የተርኪዬ ሰንደቅዓለማ

ከ 9 ሰአት በፊት

የኬንያ መንግሥት በመዲናዋ ናይሮቢ ይኖሩ የነበሩ አራት ጥገኝነት ጠያቂ ቱርካውያንን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።

ይህ ድርጊትም ሰዎችን ነጻነታቸው እና ሕይወታቸው አደጋ ላይ የሚወድቅበት በመሆኑ ሁኔታው እንዳሳሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ከኬንያ ወደ ቱርክ የተመለሱት ስደተኞች ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ይህንን መግለጫ ያወጣው በኬንያ መዲና ናይሮቢ ባለፈው አርብ ጥቅምት 08/2017 ዓ.ም. በርከት ያሉ ውጭ አገር ዜጎች መታገታቸውን ተከትሎ ነው።

አንድ ብሪታኒያዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው እርሱ እና ሌሎች የቱርክ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ጭምብል ባጠለቁ ታጣቂዎች ታግተው እንደነበር ገልጿል።

ለስምንት ሰዓታት በእገታ ከቆየ በኋላ የብሪታኒያ ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ የፓስፖርት ቅጅ አሳይቶ አጋቾቹ እንደለቀቁት ግለሰቡ ተናግሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ “የኬንያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብር በተለይም ሰዎችን አስገድዶ ወደ አገራቸው ያለመመለስ ግዴታን እንዲወጣ” አሳስቧል።

በዚህም ምክንያት “ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ነጻነታቸው አደጋ ላይ ወደሚወድቅበት ቦታ መመለስ የለባቸውም” ብሏል።

የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ ከቱርክ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት አራት የቱርክ ዜጎችን አሳልፎ መስጠቱን ገልጿል።

ይህንንም ያደረገው ሁለቱ አገራት [ኬንያ እና ቱርክ] ያላቸውን ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ጠቅሷል።

ተላልፈው የተሰጡት ሰዎችም ክብራቸው በተጠበቀ ሁኔታ ጉዳያቸው እንደሚታይ ከቱርክ መንግሥት ጋራ መስማማቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ መግለጫ አክሏል።

አራቱ ቱርካውያን “የጉለን እንቅስቃሴ” አባላት እንደሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ የጉለን እንቅስቃሴ በቱርክ ውስጥ እና በቀሪው ዓለም የሚደረግ ጠንካራ እስላማዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ የእንቅስቃሴው መሪ ማረፋቸው ተዘግቧል።

ይህ እንቅስቃሴ በፈረንጆቹ 2016 በቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ የተከሰሰ ሲሆን፣ በኋላ ላይም እንቅስቃሴው በሽብርተኝነት ተፈርጇል።

በሰዎቹ ተላልፎ መሰጠት ዙሪያ የቱርክ መንግሥት እስካሁን ምንም አላለም።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1952 ስምምነት መሠረት ሰዎች ነጻነታቸው ወይም ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወደሚወድቅበት አካባቢ በግዳጅ ሊመለሱ አይገባም።

የኬንያ መንግሥት አራቱን ቱርካውያን አሳልፎ ቢሰጥም “የስደተኞችን መብት በመጠበቅ ያልተገደበ ጥረት አደርጋለሁ” ያለ ሲሆን፣ ተላልፈው የተሰጡትን ሰዎች በተመለከተም ጉዳያቸውን ምሥጢራዊነቱን ጠብቆ እንደሚከታተል ገልጿል።

ብሪታኒያዊው ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገረው እርሱ የሚያውቃቸው እና ሁሉም የቱርክ ዜግነት ያላቸው ስድስት ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ናይሮቢ ውስጥ ታግተዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ድርጊቱን ተከትሎ እገታ ለተፈጸመበት ዜጋው እና ለቤተሰቦቹ የምክር አገልግሎት መስጠቱን አስታውቋል።

ስለእገታው የተጠየቀው የኬንያ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ድርጊቱ የተፈጸመው ሁለት ተሽከርካሪዎች አንድ ሌላ ተሽከርካሪን መንገድ በመዝጋት ካስቆሙ በኋላ ነው።

“ከእነዚህ ተሽከርካሪዎች የወጡ ስምንት የታጠቁ ሰዎች መንገድ ከተዘጋባት ሌላኛዋ ተሽከርካሪ ውስጥ የነበሩ ሁለት ተሳፋሪዎችን አስወርደው ወስደዋል” ብለዋል የኬንያ ፖሊስ ቃል አቀባይ ሬሲላ ኦንያንጎ።

የአምኒስት ኢንተርናሽናል የኬንያ ቃል አቀባይ ጉዳዩን ተከትሎ “በኬንያ ምድር ሰባት ቱርካውያን መታገታቸው በጣም አሳስቦናል” ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን የእገታው ክስተቶች እንደሚያውቅ እና ሙሉ መረጃ ሲያገኝ ይፋ እንደሚያደርግ ለቢቢሲ ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶዋን ግንኙነታቸውን ለማሳደግ ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት መሠረት ባለፉት 20 ዓመታት ቱርክ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ወዳጅነት በእጅጉ ከፍ ብሏል።

የኬንያ እና የቱርክ ግንኙነት ግን ከዚህም በላይ ረዘም ያለ ታሪክ ያለው ነው። እንደአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 የኩርድ ተገንጣይ እንቅስቃሴ ቡድን መሪ የነበሩት አብዱላህ ኦቻላን በቱርክ የፀጥታ ሰዎች ኬንያ ውስጥ ተይዞ ወደ ቱርክ ተወስዷል።

አብዱላህ ኦቻላን ቱርክ ውስጥ ክስ ከተመሠረተበት በኋላ በአገር ክህደት ወንጀል ተፈርዶበታል።