
ከ 9 ሰአት በፊት
ኤርትራዊቷ ስደተኛ ሰሜን አየርላንድ ውስጥ አንዲት የማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኛን በተደጋጋሚ በስለት በመውጋት በቀረበባት ክስ እስር እና ከአገር እድትባረር ተፈረደባት።
የ25 ዓመቷ ኤርትራዊት ፊዮሪ ከሰተ ከጥቃቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበችበት ጊዜ በሠራተኛዋ ላይ አካላዊ ጉዳት ማድረሷን አምናለች።
ተከሳሿ በማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኛዋ ላይ ጥቃቱን የፈጸመችው ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ ሳትሰጥ በድንገት በስለት ክንዷን እና ጭንቅላቷን መውጋቷ ተነግሯል።
በጥቃቱ ወቅት ፊዮሪ ዕድሜዋ ትንሽ እንደሆነ በመግለጿ በሰሜን አየርላንድ በሚገኝ አንድ የጤና እና ማኅበራዊ እንክብካቤ መስጫ ተቋም ውስጥ ነበረች።
ጥቃቱን የፈጸመችው ከሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ በወቅቱ ከመኖሪያው ማዕከል ለቀናት ጠፍታ ከቆየች በኋላ በፖሊስ ተይዛ በማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛዋ ታጅባ ከተመለሰች በኋላ ነው።
ፊዮሪ በማዕከሉ ውስጥ ከማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኛዋ ጋር ወደ ማዕድ ቤት በሄዱበት ጊዜ ነው ያለምንም ምክንያት እና ማስጠንቀቂያ በክንዷ ላይ እንዲሁም በጭንቅላቷ ላይ በተደጋጋሚ በስለት የወጋቻት።
ጥቃት ፈጻሚዋ ወዲያው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስትውል፣ የማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኛዋ ለድንገተኛ ቀዶ ህክምና በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች።
ፖሊስ ምርመራ ባደረገበት ወቅት ፊዮሪ ጥቃቱን መፈጸሟን አምና ነገር ግን ለድርጊቷ ምንም ዓይነት ምክንያት አልሰጠችም።
- ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሶማሊያ የሚደረገው አደገኛው ሕገወጥ የአልኮል ዝውውር ንግድ21 ጥቅምት 2024
- ቱርክ በመፈንቅለ መንግሥት የምትፈልጋቸው ሃይማኖታዊ መሪ ፌቱላ ጉለን አረፉ21 ጥቅምት 2024
- እስራኤል በኢራን ላይ ያቀደችውን ጥቃት አሜሪካ የገመገመችበት ሰነዶች ሾልከው ወጡ21 ጥቅምት 2024
ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት መጀመሪያ ላይ የስድስት ዓመት እስር የፈረደባት ሲሆን፣ ፊዮሪ አደገኛ ናት በሚል ምክንያት እስሯ በሁለት ዓመት እንዲራዘም ተወስኖባታል።
በውሳኔው ወቅት ዳኛው ጥቃቱን “ጭካኔ የተሞላበት እና አሰቃቂ ከመሆኑ በላይ መጠነ ሰፊ እና ዘላቂ ውጤት ያለው ነው” በማለት፣ ፊዮሪ በድርጊቷ ከመጸጸት ይቅል የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኛዋ እና ፖሊስ አናደውኛል በማለት ከሳቸዋለች ሲሉ ለእስሩ መራዘም ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።
በተጨማሪም ተከሳሿ በቁጥጥር ስር በዋለችበት ጊዜ ማንነቷን ለማረጋገጥ አዳጋች እንደነበር እንዲሁም የተለያዩ የልደት ቀናት እና ዕድሜዋ በተለያየ ሁኔታ ተመዝግቦ መገኘቱን ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል።
ዕድሜዋን በተመለከተ ምርመራ ከተደረገው በኋላ ፊዮሪ ከሰተ ወጣቶች ከሚታረሙበት ማቆያ ወደ ሴቶች እስር ቤት እንድትዘዋወር ተደርጋለች።
ዳኛው ፊዮሪ በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ወደ ሰሜን አየርላንድ መግባቷን በሚመለከት የቀረበላቸውን ሃሳብ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ ነገር ግን “በሕገወጥ መንገድ በድብቅ ገብታ ሊሆን ይችላል” ለዋል።
ጨምረውም ተከሳሿ በእስር ቤት በቆየችበት ጊዜ ያላት ባህሪይ በተደጋጋሚ ቁጡ እና ኃይለኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእስር ቅጣቷን ስትፈጽም ከአገር እንድትባረር አዘዋል።
የሰሜን አየርላንድ ፖሊስ መርማሪ የሆኑት ኮንስታብል ደንሎፕ ጥቃቱ የተከሰተበትን ሁኔታ ሲገልጹ፣ “ወንጀሉን ለመፈጸም የሚያበቃ ሁኔታ አልነበረም፤ ማንም ሰው በሥራ ቦታው እንዲህ ዓይነት ነገር ፈጽሞ ሊገጥመው አይገባም” ብለዋል።
የፖሊስ መኮንኑ ጨምረውም በፊዮሪ ላይ የተላለፈው የእስር ቅጣት በስለት ተወግታ ጉዳት ለደረሰባት የማኅበራዊ ጉዳዮች ሠራተኛ “ፍትህ በማግኘቷ በወተወሰነ ደረጃ መረጋጋትን ይሰጣታል” በማለት ተናግረዋል።