ጉግል ፒክስል 9 የተሰኘ ስልኩን ይፋ አደርገል
የምስሉ መግለጫ,ጉግል ፒክስል 9 የተሰኘ ስልኩን ይፋ አደርገል

22 ጥቅምት 2024, 07:06 EAT

ከዓመታት በፊት “ሃሎ” ለመባባል ብቻ የሚውሉ የሞባይል ስልኮች “እንደ ተዓምር” ይታዩ ነበር።

አንዳንዶቹ ስልኮች ከብረት ቢጠነክሩም፣ ከአሎሎ ቢከበዱም ሰዎች ጎናቸው ላይ “ሸጉጠው” በኩራት አደባባይ ይወጡ ነበር።

እነዚህ ስልኮች ለመደወል ግፋ ካለ አጭር የጹሁፉ መልዕክት ከመለዋወጥ የዘለለ አገልግሎት ባይሰጡም ለዓለም ሕዝብ ብርቅ ነበሩ።

ዛሬ ስልኮች ሌላ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በብዛትም በዓይነትም ተበራክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ስልክ መደወል እና መልዕክት መለዋወጥ በጣም ትንሹ ተግባር ነው።

እንዲያም ሆኖ፣ ዘመናዊ ስልኮች እንደ “ተዓምር” የሚያያቸው ሰው ቁጥር ብዙም አይመስልም።

የሆነው ሆኖ፣ የተጠቃሚዎችን ቀለብ ለመሳብ በቅንጡ ስልክ አምራቾች መካከል ያለው ውድድር ጠፏል።

በተለይ ይህ ወቅት ቅንጡ ስልክ አምራቾች አዳዲስ ምርቶቻቸውን ይፋ የሚደርጉበት ነው።

ታዲያ በአዲስ መልክ የተመረቱ ወይም የተሻሻሉ ስልኮችን ለሚፈልጉ ሰዎች የ‘ፌሽታ’ ጊዜ ነው።

ይህ ጊዜ ታላላቆቹ የስልክ አምራች ኩባንያዎች “አምና ከተመረቱት የተሻሉ ናቸው” በሚል ይፋ ያደረጓቸውን አዲስ ምርቶችን ተጠቃሚዎች እንዲገዙ የሚያሳምኑበት ጊዜ ነው።

በቅርቡ ጉግል ‘ፒክስል 9’ የተሰኘውን የተሻሻለውን ምርት ይፋ ሲያደርግ አይፎን 16ም ለገበያ ቀርቧል።

ባለፈው ሐምሌ ወር ደግሞ ሳምሰንግ ባለታጣፊ ስክሪኖቹን ‘ዜድ ፍሊፕ 6’ እና ‘ፎልድ 6’ ይፋ አደርጓል። ሁዋዌም ‘ማት ኤክስቲ’ የተሰኘውንና ስክሪኑ ሦስት ጊዜ የሚተታጠፈውን ምርት በቻይና አስተዋውቋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘የስማርት’ ስልኮች ገበያ እየተቀዛቀዘ ቢመጣም ስልክ አምራች ኩባንያዎች ማስታወቂያዎቻቸውን እያሰደጉ ደንበኞችን ለመሰብ የሚያደርጉት ጥረት ግን አልቀነሰም። እንዲያውም እየጨመረ ይመስላል።

የአፕል ኃላፊ ቲም ኩክ አይፎን 16 “ሰዎች ለስማርት ስልኮችን ያላቸውን ዕይታ ከመሠረቱ” የሚቀይሩ አዳዲስ ገጽታዎችን እንዳካተተ ተናግረዋል።

የጉግል ምርቶች አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ብራያን ራኮውስኪ ስለአዲሱ ‘ፒክስል 9’ ሲናገሩ እጅግ ማራኪ የሆነ ገጽታ አለው ሲሉ ተደምጠዋል።

አንዳንዶች ግን ከዚህ የተቃረነ አስተያየት ሰጥተዋል።

በአሰቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዳለፈ የሚገልጸው ሁዋዌም ምርቶቹን የሚያንቆላጳጵሱ ይዘቶቹን በየጊዜው ያወጣል።

አፕልም ሆነ ጉግል በአዳዲሶቹ ምርቶች የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ከፍ ባለ ሁኔታ አካተዋል።

ለአብነት የጉግል ምርት የሆነው አዲሱ ‘ፒክስል 9’ የተነሱ ፎቶዎች ላይ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የተፈጠሩ ተጨማሪ ይዘቶችን ማከተት ይችላሉ።

ወይም የማያስፈልገውን በቀላሉ ማስወገድ የሚያስችል አማራጭ አለው።

የስልክ ካሜራ

የአይፎን ‘አፕል ኢንተሌጀንስ’ የተሰኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት ቻትጂፒቲን ባበለጸገው ኩባንያ የታገዘ ነው። አስተውሎቱ በአይፎን የምትታወቅን በድምጽ የምታግዘውን ሲሪ በእጅጉ እንድትሻሻል ረድቷል።

ጥያቄው ግን ይህ ሁሉ ለምን አስፈለገ? ማንስ ይህንን ጠየቀ? – የሚል።

‘ሲሲኤስ ኢንሳይት’ በተባለ የቅንጡ የሞባይል ስልኮች ጉዳይ ላይ የሚመራመር ተቋም ውስጥ ባለሙያ የሆነው ቤን ውድ በስልኮች ውስጥ እየተካተተ ያለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት ሕይወትን ቀላል ለማድረግ ጠቃሚ እንደሆ ይገልጻል። ጥያቄው ይህ ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ የዕለተ’ለት ሕይወት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? የሚለው ነው።

ቤን ለብዙኃኑ እጅግ የረቀቁ ስልኮች እጅግ አስፈላጊ እንዳልሆነ ያምናል።

“አሁን ላይ ብዙ ሰዎች ከስልክ የሚፈልጉት እና የሚያውቁት ዋሳኝ ነገር ካሜራውን ይመስለኛል” ይላል ቤን።

የስልክ አምራቾች ይህ አስፈላጊ እንደሆነ ያውቃሉ። ለዚህም ነው አዲስ ተሻሽለው የሚመጡ ስልኮች ከቀደመው ካሜራ ላይ ለውጥ እና ማሻሻያ የሚያደርጉት።

ሆኖም አሁን ላይ ይህንን ራሱ ማድረግ ብዙ ደንበኛ እንደሚያመጣ ማስተማመኛ አይደለም።

“አሁን በትክክል እየሆነ ያለው ነገር ሰዎች ስልካቸውን ይዘው ለረዥም ጊዜ እየቆዩ ነው። ስልክ አይቀይሩም። እንደ አውሮፓውያኑ 2013 የነበረውን እውነት መለስ ብለን ብናይ 30 ሚሊዮን የሞባይል ስልኮች በየዓመቱ ይሸጡ ነበር” የሚለው ውድ “በዚህ ዓመት 13.5 ሚሊዮን ገድማ ሽያጭ” እንዳለ አመልክቷል።

በእርግጥ አሁን ያለው የኑሮ ውድነት ቀውስ ሰዎች ለስልክ ገንዘብ ከማውጣት እንዲቆጠቡ እያደርጋቸው ሊሆን ይችላል።

ሌላው ስልኮች የሚጠቀሙት አካባቢ ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ እና ውድ ግብዓቶችም ለዚህ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ብቅ እያለ የመጣው አዲስ አቋም ለስልኮች ገበያ መቀዛቀዝ ተጠቃሽ ምንክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ አቋም በወላጆች እና በልጆች መካከል እየዳበረ የመጣው ልጆችን ከዘመናዊ ስልኮች ሙሉ በሙሉ የማራቅ ውሳኔ ነው።

ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ከቅንጡ ስልኮች እንዲላቀቁ እየሠሩ ነው።

ለምሳሌ በዩናይትድ ኪንግደም ጥቂት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ስልክ ይዘው እንዳይመጡ አግደዋል።

በርካታ አገራት ደግሞ ‘ከስማርት’ ስልክ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ፖሊሲ ዳግም እያጤኑ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኝ አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ከስልክ መደዋወል እና መልዕክት መለዋወጥ በዘለለ አገልግሎት የማይሰጡ ስልኮችን ብቻ ለተማሪዎቹ ፈቅዷል።

በዚያው አገር ሌሎች በርካታ የመንግሥት እና የግል ተቋማት ተመሳሳይ ውሳኔን እየተከተሉ እነደሆነ ይሰማል።

‘ኢኢ’ የተባለ የሞባይል ስልክ ኩባንያ ከ11 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ሙሉ በሙሉ ስልክ እንዳይጠቀሙ ይመክራል።

በዩናይትድ ኪንግደም ‘ከስማርት’ ስልኮች ነጻ የሆነ የልጅነት ዘመን የሚል ዘመቻ የተጀመረ ሲሆን፣ ኖቫ ኢስት ደግሞ ይህንን ዘመቻ በሰሜን እና ምዕራብ ለንደን ቅራንጫፎች አማካኝነት ታስተባብራለች።

ዘመቻው ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ተባብረው ለህጻናት ስልክ የሚሰጥበት ጊዜ እንዲዘገይ የሚወተውት ነው።

በዩኬ ህጻናት እና ታዳጊዎች ከቅንጡ ስልክ እንዲርቁ የሚወተውት ዘመቻ ተጀምሯለ።

“እኛ ቴክኖሎጂ ጠል ሳንሆን የልጆች ጤንነት ደጋፊዎች ነን” የምትለው ኖቫ ኢስት “የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከልጆች ጋር የሚስማማ ስልክ እንዲያመርቱ እንፈልጋለን። ይህ ዓይነቱ ስልክ ለልጆች እንደ ስልክ መደዋወል፣ የመልዕክት ልውውጥ፣ ሙዚቃ እና የመንገድ ጠቋሚ ካርታ (ማፕ) አገልግሎቶቸን ያለምንም ተጨማሪ ተግባር የያዘ እንዲሆን እንፈልጋለን” ብላለች።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ የሚሠራ ኩባንያ በሆነው ‘ሃጊንግ ፌስ’ የምትሠራው ዶክተር ሳሻ ሉቹኒ ይህ ዓይነቱ ዘመቻ እና መልዕከት እስካሁን አድማጭ እያገኘ አይመስልም ትላለች።

“‘ተስማሚ የሆነ ዲጂታል ዓለም’ እየገነባን እንሄዳለን የሚል ዓይነት ዲስኩር እጅግ እየጨመረ ነው። ነገር ግን የስማርት ስልክ አምራቾች ከዚህ ሃሳብ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ እየሄዱ ነው የሚመስሉት” ስትል ገልጻለች።

ቢቢሲ ይህንን አስተያየት መነሻ አድርጎ ለኦፕል፣ ለጉግል እና ሳምሰንግ ጥያቄ አቅርቧል።

ሳምሰንግ በደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል።

“የሳምሰንግ ተጠቃሚዎች የጋላክሲ ምርቶችን ከእነሱ ጋር በሚስማማ መንገድ መጠቀም ይችላሉ። ለምሳሌ የሳምሰንግ ዲጂታል የደኅንነት ሥርዓቱ ተጠቃሚዎች በሚፈልጉት መንገድ እንዲገለገሉበት የተዘጋጀ ነው። ይህ ሥርዓት ተጠቃሚዎች የሚፈልጉትን አንድ መተግበሪያ የስክሪን ሰዓት መወሰን የሚቻለበት ጭምር ነው” ብሏል።

የስልኮች ተግባር ይገደብ የሚለውን እየጨመረ የመጣውን ጥሪ በፊላንድ የሚገኝ አንድ ኩባንያ ብቻ ጆሮ የሰጠው ይመስላል። ኩባንያው – ኖኪያ ይባላል።

ኖኪያ ለብዙዎችን ቀደምት የሞባይል ተጠቃሚዎች አዲስ ያልሆነ የስልክ ምርት ነው። ኖኪያ አሁን ድረስ መሠራታዊ የደምጽ እና የመልዕክት አግልግሎት ብቻ የሚሰጡ ስልኮችን እያመረተ ነው።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አዲስ ሮዝ ቀለም ያለው ስልክ አስተዋውቋል።

ስልኩ አሁን ቅንጡ ስልኮች ያሏቸው ተግባራት የሉትም።

የስልክ መተግሪያዎች እና የፊት ለፊት ካሜራ በዚህ ስልክ አይገኝም። አንድ ‘ጌም’ ብቻ አለው። ሙዚቃ መዳመጥ የሚፈልጉ ሰዎች ኤፍኤም ጣቢያዎችን መቀያየር ይችላሉ።

‘ሲሲኤስ ኢንሳይት’ የተባለ አንድ ተቋም በዚህ ዓመት በዩናይትድ ኪንግደም ቅንጡ ያልሆኑ 400 ሺህ ስልኮች ለሽያጭ ይቀርባሉ የሚል ግምት አስቀምጧል።

ይህ ቁጥር ከአይፎንም ሆነ ከሌሎች ቅንጡ ስልኮች ጋር ሲነጻጻር ‘እዚህ ግባ’ የሚባል አይደለም። ግን ደግሞ ቀላል የሚባል ሽያጭም አይደለም።

በባዝ ስፓ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና እና ሳይንስ ኮሚዩኒኬሽን ፕሮፌሰር የሆኑት ፔት ኤትቼልስ በቅንጡ ስልኮች አሉታዊ ጎን ላይ አተኩረናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

“ከስማርት ስልኮች የምናገኘው የማይተኩ ጥቅሞች እንዳሉ እየረሳነው ያለ ይመስለኛል። ወደ አሉታዊ ጎኑ በጣም እያዘነበልን ሳይሆን አይቀርም። ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብን ስልኮች ሕይወትን ለማቅለል የተሠሩ እንደሆነ ነው። እያገዙን ነው። መልካም ጎንም አላቸው” ሲሉ ይከራከራሉ።

የሆነው ሆኖ፣ እጅግ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የያዙ የሞባይል ስልኮች በሚመረቱበት እና በሚሸመቱበት በዚህ ጊዜ “የድሮ ስልኮች” ወደ ገበያው መመለሳቸው እና ፈላጊ ማግኘታቸው ሃቅ ነው።