
October 23, 2024

የጃፓኑ ቶዮ ሶላርና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲፈራረሙ
የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፓነሎች በማምረት የሚታወቀው የጃፓኑ ኩባንያ ቶዮ ሶላር (Toyo Solar) በቬትናም የሚገኘውን ፋብሪካውን ወደ ኢትዮጵያ ለማዛወር በዝግጅት ላይ መሆኑን ገለጸ።
ቶዮ ሶላር የመጀመሪያውን 2 ጊጋ ዋት የፀሐይ ፓናሎች ማምረቻ ፋብሪካ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማቋቋም የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እና የቶዮ ኩባንያ ኃላፊ ናቸው።
ኩባንያው ከፀሐይ ኃይል አመንጪ ፓናሎችና መሰል ምርቶችን ለማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ በኢትዮጵያ ሀዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ ውስጥ ለመገንባትም የ31,500 ካሬ ሜትር ሊዝ ውል መፈጸሙ ታውቋል። ኩባንያው ፋብሪካውን ለመገንባት 60 ሚሊዮን ዶላር (ወደ 7 ቢሊየን ብር የሚጠጋ) ወጪ የመደበ ሲሆን ይህንንም ከራሱ ውስጣዊ ሀብቶች በቅድመ ክፍያ እንደሚሸፈን አስታውቋል።
የተመረጠው ቦታ የማዘመንና የፀሐይ ፓናሎችና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉ የኩባንያው መረጃ ያመለክታል።
ኩባንያው በሐዋሳ ኢንደስትሪ ፓርክ በተረከበው ቦታ ላይ ማምረቻዎችን በኅዳር 2017 ዓ.ም. መትከል እንደሚጀምርና በመጨረሻው ሩብ ዓመት ደግሞ ፋብሪካውን ሥራ በማስጀመር የፀሐይ ፓናሎችን ማምረት እንደሚጀምር አስታውቋል። ቶዮ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በማኑፋክቸሪንግና ምህንድስና ለሠለጠኑ እስከ 880 ለሚደርሱ ሠራተኟት የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም አስታውቋል።
ለቶዮ ኩባንያ የንግድ መስፋፋት ኢትዮጵያ ስትራቴጅክ መሆኗን የገለጸው ኩባንያው፣ አገሪቱ በአሜሪካ መንግሥት ከታሪፍ ነፃ የገበያ ዕድል ያላት በመሆኑ እንደመረጣትም አስታውቋል።
እ.ኤ.አ. በ1974 በአሜሪካ የንግድ ሕግ ክፍል 201 መሠረት ኢትዮጵያ ለሁለትዮሽ የሶላር ህዋሶች ከታሪፍ ነፃ መብት ማግኘቷን የጠቀሰው ኩባንያው ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የውኃ ኃይል ሀብት ባለፀጋ በመሆኗ እንደመረጣት አስታውቋል።
የቶዮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጁንሴይ ሪዩ እንዳሉት ‹‹ይህን የማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለማቋቋም መወሰናችን የአቅርቦት ሰንሰለታችንን ለማብዛትና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የፀሐይ ኃይል አመንጪ ምርቶችን የማምረት አቅማችንን ለማሳደግ በስትራቴጂክ ራዕያችን ውስጥ ቁልፍ እርምጃ ነው። በግምት 90 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከውኃ ኃይል ሲሆን፣ የነፋስ ኃይል 8 በመቶ፣ የተቀረው 2 በመቶ ደግሞ ከጂኦተርማል (የሙቀት) ኃይል የሚገኝ ነው፤›› ብለዋል።
‹‹በኢትዮጵያ የታቀደው ፋብሪካ የማምረት አቅማችንንና ውጤታማነታችንን ያሳድጋል፣ ወጪን ይቀንሳል። እንዲሁም ለገበያ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንድንሰጥ ያስችለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ኩባንያችን ቶዮ ተወዳዳሪና በታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ ቁልፍ ተዋናይ እንዲሆን ያደርገዋል፤›› ብለዋል።
ቶዮ በቬትናም የሚገኘውን የማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካውን ወደ ኢትዮጵያ ለማዘዋወር ያቀደው የአሜሪካ መንግሥት የፀሐይ ኃይል አመንጪ ምርቶችን ወደ አሜሪካ በሚልኩ አራት የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ላይ፣ ቬትናምን ጨምሮ አዲስ ታሪፍ ለመጣል በማቀዱ ነው።