተኛ መረጃ እያሠራጩ ነው የተባሉ ዜጎች ይታሰሩ ነበር።
መንግሥት የጤና ሁኔታቸውን ረዥም ርቀት ሄዶ ያድበሰበሰላቸው ሌላኛው መሪ ደግሞ የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ኡማሩ ያራዱዋ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በወቅቱ ለአምስት ወራት አልታዩም ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቶ “እየተሻላቸው ነው” ቢልም የመሞታቸው ወሬ ግን በሰፊው ሲናፈስ ቆይቷል።
ያራዱዋ አንዴም አደባባይ ወጥተው ለሕዝብ ሳይታዩ ከአምስት ወር በኋላ የመሞታቸው መርዶ ተነገረ።
ፕሮፌሰር ቴንዲ “አንዳንዶቹ እነዚህ ሰዎች እስከ መጨረሻዋ መራር ፍጻሜ ድረስ ሥልጣን ላይ ተንጠልጥሎ መቆየት ይፈልጋሉ” ይላሉ።
ይህ ግን የአፍሪካ መሪዎች ባህሪ ብቻ አይደለም።
በሌላ አህጉር የሚገኙ መሪዎችም የጤና ሁኔታዎችን ዜጎቻቸው የማወቅ መብት እንዳላቸው ስለማያስቡ በከፍተኛ ምሥጢር ተይዞ እንዲቆይ ያደርጋሉ።
እኤአ በ2017 ለሰባት ሳምንታት ያህል ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት የናይጄርያው ፕሬዝዳንት ቡሀሪ ለዜጎቻቸው በሕይወታቸው “ታምመው” እንደማያውቁ የገለጹ ሲሆን፣ ምን ተፈጥሮ በሥራ ገበታቸው ላይ ለሳምንታት እንዳልተገኙ አላስረዱም።
ካሜሮንን ለ22 ዓመታት ያስተዳደራት ፕሬዝዳንት አህማዶው አሂጆ በ1982 በጤና መታወክ ምክንያት ሥልጣኑን የለቀቀ ብቸኛው አፍሪካዊ መሆኑ ይታመናል።
እንዲህ ዓይነቱ ግልጸኝነት እና ሥልጣንን እንካችሁ ብሎ ማስረከብ የማይታሰብ ነው።
ከ20 በላይ የአፍሪካ መሪዎች በሥልጣን ላይ እያሉ ነው የሞቱት። አንዳንዶቹ ለሕዝባቸው መታመማቸው አንኳ ሳይነገር የመሞታቸው ወሬ ይሰማል።
ይህ ምሳሌ ግን አሂጆን በተኩት ፖል ቢያ የሚደገም አልሆነም።
መሪዎች የጤናቸው ሁኔታ ቢታወቅ አድብተው ያሉ ተቀናቃኞቻቸውን ያነሳሳል፤ ወይንም አገሪቱ ላይ እጃቸውን ማርዘም ወይንም መረበሽ ለሚፈልጉ የውጪ ኃይሎች ዕድል ይሰጣል ሲሉ ሊሰጉ ይችላሉ።
የተወሰኑ ፕሬዝዳንቶች መታመማቸው እንደተሰማ በተቀናቃኞቻቸው መፈንቅለ መንግሥት ተካሄዶባቸዋል።

“የባህል ተጽዕኖ”
በአውሮፓውያኑ 1996 አሁን ዲሞክራቲክ ኮንጎ በመባል የምትታወቀው ዛየር መሪ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የፕሮስቴት ካንሰር ሕክምና እያደረጉ ነበር።
ይህ ደግሞ ለሎረንት ካቢላ በሩዋንዳ የሚደገፉ አማፂያንን አቀናጅተው እንዲመሩ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል።
ሞቡቱ የአማፂያኑን እንቅስቀቃሴ በተደራጀ ሁኔታ ለመመከት የጤና ሁኔታቸው አላስቻላቸውም፤ ስለዚህ ወደ ሞሮኮ ሲሸሹ ካቢላ የአገሪቱን ሥልጣን በበላይነት ተቆጣጠሩ።
“እንደ ደካማ ከታየህ ያ ለውስጥ ተቀናቃኞችህ ምልክት ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ቴንዲ።
ሁለት ፕሬዝዳንቶች በሥልጣን ላይ ሳሉ ሲሞቱ ላየው የ41 ዓመቱ ናይጄሪያዊ አርሶ አደር እና መምህር አቤኩ አዳምስ ግን የጤናን ጉዳይ ምሥጢር አድርጎ መያዙ “የባህልም ተጽዕኖ” ነው።
“በበርካታ የአፍሪካ አገራት ስለ ጤና ሁኔታ ምሥጢር አድርጎ መያዙ የፈውስ ሂደቱ አካል ተደርጎ ይታሰባል። ለዚህም ይሆናል ስለ ጤና ሁኔታቸው የሚደብቁት፤ አልያም የሚዋሹት” ይላል።
ይሁን እንጂ ተራው ማኅበረሰብ የጤና ሁኔታው ምሥጢራዊነትን የመጠበቅ መብት ቢኖረውም፣ በርካታ ኃላፊነት የተጫናቸው መሪዎች ግን ይህ ዕድል የላቸውም። ምክንያቱም የእነርሱ ጤና መላ አገሪቱ ላይ ተጽዕኖው ቀላል አይደለም ሲሉ የሚከራከሩ አሉ።
በርካታ አፍሪካ አገራት የመተካካት ሂደቱን በሚገባ እየገነቡ ሲመጡ የመሪዎች ጤና ሁኔታ ላይ የበለጠ ግልጽ እየሆኑ መምጣት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
አዳምስ “መንግሥታት እንዲህ ዓይነትን መረጃ ለዜጎቻቸው የማጋራት ግዴታ አለባቸው” ይላል።
ዜጎች ግብር ከፍለው የሚደግፉትን መንግሥት መሪ ጤና ሁኔታ የማወቅ መብት አላቸው ሲል ሃሳቡን ያጠናክራል።
በማላዊ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ባለው ብርቱ ፉክክር የተነሳ ሊሆን ይችላል ፕሬዝዳንቱ በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን ለማሳየት ስፖርት ሲሠሩ እንዲታዩ የተደረጉት።
በተቃራኒው ደግሞ አምስት ተከታታይ ምርጫዎችን ተቃዋሚዎች ተጭበርብሯል እያሉም ቢሆን ያሸነፉት ቢያ ግን የጤናቸው ሁኔታ ዝም ዝም ተብሏል።
ዲሞክራሲ በሰፈነበት አገር የመሪዎች ጤናን በሚመለከት አገራት ግልጽ መሆን እንዳለባቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን በአፍሪካ ባለው የፖለቲካው ባህሪ የተነሳ፣ በተጭበረበረ ምርጫ ሥልጣን የያዙ መሪዎች ባሉበት፣ መፈንቅለ መንግሥት በተለመደበት ስለጤና ሁኔታ ግልጽ መሆን ላይ መሪዎች ደፋር መሆን ይቸግራቸዋል።