ኤልያስ ተገኝ

October 23, 2024

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በ30 ሚሊዮን ዶላር መነሻ ካፒታል፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች 100 የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎች የማቋቋም ኢንቨስትመንት ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የመንግሥት ስትራቴጂካዊ የኢንቨስትመንት ተቋም ሆኖ እንዲያገለግል በ100 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የኢንቨስትመንት ስትራቴጂውን ዕውን ለማድረግ አጋር ይሆናል ከተባለው ዶዳይ የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት አምራች ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ተፈራርሟል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌት የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎች የማቋቋም ኢንቨስትመንት “ስትራክቸር” ሒደቱ እየተከናወነ ቢሆንም እስካሁን አልተጠናቀቀም፡፡

በመግባቢያ ስምምነት ሰነዱ ላይ በተቀመጠው መሠረት ኢንቨስትመንቱ 30 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ካፒታል ሲኖረው፣ በ100 የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎች እንደሚኖሩ ታሳቢ ያደርጋል ያሉት ብሩክ (ዶ/ር)፣ ሌሎች ቀሪ ጉዳዮችን መንግሥት ከኩባንያው ጋር የሽርክና ስምምነት (Shareholder Agreement) ሲፈራረም ይታያሉ ብለዋል፡፡

ለባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎች ኢንቨስትመንት ዶዳይ ኩባንያ የራሱን ኢንቨስትመንት ካፒታል ይዞ የሚቀርብ መሆኑን፣ ‹‹ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በበኩሉ የሚያደርገው አስተዋጽኦ የኢክዩቲ፣ የዓይነት አስተዋጽኦ (Kind Contribution) ወይስ ፍሪ ኮንትሪብዩሽን ነው የሚለው በቀጣይ በሚደረግ ድርድርና ስምምነት የሚታወቅ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹እኛ የተግባባነው ዋና ነገር ኢንቨስትመንቱን አብረን መሥራት እንፈልጋለን፣ ለመነሻ 30 ሚሊዮን ዶላር ስለሚያስፈልግ እሱን እናመነጫለን፣ 100 ያህል ቦታዎች ያስፈልጋሉ፣ እኛም ባሉን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች መጠቀም እንችላለን፣ በእነዚህ ላይ ተመሥርተን ነው መስማማት ላይ የደረስነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ያስረዱት ብሩክ (ዶ/ር)፣ በቀጣይ የሚፋጠነው ሥራ የኢክዩቲ አስተዋጽኦ ካለ ምን ያህል? በመቶኛስ የሚያስገኘው የኢንቨስትመንት ትርፍ መጠን ምን ይመስላል? የሚለውን መለየት ይሆናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎችና የሞተር ብስክሌቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ የጀመረው ዶዳይ ኩባንያ፣ እስካሁን 1,000 የኤሌክትሪክ ሞተር ብስክሌቶችን መሸጡን፣ በተያዘው የበጀት ዓመት ይህንን አኃዝ ወደ 10,000 እንደሚያሳድገው ተገልጿል።

ዶዳይ ኩባንያና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባደረጉት የኢንቨስትመንት መግባቢያ ስምምነት መሠረት በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ 100 የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎች ከመክፈት ባሻገር፣ በቀጣዮች ሦስት ዓመታት ሸገር ከተማን ጨምሮ 300 ጣቢያዎች በተለያዩ ቦታዎች ለመክፈት ዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ  ዘላቂና አመቺ የትራንስፖርት  አገልግሎት ለመዘርጋት ያለመ ነው የተባለው ይህ ኢንቨስትመንት የካርቦን ልቀት መጠንን በመቀነስና የከተማ እንቅስቃሴን በማሳደግ፣ ለአንድ መቶ ሺሕ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር ባለፈው የበጀት ዓመት በነዳጅ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ማገዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የሞተር ብስክሌቶችም ሆኑ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል መባሉ አይዘነጋም፡፡