እስር ቤት

ከ 5 ሰአት በፊት

ትክክለኛ አድራሻው ባልታወቁ ቦታዎች በግዳጅ ከቀናት እስከ ወራት ለቆየ ጊዜ ተሰውረው በእስር ላይ ከቆዩ ሰዎች መካከል ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኢሰመኮ ከ2015 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ጀምሮ “በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ” ከ52 በላይ ሰዎችን የተመለከቱ አቤታዎችን መመርመሩን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው ረቡዕ ጥቅምት 13፤ 2017 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

የመንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም መግለጫ መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎችን የሚመለከት ነው።

ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው ተጎጂዎች “በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎች እና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለሰቡ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የህግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ የተያዙ” መሆናቸውን አመላክቷል።

ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ በተካሄደው 57ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ኢሰመኮ “የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች መስፋፋት [እና] አሳሳቢነት መቀጠልን” አስመልክቶ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ማቅረቡን አስታውሷል።

ኢሰመኮ የዛሬውን መግለጫ እስካወጣበት ቀን ድረስ “ባልታወቀ ቦታ ከታሰሩት ከ52 በላይ ሰዎች” መካከል፤ “44 ሰዎች ከ1 እስከ 9 ወር በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን” ጠቁሟል።

ተቋሙ አክሎም፤ “ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ በተራዘመ እስር፣ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች፣ ብሎም በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ የቀጠለ” መሆኑን ገልጿል።

ኢሰመኮ በመግለጫው “[ታሳሪዎቹ] በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው የነበሩ፣ እንዲሁም ለየብቻቸው ተለይተው ተይዘው የቆዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ” ብሏል።

ተጎጂዎች ከእስር ሲለቀቁም፤ “በምሽት ዐይናቸው ተሸፍኖ በተሽከርካሪ ከተጫኑ በኋላ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እንዲወርዱ” መደረጋቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ተጎጂዎቹ “ለመጓጓዣ በሚል ከ300 እስከ 1000 ብር እንደተሰጣቸው” አክሏል።

ኮሚሽኑ የታሳሪዎችን ድህረ እስር ሁኔታ “ሁሉም ተጎጂዎች በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ መድረሱን እና በሥጋት መኖራቸውን ያስረዳሉ” ሲል አብራርቷል።

ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫ በእስር ላይ ቆይተው ከተለቀቁ ሰዎች መካከል “የያዟቸው ሰዎች ገንዘብ ከፍለው ሊለቀቁ የሚችሉ መሆናቸውን የገለጹ እና አንዳንዶቹም በቤተሰብ አማካኝነት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠር ብር የከፈሉ መሆኑን” ጠቁሟል።

ለኮሚሽኑ ቃላቸውን የሰጡ አንድ ተጎጂ፤ “እንለቅሃለን ስላሉኝ መርማሪ የነበረው የሻለቃ ማዕረግ ያለው ሰው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ከቤተሰቤ ተቀብሏል” ብለዋል።

ሆኖም ግን ግለሰቡ ከገንዘቡ መከፈል በኋላ ሳይለቀቁ መቅረታቸውን የኮሚሽኑ መግለጫ ላይ ተገልጿል።

የጀነራል ማዕረግ እንዳላቸው የተገለጸ ሌላው ሰው ደግሞ “በቦታው በእስር ከነበሩ መካከል በተመሳሳይ መንገድ ገንዘብ የከፈሉ ሰዎችን ቃል ከተቀበሉ በኋላ” መለቀቃቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቅሷል። የተለቀቁት ግለሰቦች “ ከ“ፋኖ” ጋር ትብብር እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ” እንደተሰጣቸውም ኮሚሽኑ አክሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ይህ ክስተት “የጉዳዩን አሳሳቢነት እና አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድበት የሚገባ መሆኑን በተጨማሪ የሚያጠናክር ነው” ሲል በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።

ተቋሙ በመግለጫው ላይ በሰጠው ምክረ ሃሳብ፤ “ያሉበት ቦታ በማይታወቅ፣ ብሎም የአስገድዶ መሰወርን ሊያቋቁም በሚችል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን በተመለከተ የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ አካላት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል” ብሏል።

በተጨማሪም “ሰዎችን የመያዝ እና በእስር የማቆየት ሥልጣን በሕግ ያልተሰጣቸው ተቋማት ወይም መደበኛ ያልሆኑ መዋቅሮች (ad hoc structures) እና ይህንን ተግባር በሚፈጽሙ አባላት ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና በአፋጣኝ ሊቆም የሚገባ ነው” ሲል አሳስቧል።

ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የዜጎች አስገድዶ መሰወር፣ ተጠርጣሪዎችን በጭካኔ፣ በአዋራጅ እና ኢሰብዓዊ በሆነ መልኩ አያያዝ መጨመሩን መግለጹ ይታወሳል።