
21 ጥቅምት 2024, 14:12 EAT
ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ትምህርት ቤቶች የነበሯቸው እንዲሁም በቱርክ የተካሄደን መፈንቅለ መንግሥት መርተዋል ተብለው የሚከሰሱት ሃይማኖታዊ መሪ ፌቱላህ ጉለን በ83 ዓመታቸው ማረፋቸውን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋገጠ።
ከቱርክ ሸሽተው በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ የኖሩት ጉለን ፔንሲልቬኒያ ውስጥ ሆስፒታል ከገቡ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን የቱርክ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
‘ጉለን ሙቭመንት’ የተባለው በቱርክ እና በዓለም ዙሪያ ተከታዮች ያሉት ተጽእኖ ፈጣሪ የእስልምና ሃይማኖት እንቅስቃሴ መሪ የሆኑት ፌቱላህ ጉለን አንዳንድ ጊዜ የቱርክ ሁለተኛው ኃያል ሰው እየተባሉ ይገለጻሉ።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ታይብ ኤርዶዋን በአውሮፓውያኑ 2016 የተፈጸመውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የጉለን እንቅስቃሴ የመራው ነው በማለት የከሰሱ ሲሆን፣ ጉለን ግን አስተባብለዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን አንካራ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “የጨለማው ድርጅት” መሪ ናቸው ኣሏቸው ጉለን መሞታቸውን የደኅንነት ምንጮች ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ጉለን በቱርካውያን ዘንድ እውቅናን ያገኙት በአገሪቱ ያሉ ወጣቶች መንገዳቸውን በመሳታቸው ትምህርት ላይ ትኩረት መስጠት ወሳኝ ነው በሚል በሚያራምዱት አቋም ነው።
በተጨማሪም ጉለን አካታች የሆነ፣ ከራስ በላይ ለሌሎች የሚያስብ እና በሥራ የሚያምን እስላማዊ አመለካከትን በማራመድም ይታወቃሉ።
እንቅስቃሴው በቱርክ ውስጥ ‘ሂዝሜት’ ወይም ‘አገልግሎት’ በሚል ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ ታዋቂ የሆኑ የትምህርት ተቋማትን በመላዋ ቱርክ እና በዓለም ዙሪያ ለመክፈት ችሏል።
ይህ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶች የነበሩት ሲሆን፣ በቱርክ የተከሰተውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ትምህርት ቤቶቹ ለቱርክ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸው ይታወሳል።
- የአፍሪካ መሪዎች የጤናቸው ጉዳይ ስለምን ምሥጢራዊ እንዲሆን ይፈልጋሉ?20 ጥቅምት 2024
- እስራኤል በኢራን ላይ ያቀደችውን ጥቃት አሜሪካ የገመገመችበት ሰነዶች ሾልከው ወጡ21 ጥቅምት 2024
- “በእሳት እየተቃጠልን እያያችሁ ዝምታን መረጣችሁ” – እናት እና ልጆች በእሳት ቃጠሎ ያጣው ቤተሰብ21 ጥቅምት 2024

ይህ እንቅስቃሴ እየጎለበተ ሲሄድም ተከታዮቹ ወደ ንግድ፣ ወደ መንግሥት ሥራዎች በመሰማራት እና በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ውስጥ በስፋት መሳተፍ ጀመሩ።
በአንድ ወቅት የፕሬዝዳንቱ ወዳጅ የነበረው እንቅስቃሴ ኤርዶዋን በአውሮፓውያን 2013 ፊታቸውን አዙረውበት በመቶዎች የሚቆጠሩትን ትምህርት ቤቶቹን ለመዝጋት እና “በመንግሥት ወስጥ መንግሥት” እየሆነ ነው በሚልም መንግሥታቸውን ከጉለን ተከታዮች ለማጽዳት ዛቱ።
የጉለን ደጋፊዎች የሆኑ የፖሊስ መኮንኖች በኤርዶዋን ደጋፊዎች ላይ ፍተሻ እያካሄዱ ነው በሚል የተከሰሱ ሲሆን፣ በ2016 የቱርክ መንግሥት ‘ሂዝሜት’ ሽብርተኛ ድርጅት ነው በማለት በይፋ አወጀ።
ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ በቱርክ ሠራዊት ውስጥ የነበረ አንጃ ኤርዶዋን ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አደረገ። ዓላማውም የቱርክን ዴሞክራሲ ከፕሬዝዳንቱ አምባገነንነት ለመጠበቅ የሚል ነበረ።
በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ምሽት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በወታደሮች ሲወረሩ፣ በኢስታንቡል እና አንካራ ፍንዳታዎች ተከስተዋል። ተቃዋሚዎች ላይ ጥይት የተተኮሰ ሲሆን በአገሪቱ ፓርላማ ላይ እና በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት ላይ ተኩስ ተከፍቶ ነበር።
ነገር ግን መፈንቅለ መንግሥቱ የአገሪቱን ሕዝብ ወይም የአብዛኛውን ጦር ሠራዊት ድጋፍ ሳያገኝ በመቅረቱ ሙከራውን ያካሄደው የሠራዊቱ ክፍል መሪዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተገደዱ።
የቱርክ መንግሥት ለመፈንቅለ መንግሥቱ ጉለንን ተጠያቂ ቢያደርግም ፌቱላህ ጉለን ግን ክሱን አስተባብለው ሙከራውን አውግዘውታል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር ተያይዞም በርካታ የአገሪቱ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ሠራተኞች ለእስር ተዳርገዋል።
ከሃያ ዓመታት በፊት ከቱርክ ተሰደው ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገው የቆዩት ጉለን በመፈንቅለ መንግሥቱ ወቅትም እዚያው ነበሩ።
ቱርክ ጉለን ለፍርድ እንዲቀርቡ ተላልፈው እንዲሰጧት ብትጠይቅም የአሜሪካ ባለሥልጣናት ግን መጀመሪያ ግለሰቡ በመፈንቅለ መንግሥቱ ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲቀርብ ጠይቀዋል። በዚህም ጉለን እስከ ህልፈታቸው ድረስ በአሜሪካ ቆይተዋል።