‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ በኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ የተያዙ መንገዶችን ይዟል።
የምስሉ መግለጫ,‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ በኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ የተያዙ መንገዶችን ይዟል።

23 ጥቅምት 2024

ከደመቀው የሮም ማዕካላዊ የባቡር ጣቢያ በጥቂት ‘ፌርማታዎች’ ርቆ የሚገኝ ስፍራ ነው።

በየዓመቱ ሚሊዮኖች ከሚጎበኙት ታሪካዊው እና የሮም መገለጫ ከሆነው ‘ኮሎስየም’ በ5 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል።

ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠሩ ቅርሶች በቅርብ ርቀት ከበውታል።

አካባቢው ግን ሮም ካላት ጥንታዊነት አንጻር አዲስ የሚባል ነው።

የመኖሪያ ህንጻዎች በብዛት ቢገኙበትም ጥቂት የንግድ ቦታዎችንም ይዟል።

ይህ ስፍራ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ ይባላል። የአፍሪካ ‘ሰፈር’ እንደማለት ነው።

የ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ መንገዶች ጣልያን ‘እግሯን ያስገባችባቸው’ን የአፍሪካ አገራት ከተሞች ስያሜን ይዘዋል።

ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሊቢያ እና ኢትዮጵያ፣ አሥመራ፣ ሞቃዲሾ፣ ትሪፖሊ እና አዲስ አበባ ከመንገዶቹ ስያሜዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ብቻ አይደሉም።

በርካታ መንገዶች ወይም አንስተኛ አደባባይ በኢትዮጵያ ከተሞች ስም ይጠራሉ።

ከሮም በ275 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የፍሎረንስ ከተማ ዕምብርት ላይ ደግሞ ዓድዋ የሚል ስያሜ ያለው አደባባይ ይገኛል። በሌሎችም የጣልያን ከተሞች በኢትዮጵያ ከተሞች የተሰየሙ መንገዶች እንደሚገኙ ይነገራል።

ለመሆኑ በጣልያን አንዳ’ንድ መንገዶች በኢትዮጵያ ከተሞች ስም የሚጠሩት ለምንድን ነው?

ቤንቶ ሙሶሊኒ እና የጣልያን ከተሞች

አሁን ላይ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚታይበት ‘አፍሪካኖ’ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የተመሠረተ ነው።

ያ ጊዜ በጣልያን ከተሞች መስፋፋት የጀመሩበት፣ አዲስ የኪነ ህንጻ ሥራዎች ብቅ ያሉበት ነበር።

ያ ጊዜ ጥንታውያኑ የጣልያን ከተሞች ከአዲስ የግንባታ እሳቤ ጋር እንዲተሳሰሩ ጥረት የተጀመረበት ጊዜ ነበር።

በተመሳሳይ ወቅት ጣልያን ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ልካ ነበር።

ከዓድዋ ድል 39 ዓመታት በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ተነሳች።

‘ታላቅ’ አምባገነን መንግሥት የመሠረተው ቤኒቶ ሙሶሊኒ በአንድ እጁ የጣልያን ከተሞችን እያስፋፋ በሌላኛው በኢትዮጵያ ላይ ጦር አዘመተ።

‘ናሽናል’ ፋሺስት ፓርቲን አቋቁሞ ከአውሮፓውያኑ 1922 እስከ 1943 ጣልያንን የመራው ሙሶሊኒ ሮምን ጨምሮ የጣልያን ከተሞችን የማዘመን ሃሳብ ነበረው።

ይህ ሃሰብ ወደ ተግባር ሲቀየር ‘ከተፈጠሩት’ አከባቢዎች አንዱ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ ነው።

ታዲያ በዚያ ጊዜ ከሞላ ጎድል ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረችው ጣልያን የአካባቢውን መንገዶች በኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ ሰይማለች። የሶማሊያ፣ የሊቢያ እና የኤርትራ ከተሞች ስያሜም በዚህ ሰፈር አለ።

የፋሺስቱን መንግሥት መሪ ሙሶሊኒ ወይም ዱቼ የጣልያን ከተሞች ጥንታዊነታቸውን ሳይለቁ ዘመናዊ እንዲሆኑ ሠርቷል። በአውሮፓውያኑ 2016 ጆናታን ሮም የተባለ የኪነ ህንጻ ጉዳዮች ፀሐፊ፣ ሙሶሊኒ ባደረገው ጥረት የሮምን መልክ ቀይሯል ሲል ጽፏል።

ጨምሮም ዱቼ በዘመናዊው ዓለም ልክ እንደ ጥንቱ የገነነች አገር እንዲኖረው የነበረውን ፍላጎት በኪነ ህንጻዎች እንዲንጸባርቅ እንዳደረገ ያነሳል።

በ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ ከተሰየሙት መካከል፡ ፒያሳ አዲስ አበባ
የምስሉ መግለጫ,በ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ ከተሰየሙት መካከል፡ ‘ፒያሳ’ አዲስ አበባ

ይህንን ፍላጎቱን የሚሳዩ ከእብነ በረድ እና ነሐስ የተዘጋጁ አምስት ግዙፍ ካርታዎችን መሐል ሮም ላይ ሰቆሎም እንደነበር ይጠቅሳል። ከእነዚህ ካርታዎች አምስተኛው የሙሶሊኒን ፍላጎት በማያወላድ መንገድ አስቀምጧል።

ካርታ የሮምን አዳዲስ የቅኝ ግዛት ‘ኢምፓየርን’ ያሳያሉ። ይህ ካርታ ‘በአዲሱ የጣልያን ኢምፓየር’ ውስጥ ጥቂት የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ቱኒዝያ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያን እና ኢትዮጵያን አካቷል።

በአሮፓውያኑ 1911 የቀድሞ የጣልያን መንግሥት በከፊል በሊቢያ የነበረውን ግዛት ዱቼ በ1934 ሙሉ በሙሉ መጠቅለል ችሏል። በ1928 ዓ.ም. ወራት ከፈጀ ውጊያ በኋላ የጣልያን ጦር ኢትዮጵያ ወሯል። በአወሮፓውያኑ 1934 ደግሞ አልቤንያን ይዟል። ከዚህ ውጪ ግን ካርታው ላይ ያለው ‘የጣልያን ኢምፓየር’ ንድፍ መሬት ላይ እውን አልሆነም።

ወደ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ እንመለስ።

የኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ በጣልያን

‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ እንደማንኛው የጣልያን ሰፈር ጎዳናዎች ወይም በጣልያንኛ ‘ቪያሌ’ ፣ ከጎዳና አነስ ያሉ መንገዶች ወይም ‘ቪያ’ እና አንስተኛ አደባባዮች ወይም ‘ፒያሳ’ አሉት። እነዚህ ‘የአፍሪካኖ’ አካሎች ጣልያን በአንድም በሌላም መንገድ በቅኝ ግዛት ይዛቸው ወይም ፍላጎቱ በነበራት አገራት ወይም ከተሞች ተሰይመዋል።

ቪያሌ ኢትዮጵያ፣ ቪያሌ ኤርትራ፣ ቪያሌ ሶማሊያ እና ቪያሌ ሊቢያ በአካባቢው ያሉ ዋነኛ ጎዳናዎች የተሰየሙ ስያሜዎች ናቸው።

ቪያ ዓድዋ፣ ቪያ አሥመራ፣ ቪያ ድሬ ዳዋ፣ ቪያ ምጽዋ፣ ቪያ ትግሬ፣ ቪያ ላጎ ጣና (ጣና ሃይቅ)፣ ቪያ መቀሌ፣ ቪያ ደሴ፣ ቪያ አዲግራት፣ ቪያ ሲዳማ፣ ቪያ እንደርታ፣ ቪያ ተምቤን፣ ቪያ አሸንጌ፣ ቪያ ትሪፖሊ እና ቪያ ቤንጋዜ ደግሞ የ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ መንገዶች ስያሜ ናቸው።

ፒያሳ አዲስ አበባ (አዲስ አበባ አደባባይ እንደማለት)፣ ፒያሳ ጅማ፣ ፒያሳ አምባላጌ እና ፒያሳ ጎንደር በአካባቢው የሚገኙ አንስተኛ አደባባዮች፣ መስቀለኛ መንገዶች ወይም አካፋዮች ከተሰየሙባቸው ስሞች መካከል ናቸው።

በአካባቢው ከእነዚህ ስያሜዎች በተጨማሪ በርካታ የጎዳና፣ የመንገድ ወይም የአደባባይ ስያሜዎች አሉ።

የጣልያኗ መዲና ሮም አካል የሆነው ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ ‘ትሬስቴ’ በሚል ስያሜም ይታወቃል። ስፍራው በከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኝነው።

አካባቢው ከእምስት ፎቅ ያልዘለሉ በርካታ የጋራ መኖሪያ ህንጻዎች በስፋት ይገኙበታል።

ተንቤን መንገድ በጣልያን ሮም
የምስሉ መግለጫ,ተንቤን መንገድ በጣልያን ሮም

ካርሜሎ ክሪሼንቲ “ፋሺስቶች በኢትዮጵያ ብዙ ዓመታት የሚቆዩ መስሏቸው ነበር [መንገዶቹን] በኢትዮጵያ [ከተሞች] ስያሜ የሰየሙት” ይላሉ።

ሮም ተወልደው ያደጉት የ65 ዓመቱ ካርሜሎ ለኢትዮጵያ “ልዩ ፍቅር አለኝ” ሲሉ ይገልጻሉ። ለዚህም ነው ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉት።

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ታሪክ ሲያነቡ በኢትዮጵያ እጅግ እንደተሳቡ ይናገራሉ።

ጣልያን ኢትዮጵያን መረሯን አምርረው የሚያወግዙት ካርሜሎ “ቆይቼ ሳጠና የእኔ ቤተሰቦችም ይሁን ዘመዶች ወደ ኢትዮጵያ ሄደው አለመዋጋታቸውን አውቄያለሁ። ኢትዮጵያውያንን አልገደሉም። በዚያም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ።

ወደ መንገዶቹ ስያሜ ስንመለስ – እንደ ካርሜሉ ገለጻ የእነዚህ መንገዶች ስያሜ መነሻ ለኢትዮጵያ ማስታወሻ እንዲሆን በማሰብ የተደረገ አይደለም።

ይልቅስ፣ በፋሺስቱ መንግሥት እና በሙሶሊኒ ልብ ውስጥ የነበረውን ግዛት የማስፋፋት ፍላጎት የሚያሳዩ ናቸው።

“ያኔ ከተሞችን ያስፋፉ ነበር። አዲስ የሚሠሩ አካባቢዎችን በኢትዮጵያ እና በሌሎች [የጣልያን ቅኝ በነበሩ አገራት] ታዋቂ ከተሞች መሰየም ጀመሩ። አንዳዴም በአውደ ውጊያዎች ስም የሚሰየሙ ነበሩ” የሚሉት ካርሜሎ “መንገዶቹን የጣልያን አዲስ ኢፓየር [ግዛት] ናቸው እየሉ ነው የሰየሙት። በዚህም ፕሮፓጋንዳ እየሠሩ የጣልያን ዜጎች ኩራት እንዲሰማቸው ያደርጉ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

“ስያሜዎቹን ስመለከት ቤቴ ያለሁ ያህል ይሰማኛል”

ካርሜሎ ክሪሼንቲ ሰባት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመላልሰዋል። ከ14 ዓመታት በፊት ወደ ላሊበላ አቅንተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን እምነትን ተቀብለዋል።

ለኢትዮጵያ “ልዩ ፍቅር” ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ ወዳለበት ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ የግድ ካልሆነ ባይሄዱ ይመርጣሉ። ለምን?

“እውነቱን ለመናገር ቦታው የሚሰብ አይደለም። በኮንዶሚኒየሞች የተጨናነቀ ነው። ብዙ አረንጓዴ ቦታ የለውም፣ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ አለ። የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ለማግኘትም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ብዙም አልወደውም” ይላሉ።

እርግጥ ይህንን ሀሳብ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት የኢትዮጵያው ወዳጅ ሞክሼ ካርሜሎ ጆርዳኖም ይጋሩታል።

አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ካርሜሎ ጆርዳኖ
የምስሉ መግለጫ,አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት ካርሜሎ ጆርዳኖ በኢትዮጵያ ከተሞች ወደ ተሰየመው አካባቢ ሲያቀኑ ቤታቸው የመሆን ስሜት አለው ይላሉ።

ልዩነቱ ካርሜሎ ጆርዳኖ፣ አካባቢው ባይስብ እንኳን ወደዚያ ማቅናት ደስ ያሰኛቸዋል። እዚያ ስሄድ “ቤቴ ያለሁ ያህል ይሰማኛል” ይላሉ።

ካርሜሎ ጆርዳኖ በእናታቸው በኩል ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ፣ እስከ 21 ዓመታቸው አዲስ አበባ ኖረዋል። የ70 ዓመቱ አዛውንት ለ48 ዓመታት ጣልያን ኖረዋል።

በደርግ ዘመነ መንግሥት ወደ ጣልያን ሮም መሄድ እንዳለባቸው ሲያውቁ “መርዶ” ሆኖባቸው ነበር።

“እኔ አገሬ ኢትዮጵያ ነው። ምንም እንኳን ጣልያን የአባቴ አገር ቢሆንም ልክ ከአውሮፕላን ወርጄ የሮም ምድርን ስረግጥ እንደሞትኩኝ ነበር የተሰማኝ። በጣም በጣም አዝኜ ነበር። ምክንያቱም ቤተሰቤን፣ እናቴን፣ የተወለድኩበትን ቦታ፣ ጓደኞቼን ጥዬ ነበር የመጣሁት” ሲሉ ያስታውሳሉ።

ታዲያ ከሐዘን እና ድባቴ ስሜት “ትንሽ ለማረፍ” የኢትዮጵያ ከተሞች ስያሜ ያለበት ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ አግዟቸዋል።

ልክ እንደዛሬው ‘ጉግል ማፕስ’ ባልነበረበት ጊዜ አካባቢውን እንዴት አወቁት?

'ፒያሳ' ጅማ
የምስሉ መግለጫ,’ፒያሳ’ ጅማ

የከተማ አውቶብስ እና ባበሩ የሚጠቁሙ የወረቅት ካርታዎች ላይ የኢትዮጵያ እና የከተሟቿን ስያሜ ተመለከቱ።

ሳይውሉ ሳይድሩ ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ን ጎበኙት።

“እንደመጣሁ ሳምንት እንኳን ሳልቆይ ነው ወደዚያ የሄድኩት” ካሉ በኋላ “አሁን ድረስ በዚያ ሳልፍ የቤቴ ያህል ስሜት ይሰማኛል። የአገሬን ከተሞች ስም እዚያ ቦታ ላይ ሳይ አገሬ ያለሁ ዓይነት ስሜት ነው የሚሰማኝ” ሲሉ አክለዋል።

በጣልያን ለመንገዶች ስያሜ መስጠትን የተመለከተ አንድ ብሔራዊ ሕግ የለም። ይህ ሥልጣን ከተሞቹን ለሚያስተዳድሩት ማዘጋጃ ቤቶች እና የከንቲባ ጽህፈት ቤቶች የተሰጠ ነው።

የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ለመንገዶች ስያሜ መስጠት አስፈላጊ ከመሰላቸው የመቀየር ሥልጣናም አላቸው።

በሮም እና በሌሎች የጣልያን ከተሞች የመንገድ እና የቦታ ስያሜዎች ታሪክ በሠሩ ወይም በተለያዩ ጥቃት በተገደሉ ሰዎች ስም ወይም በአካባቢው በነበረው ታሪካዊ ሁነት አሊያም መታሰቢያ በሚገባቸው ከጣልያን ጋር በልዩ ልዩ መንገድ ከተሳሰሩ ሁነቶች እና ስፍራዎች ሊየሰየሙ እንደሚችሉ ተደንግጓል።

በዚህ መነሻ በሮም ሁለት ቦታዎች በአትሌት አበበ ቢቂላ ስም መንገዶች ተሰይመዋል።

የ‘ኳርቴሬ አፍሪካኖ’ መንገዶች ምንም እንኳን በቅኝ ግዛት መንፈስ በኢትዮጵያ ከተሞች ቢሰየሙም እስካሁን በዚያ ስም መቀጠሉን ሁለቱ ካርሜሎዎች በመልካም ይመለከቱታል።

በአካባቢው የኢትዮጵያ ስሞች መኖራቸው “አሁን ያለው ትውልድ ያለፈውን መጥፎ ጊዜ እንዲያስታውስ ጥሩ ነው። ወጣቶች ባለፈው ጊዜ ምን ተከናውኖ ነበር የሚለውን ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ጣልያን ኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችውን ወንጀል ለማስታወስ በጣም ጥሩ ማስታወሻ ነው” ይላሉ ካርሜሎ ክሪሼንቲ።

ካርሜሎ ክሪሼንቲ
የምስሉ መግለጫ,ካርሜሎ ክሪሼንቲ

ቀጥለው “ይህ ቦታ ማስታወሻ ሆኖ መቆየት አለበት። መጥፋት የለበትም። ስሙ ከጠፋ እና ከተቀየረ ታሪክ እንደተፋቀ ነው የምቆጥረው” ሲሉ አክለዋል።

ካርሜሎ ጆርዳኖ ደግሞ “እርግጥ ወረራ በተፈጸመበት መጥፎ ጊዜ ነው የተሰየሙት። ነገር ግን ታሪክ አይቆምም ከፋሺስት ዘመን በኋላ እነዚህ መንገዶች የጥላቻ ሳይሆኑ የወዳጅነት። የማስታወሻ ናቸው” ብለዋል።

በተመሳሳይ እሳቤ “ፋሺስቱ መንግሥት” በሌሎች አካባቢዎችም በተለይ ዓድዋ የሚለውን ስም ለመንገዶች እና ለአደባባዮች እንደተጠቀመባቸው ካርሜሎ ክርሺንቶ ያነሳሉ።

“በሙሶሊኒ ጊዜ ‘ተበቀልናቸው’ ለማለት፣ አድዋን በተለያዩ ቦታዎች ለስያሜ ተጠቅመውታል። ኩራትን ለማሳየት የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ ነበር። ለዚህ ነው በበርካታ ከተሞች በዓድዋ ወይም በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ስም የሚሰየሙት” ሲሉ ገልጸዋል።

በጣልያን ሌላኛው ከተማ የሚገኘው በዓድዋ ስም የተሰየመው አደባባይ
የምስሉ መግለጫ,በጣልያን ሌላኛው ከተማ የሚገኘው በዓድዋ ስም የተሰየመው አደባባይ

እርግጥ ነው በሌላኛዋ የጣልያን ታሪካዊት ከተማ ፍሎረንስ በከተማው እና በባቡር ጣቢያው ማዕከላዊ ስፍራ በዓድዋ የተሰየመ አደባባይ ይገኛል። ምክንያቱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደበዘዘ የመጣ ይመስላል።

ወደ ስፍራው ባቀናንበት ወቅት የአደባባዩ ስያሜ ካረፈበት ጽሁፍ ስር አንድ በግምት በ50ዎቹ መጀመሪያ የሚገኝ ጣልያናዊ ሞተረኛ አገኘን።

ሰላምታ ተለዋወጥን።

“ይኼ አደባባይ ምንድን ነው የሚባለው?” ስንል ጠየቅን።

“ዓድዋ ነው የሚባለው” ወደ ጽሁፉ እየጠቆመ አሳየን።

“ዓድዋ ምንም ማለት ነው?”

“በደምብ አላውቀም፤ ነገር ግን የሆነ ታሪክ የሠራ ሰው ስም ይሆናል። ብዙ ቦታዎች እንዲዚያ ነው የሚሰየሙት” አለን።