የያህያ ሲንዋር ፖስተር
የምስሉ መግለጫ,ከያህያ ሲንዋር መገደል በኋላ ሐማስ አዲስ መሪ ለመሰየም እየመከረ ነው

ከ 7 ሰአት በፊት

ባለፈው ሐሙስ መገደሉ የተረጋገጠው የሐማስ ጠቅላይ መሪ ያህያ ሲንዋርን ማን ይተካ በሚለው ጉዳይ ውይይት መጀመሩን ሁለት የቡድኑ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእስራኤል ዒላማ የሆነው የሐማስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ውስጥ ከሁሉ በበለጠ ነባር የሚባሉት አመራር እና ከጋዛ ውጪ ያለውን ክንፍ የሚመሩት ኻሊል አል-ሃያ መሪ ሆነው እንደሚመረጡ ይጠበቃል።

ኻሊል አል-ሃያ ያህያ ሲንዋር ከቀናት በፊት ከመገደሉ በፊት የፍልስጤማውኢው ቡድን ምክትል ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል።

ከጋዛ ውጪ የሐማስ ዋነኛ መቀመጫ በሆነችው ኳታር ውስጥ የሚገኙት ኻሊል አል-ሃያ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን የተኩስ አቁም ንግግር ሲመሩ ቆይተዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ እየተካሄደ ባለቀው ጦርነት ምክንያት በጋዛ ስላለው ሁኔታ እና ስለቀጠናው ፖለቲካ የበሰለ ዕውቀት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ኻሊል አል-ሃያ ከብዙዎች ጋር ግንኙት አላቸው ይባላል።

በቅርቡ የሐማስ ከፍተኛ የአመራር አባላት ስብሰባ ተቀምጠው የያህያ ሲንዋርን ምክትል ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እስራኤል ሁሉንም የሐማስ መሪዎች አድኖ የማጥፋት ዓላማ ያላት ሲሆን፣ በተለይ ባለፈው ዓመት የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ ሲንዋር በእስራኤል ከሚፈለጉ የሐማስ መሪዎች መካከል ቁንጮው ነበረ።

ያህያ ሲንዋር በጋዛ የሚገኘው የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ መሪ የነበረ ሲሆን፣ ኢስማኤል ሃኒያ ደግሞ የቡድኑ የፖለቲካ ክንፍ መሪ ነበረ።

የሐማሱ የፖለቲካ ቢሮ መሪ ኢስማኤል ሃኒያ ባለፈው ዓመት ሐምሌ በኢራኑ አዲስ ሲመተ በዓል ላይ ለመገኘት መዲናዋ ቴህራን ውስጥ ሳሉ መገደላቸው ይታወሳል።

አንድ ነባር የሐማስ ባለሥልጣናት ሲንዋር ባለፈው መስከረም 2016 ዓ.ም. እስራኤል ላይ በቡድኑ የተፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ያቀነባበረ መሆኑን ተናግረው፣ ከሃኒያ ግድያ በኋላ ሲንዋር የቡድኑ ጠቅላይ መሪ ሆኖ መሾም ለእስራኤል ግልፅ መልዕክት ለማስተላለፍ የተደረገ እርምጃ ነበር ብለዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄዱ የተኩስ አቁም ድርድሮች ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ ባለቡት የቆሙ ሲሆን፣ ብዙዎች ይህ የሆነው በሲንዋር አመራር ምክንያት ነው ይላሉ።

ምንም እንኳ ሲንዋር ቢገደልም አንድ ነባር የሐማስ አመራር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቡድኑ የተኩስ አቁም ስምምት እና የታጋቾች መለቀቀን በተመለከተ ያለውን አቋም አሁንም አይቀይርም።

ሐማስ እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ነቅላ እንድትወጣ፤ የሰብዓዊ እርዳታ በነፃነት እንዲደርስ እና በጦርነት ምክንያት የፈራረሱ ከተሞች መልሰው እንዲቋቋሙ ይጠይቃል። እስራኤል ደግሞ እነዚህን ጥያቄዎች እንደማትቀበል አሳውቃ ሐማስ ሙሉ በሙሉ እጁን እንዲሰጥ ትጠይቃለች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ የፍልስጤሙ ንቅናቄ ሐማስ ትጥቁን እንዲፈታ አና እጁን እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የሐማስ አመራሮች ግን “ይህ በፍፁም የሚታሰብ አይደለም” ይላሉ።

“እየታገልን ያለውን ለሕዝባችን ነፃነት ነው። በፍፁም እጅ አንሰጥም። እስከ መጨረሻው ጥይት ድረስ እንዋጋለን፤ እስከመጨረሻው ወታደር ድረስ እንፋለማለን፤ ልክ ሲንዋር እንዳደረገው።”

ሐማስ በቅርብ ዓመታት ከደረሰበት ኪሳራ መካከል የያህያ ሲንዋር ግድያ ዋነኛው የሚባለው ነው። ምንም እንኳ ሲንዋርን ማን ይተካው የሚለው ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም ቡድኑ ከ1990ዎቹ ጀምሮ መሪዎቹ ሲገደሉበት በጥንቃቄ በመምረጥ ይታወቃል።

እስራኤል የሐማስ መሥራቾች እና አመራሮችን በመግደል ስኬታማ ብትሆንም፣ ቡድኑ ግን አዳዲስ አመራሮችን ወደላይ በማምጣት ጥንካሬውን እያሳየ ይገኛል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር በምታደርገው ጦርነት መካከል በጋዛ የሚገኙ እስራኤላዊያን ታጋቾች ጉዳይ አጠያያቂ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል።

የያህያ ሲንዋር ወንድም ሞሐመድ ሲንዋር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቡድኑ ውስጥ ወደፊት ብቅ እያለ የመጣ ግለሰብ ሆኗል። ሞሐመድ በጋዛ የሚገኘውን ሐማስ እየመራ እንዳለ ይገመታል። እንዲሁም የቡድኑን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ የሚወስን ግለሰብ ሊሆን ይችላልም ይባልለታል።

ሐማስ አዲስ ተተኪ መሪ ለመምረጥ ደፋ ቀና በሚልበት በዚህ ወሳኝ ወቅት በጋዛ ያለው ጦርነት እየተፋፋመ ይገኛል።

ቅዳሜ ዕለት በሰሜናዊ ጋዛ ጃባሊያ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ከ10 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። እስራኤል ሐማስ ተመልሶ እየተደራጀ ነው በሚል በጋዛ የምታደርገውን ጦርነት አጠናክራ ቀጥላለች።