October 21, 2024 – Konjit Sitotaw
የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ማብራሪያ ማቅረባቸውን አስታወቁ።
ጥቅምት 09 ቀን 2017 ዓ.ም የአማራ ፋኖ በወሎ፣ የአማራ ፋኖ ሸዋ ዕዝ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃም እና የአማራ ፋኖ በጎንደር ከፍተኛ አመራሮች በጋራ በመሆን ለሦስተኛ ጊዜ ከውጭ ሚዲያዎች ጋር በስልክ ቆይታ አድርገዋል። በአማራ ማኅበር በአሜሪካ (AAA) አመቻችነት በተደረገው የሚዲያ ብሪፊንግ ተግባር፣ የፋኖ አመራሮቹ ከዋሽንግተን ፖስት (Washington post)፣ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት (Reuters)፣ ዘኢኮኖሚስት (The Economist)፣ ብሉምበርግ (Bloomberg) እና ከአውሮፖ ፍሪላንስ (freelance journalist from Europe) ጋዜጠኞች ጋር ተገናኝተዋል።
በዚህም የፋኖ አመራሮቹ በአማራ ህዝብ ላይ እየሆነ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በተለይም የአብይ አህመድ ቡድን በንፁሃን ላይ እያደረገ ስላለው ጭፍጨፋ አጭር ገለፃ ካደረጉ በኋላ፣ በጋዜጠኞች በኩል የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው መልስ እና ማብራሪያ እንደሰጡ ተገልጿል።
በዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ እና የጦር ወንጀሎች ለማጣራት የውጭ ገለልተኛ ቡድን ገብተው ለማጣራት እንዲችሉ የተኩስ አቁም ስምምነት ልታደርጉ ትቀበላላችሁ ወይ? የአማራ ክልልን ከዋና ዋና ከተሞች በስተቀር 90 በመቶ ተቆጣጥራችኋል ይባላል፣ ክልሉን ሙሉውን ብትቆጣጠሩ ምን ታደርጋላችሁ? እናንተ በምትቆጣጠሯቸው ቦታዎች ለህዝቡ ምን አይነት አገልግሎት እየሰጣችሁ ነው? እና መሰል ጥያቄወች ይገኙበታል።
በተጨማሪም፣ እናንተ በተቆጣጠራችኋቸው ቦታዎች የሚፈጸሙ ህገወጥ ድርጊቶች፣ ለምሳሌ ዘረፋ እና እገታ የመሳሰሉትን እንዴት ነው የምትፈቱት? ህወሓት ከተከዜ ደቡብ የድንበር ጥያቄ አለኝ፣ ተፈናቃዮችንም ወደነበሩበት እመልሳለሁ ብሏል፤ ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚተባበር ገልጿል፤ ስለዚህ እናንተ የትግራይ ተፈናቃዮች መመለስ ላይ አቋማችሁ ምንድን ነው? አንዳንድ ከተሰሙ መረጃዎች ውስጥ ከአማራ ክልል የምግብ እህል እና ልዩ ልዩ ምርቶችን ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ክልሎችም እንዳይሄድ ፋኖ የመከልከል እቅድ አለው ይባላል፤ ይህ እውነት ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ከጋዜጠኞች ቀርበውላቸዋል።
የአማራ ፋኖ አመራሮችም ጋዜጠኞች ላነሷቸው ጥያቄዎች በቂ ማብራሪያ እንደሰጡ ገልጸዋል። ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎቹ በጋዜጠኞቻቸው ለተነሱ ጥያቄዎች የፋኖ አመራሮቹ የሰጧቸውን መልስና ማብራሪያ ለዓለም ሕዝብ እንደሚያደርሱ እንጠብቃለን ሲሉ አመራሮቹ ገልጸዋል።
የፋኖ አደረጃጀቶቹ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማሳወቁን ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉበትም አሳውቀዋል።
በመጨረሻም በውጭ ለሚኖሩ የአማራ ተወላጆች እና በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት የሚሰማችው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በየሚኖሩበት ሀገር ለአማራው ሕዝብ አምባሳደር በመሆን የሚፈጸምበትን ሁሉ እንዲያሳውቁልን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል