” መዋጋት ርስት አይደለም። ለ42 ዓመታት በውግያ ቆይቻለሁ። እኔ እጣ ፈንታዬ መዋጋት ነው ብዬ አላምን ፤ አቋሜ ውግያ አያስፈልግም ይቁም የሚል ነበር ፤ አሁንም አቋሜ ያው ነው የተለወጠ የለም !! ” – ጄነራል ሳሞራ የኑስ

ከሰሞኑን የቀድሞው የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሳሞራ የኑስ አነጋጋሪ ቃለ ምልልስ ሰጥተው ነበር።
ከረጅም ጊዜ በኃላ ወደ ሚዲያ ቀርበው ቃላቸውን የሰጡት ብራኸ (ከፍታ) ለተሰኘ በዩትዩብ ላይ ለሚተላለፍ ፕሮግራም ነው።
ምን አሉ ?
የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠ/ሚ አቶ ኃለማርያም ደሳለኝ በጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ከመተካታቸው በፊት በእሳቸው (ጄነራል ሳሞራ) እና በአገር ድህንነት ሃላፊ በነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ መካከል አለመጣጣም እንደነበር በዚህም ጠቅላይ ሚንስተር ዶ/ር ዐብይ አህመድ የኦህዴድ ምክትል ሊቀመንበር እያሉ እንዲያስሯቸው ሲጠይቋቸው ” አላስርም ! ” ማለታቸውን አንሰተዋል።
ጄነራል ሳሞራ የኑስ ፥
” ያኔ ዐብይን እሰረው ተብዬ አይሆንም ካልኩኝ ዛሬም ልክ ነኝ። ምክንያቱ እኔ የሰራዊት መሪ እንጂ የሲቪል ፓለቲከኛ አሳሪና መሃሪ አይደለሁም።
መከላከያ ሲቪል ፓለቲከኛ የማሰር ስልጣንና ልኡክ የለውም።
ዐብይ ያኔ የአንድ ታላቅ ክልልና ህዝብ አመራር ነበር። ታላቁ ህዝብ ማለት ኦሮሞ ነው። ያኔ የኦሮሞ ህዝብ መሪ የፓለቲካ ድርጅት የነበረው ኦህዴድ ነው። የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አብይ ነበር። በተጨማሪም የፓርላማ የህዝብ ተመራጭ አባል ነበር።
ዐብይ ያኔ መታሰር ከነበረበት ጥንካሬና ድክመቱ ወደ ሳራሞራ ሳይሆን ወደ ፓርለማ ነው የሚወሰደው።
ከፓርላማ ካለፈ ወደ ያኔው የኢህአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ይቀርባል።
የኢህአዴግ ሊቀመንበሩና ጠ/ ሚንስትሩ የዐብይ ድክመት ልክ ነው ብሎ ካመነበት ከፓርላማ ሃላፊነቱ ማንሳት አለበት።
እንዲህ ሆኖ ራሱ ሃይለማርያም ደሳለኝ ዐብይን የማሰር ስልጣን ስለሌለው ወደ ኦህዴድ መላክ አለበት።
ኦህዴድ ካመነበት ደግሞ ይታሰር ብሎ ከወሰነ የሚመለከተው የህግ አካል እንጂ ሳሞራ ዐብይን የማሰር ስልጣን የለውም ” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፦
– በትግራዩ ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ እልቂት መፈጸሙን እንደሚያምኑ፤
– የትግራዩ ጦርነት መንስኤ የፓለቲካ ብልሽት ፤ የአመራሮች መበስበስና ከህዝብ አገልጋላይነት መውጣት ውጤት እነደሆነ፤ የአማራ ኤሊቶች የትግራዩ ጦርነት አንዲጋጋል ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ በርካታ እላፊ ነገሮች እንደተናገሩ፤
– የትግራዩ ጦርነት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡ ወታደሮች የተሳተፉበት ቢሆንም የሁሉም ክልሎች ህዝብ ደግፎታል ተሳትፎበታል ማለት እንዳልሆነ፤
– በትግራይ ጦርነት የሻዕብያ ሃይል አጋጣሚው በመጠቀም የትግራይን ህዝብ ያለ ስሙ ስም በመስጠት አንገቱ ለማስደፋትና ለማጥፋት እንደዘመተ፤
– ከጦርነቱ በፊት ከምርጫው ጋር ተያይዞ የነበሩት የእልህ አገላለጾችና አካሄድ እንዲቆሙ በሁለቱም በኩል ሲገስጹ እንደነበር፤
– ጦርነቱ እንዳይነሳ ፤ ከዛም እንዲቆም ብዙ ጥረት እንዳደረጉ፤
– ” ጄነራል ሳሞራ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ወግነው በድብቅ ጦርነት መርተዋል / ተሳትፈዋል ” የሚለው ወሬ ጦርነቱ የከበዳቸው የትግራይ ፓለቲከኞች ለድክመታቸው መሸፈኛ የፈጠሩት እንደሆነ ፤ ጦርነቱ ሲጀመርም ሆነ ሲፋፋም ከቤተሰቦቻቸው ጋር አዲስ አበባ እንደነበሩ፤
– መዋጋት ርስት እንዳልሆነ ፤ ለ42 ዓመታት በውግያ እንደቆዩ ፤ እጣ ፈንታቸው ውግያ ነው ብለው እንደማያምኑ ፤ አቋማቸው ውግያ አያስፈልግም የሚል እንደሆነ ፤ አሁንም ድረስ አቋማቸው ያው እንደሆነ፤
– ያልተዘጋጁበትን፣ ያላመኑበትን ወግያ እንደማይሳተፉ፣ እንደማይዋጉ፤
– እምነታቸው የትግራይ ህዝብ መዋጋት የለበትም የሚል እንደሆነ ፤ እንደ አመራር ህዝቡ ወደ ውግያ መግፋት የለበትም የሚል እንደሆነ ፤
– ውግያ ሲጀመር አከባቢ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ እና አቶ ግርማ ብሩን አግኝተው ውግያ እንዳይጀመር እንደጠየቁ ፤ እነሱም እንደ አመራር የሰጧቸው መልስ እንዳለ፤
– ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት መንግስትንና ጀነራሎቹን ጦርነቱ እንዲቆም እንደጠየቁ ፤ እስከ መጨረሻ ድረስም ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ ጥረት እንዳደረጉ፤
– የትግራይ ህዝብ ሃያ ዓመት እየቆጠረ መዋጋት እንደሌለበት ፤ ጦርነትም እንደሰለቸው፤ የሰላም አርአያ መሆን እንደሚፈልግ ፤ ፓለቲከኞችም የህዝበ ሰላም መጠበቅ እንዳለባቸው፤
…. የሚሉና ሌሎችንም ጉዳዮች አንስተዋል።
የጄነራሉ አቋም የአሁን ወይስ የነበረ ?
የመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ጄነራል ሳሞራ የኑስን ከ5 ዓመታት በፊት በ2012 ዓ.ም ህዳር እና ታህሳስ ወር ላይ እንዲሁም ጦርነቱ ተጀምሮ የፌደራል መንግስት መቐለ በተቆጣጠረበት ወቅት የካቲት 2013 ዓ.ም በአካልና በስልክ አግኝቶዋቸው ሃሳባቸውን ሰጥተው ነበር።
ጀነራል ሳሞራ ሀገራዊ ኒሻን ተሸልመው በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ በመቐለ ከተማ ፕላኔት ሆቴል አግኝቶ ባናገራቸው ወቅት ፥ በዚህም በዚያም በወጣቶች የሚታይ የነበረው የጦረኝነት ስሜት ፓለቲከኞቹ በማርገብ ሃላፊነታቸው እንዲወጡ ወታደራዊ ምክር ሰጥተው ነበር።
ጥር 2012 ዓ/ም ደጀና ላይ 45ኛው የህወሓት የምስረታ በዓል ለማክበር ለተሰባሰቡት ወጣቶች ባሰሙት ንግግር ፥ ወጣቶች ከዚህም ከዚያም ያሉ ፓለቲከኞች በሚለኩሱት ጦርነት ገብተው እንዳይቃጠሉ የሚያስገነዝብ አባታዊና ወታደራዊ ምክር አስተላልፈው ነበር።
ጦርነቱ ከተጀመረ እና ከተባባሰ በኃላ በሰጡትም አስተያየት ጦርነትን ከበፊቱ የባሰ እንደተጠየፉት ገልፀውለት ነበር።
ያንብቡ
https://teletype.in/@tikvahethiopia/lTm24ja5TwM