
ከ 6 ሰአት በፊት
አዲስ የሚመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው “የሙሉ ዕውቅና” የምስክር ወረቀት ለማግኘት ሲጠየቁ የነበረው የ200 ብር ክፍያ ወደ 30 ሺህ ብር አደገ።
በአዲሱ የምርጫ ቦርድ የክፍያ ተመን መሠረት አዲስ የሚቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ እና ሙሉ የዕውቅና ምስክር ወረቀቶችን ለማግኘት በድምሩ 45 ሺህ ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ እንዲሁም የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚጠይቀው ክፍያ ተመን ላይ ጭማሪ ማድረጉን ያስታወቀው ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 12/2017 ዓ.ም. ነው።
ከትናንት ሰኞ ጥቅምት 11 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው ይህ የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው ቦርዱ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሰጣቸው ሦስት አገልግሎቶች ላይ ነው።
የዋጋ ጭማሪ ከተደረገባቸው አገልግሎቶች መከካል አንዱ አዲስ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ከቦርዱ የሚያገኙት የጊዜያዊ እውቅና ምስክር ወረቀት ነው። ይህ ጊዜያዊ እውቅና የሚሰጠው ፓርቲ ለማቋቋም የሚፈልጉ “የዜጎች ስብስብ” ነው።
አገር አቀፍ እና ክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲ መመሥረት የሚፈልጉ ግለሰቦች ቢያንስ የ100 ሰዎች ፊርማ የያዘ ቃለ ጉባኤ እና የፓርቲውን ጊዜያዊ ስም እንዲሁም “የምርጫ ሕጉን እና ተያያዥ ሕጎችን የሚያከብሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ” ሲያቀርቡ ይሰጣቸዋል።
- ከኢትዮጵያ ድንበር ወደ ሶማሊያ የሚደረገው አደገኛው ሕገወጥ የአልኮል ዝውውር ንግድ21 ጥቅምት 2024
- ለሳይንቲስቶች እንቆቅልሽ ሆኖ የዘለቀው በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው ከፍተኛ የደም ግፊት22 ጥቅምት 2024
- የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ለተቀናቃኛቸው ወስነው የነበሩ ሦስት ዳኞችን ከሥራ አባረሩከ 9 ሰአት በፊት
ይህ ጊዜያዊ ዕውቅና፤ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ሙሉ ዕውቅና ለማግኘት ማሟላት ያለባቸውን የመሥራቾች ፊርማ ለመሰብሰብ፣ መሥራች ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ እንዲሁም ተያያዥ የምሥረታ ሥራዎችን ለማከናወን የሚጠቀሙበት ነው።
የክፍያ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት በነበረው የዋጋ ተመን መሠረት አዲስ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች ጊዜያዊ እውቅናውን ለማግኘት ይከፍሉ የነበረው 100 ብር ነበር። አዲሱ የምርጫ ቦርድ የዋጋ ማሻሻያ ጊዜያዊ ዕውቅና ለማግኘት ይጠየቅ የነበረው ክፍያን ወደ 15 ሺህ ብር አሳድጓል።
በምሥረታ ላይ ያሉ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ዕውቅናውን ተጠቅመው ፊርማ ካሰባሰቡ እና መሥራች ጠቅላላ ጉባኤ ካደረጉ በኋላ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን የሙሉ ዕውቅና ምስክር ወረቀት ከቦርዱ ያገኛሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው የክፍያ ተመን ይህንን ሙሉ ዕውቅና ለማግኘት ፓርቲዎች መክፈል የሚጠበቅባቸው 200 ብር ነበር።
በፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያገኟቸው አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማድረጉን ያስታወቀው አዲሱ የምርጫ ቦርድ የክፍያ ተመን፤ ይህንን ክፍያ 30 ሺህ ብር አድርሶታል።
በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ክፍያ ተመን መሠረት አዲስ የሚቋቋሙ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ዕውቅና አግኝው የምሥረታ ሥራዎች ለማከናወን እንዲሁም እነዚህን ተግባራት አጠናቀው ሙሉ ዕውቅና ለማግኘት መክፈል የሚጠበቅባቸው የአገልግሎት ክፍያ በድምሩ 45 ሺህ ብር ሆኗል።
ምርጫ ቦርድ ጭማሪ ያደረገበት ሌላኛው አገለግሎት የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ ሰነዶቻቸውን አሻሽለው ዕውቅና እንዲያገኝ ለምርጫ ቦርድ ሲያቀርቡ የሚከፈል ነው። ይህ ክፍያ ከዚህ ቀደም 30 ብር የነበረ ሲሆን በአዲሱ የዋጋ ተመን የዚህ አገልግሎት ክፍያ አምስት ሺህ ብር እንዲሆን እንደተወሰነ ቦርዱ አስታውቋል።
ለሚያስከፍላቸው አገልግሎቶች የዋጋ ማሻሻያ የማድረግ ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በሦስቱ አገልግሎቶች ላይ ይህንን የክፍያ ጭማሪ ያደረገው “ይህን የክፍያ መጠን በየጊዜው ማሻሻል እንደሚያስፈልግ በማመን” እንደሆነ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።