
ከ 9 ሰአት በፊት
የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩናይትድን ኪንግደም ገዢ ሌበር ፓርቲ ለካማላ ሃሪስ ድጋፍ በማድረግ ጣልቃ እየገባ ነው ሲሉ ለአሜሪካ የፌደራል ምርጫ ኮሚሽን አቤቱታ አቀረቡ።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ቅሬታቸውን ያቀረቡት በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው ቡድን በኩል ሲሆን የዩኬውን የሰራተኛ ፓርቲ በግልጽ በሚታይ መልኩ በውጭ ጣልቃ ገብነት ከሰውታል።
የቀረበው አቤቱታ በሌበር ፓርቲ እና በዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ መካከል ስላሉ ግንኙነት ሪፖርት የተደረጉ የሚዲያ ዘገባዎችን እንዲሁም ለቅስቀሳ ዘመቻቸው የተደረጉ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ዋቢ አድርጎ ይህ “ህገወጥ” አስተዋጽኦ ነው ሲል ጠቅሷል።
በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉ የሌበር ፓርቲ ተሟጋቾች ይህንኑ የሚያደርጉት ከፓርቲው በተቀመጠላቸው አቅጣጫ ሳይሆን በግላቸው መሆኑን ቢቢሲ ተረድቷል።
በውጭ ጣልቃ ገብነት የተከሰሰው የሌበር ፓርቲ እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።
አቤቱታው ከሌበር ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ለካማላ ሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ለማድረግ ወደ አሜሪካ መጓዛቸውን የጋዜጣ ዘገባን ዋቢ በማድረግ አካቷል።
የሚዲያ ሪፖርቱ “የሌበር ፓርቲ ጣልቃ መግባቱን የሚያሳይ ነው። የሃሪስ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻም ይህንን ህገወጥ የሆነ የውጭ አገር ድጋፍን ተቀብሏል” ሲል አቤቱታው አጣቅሷል።
የአቤቱታ ደብዳቤው በዲሞክራት እና በሌበር ፓርቲዎች መካከል ግንኙነት መደረጉን እንዲሁም በከፍተኛ ባለስልጣናቱ መካከል ምስጢራዊ በሆነ መልኩ መገናኘታቸውን የዋሽንግተን ፓስትን ዘገባ አትቷል።
- የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ሴት ፕሬዝዳንት ለመሆን እየተፎካከሩ ያሉት ካማላ ሃሪስ ማን ናቸው?10 ሀምሌ 2024
- የአነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ የሕይወት ታሪክ – ከሪል ስቴት እስከ ፖለቲካ5 ጥቅምት 2024
- የካማላ ሃሪስ እና የዶናልድ ትራምፕ ወሳኝ የፖሊሲ አቋሞች ምን ይመስላሉ?3 ጥቅምት 2024
በተጨማሪም በሊንክደን የማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ የሌበር ፓርቲ አባል ወደ ‘100 የሚጠጉ’ የአሁን እና የቀድሞ የፓርቲ አባላት ወደ አሜሪካ ምርጫ ወሳኝ ግዛቶች እንደሚጓዙ መጻፋቸው ሰፍሯል። ልጥፉ የተጻፈው በሌበር ፓርቲ የኦፕሬሽን ኃላፊ ሶፊያ ፓቴል ሲሆን ይህም “10 ክፍት ቦታዎች እንዳሉ” እና “ማረፊያዎትን እኛ እንሸፍናለን” ማለታተው ተጠቅሷል። ይህ ልጥፍ በአሁኑ ወቅት ከገጹ ላይ ተነስቷል።
ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2016 የአውስትራሊያ ሌበር ፓርቲ የአሜሪካውን ፓለቲከኛ በርኒ ሳንደርስ የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ለመርዳት ልዑካንን የላከበትን የዓለም አቀፉን ፕሮግራም ሁነት ይኸው አቤቱታ በማነጻጸር አትቷል።
በዚያን ወቅት የአውስትራሊያው ፓርቲ ለልዑካን የበረራ እና ዕለታዊ አበል ከፍሎ ነበር።
በዚህም የተነሳ ፓርቲው እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው ቡድን እያንዳንዳንዳቸው 14 ሺህ 500 ዶላር በፍትሐ ብሄር መዝገብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
የሌበር ፓርቲ ተሟጋቸቾች ወደ አሜሪካ ያደረጉት ጉዞ በፓርቲው የተደራጀ ወይም የገንዘብ ድጋፍ የተደረገበት እንዳልሆነ ከፓርቲው ባለስልጣናት መረዳት ተችሏል።
በአሜሪካ የየፌደራል ምርጫ ኮሚሽን ደንቦች መሰረት የውጭ አገር ዜጎች ካሳ እስካልተከፈላቸው ድረስ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እንደ በጎ ፈቃደኞች ሆነው እንዲያገለግሉ ይፈቀድላቸዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፓርቲ ባለስልጣናት በአሜሪካ ካሉ አቻዎቻቸው ጋር መገናኘታቸው የተለመደ አሰራር ነው ተብሎ ይታመናል።
ቀደም ሲል የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ፓርቲ እና የአሜሪካ ሪፐብሊካን ፓርቲ አመራሮች ጋር ተገናኝተው ነበር።
ቢቢሲ የካማላ ሐሪስን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ቡድን ለቀረበባቸው ክስ አስተያት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።