
ዜና ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የገዥውን ፓርቲ የስህተት መንገድ ማስቆም እንዳለበት የንጋት ኮከብ…
ቀን: October 23, 2024
ስማቸው ለጊዜው በአደባባይ እንዲገለጽ በማይፈልጉ በዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በለቀቁ ነባር ፖለቲከኞች በምሥረታ ሒደት ላይ የሚገኘው የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ (ንጋት ኮከብ ኢትዮጵያ)፣ ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የገዥውን ፓርቲ (ብልፅግና) የስህተት መንገድ በሰላማዊ መንገድ ታግሎ እንዲያስቆም ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለግል ሀብታቸው ዋስትና ያጡባት፣ ኢንቨስተሮች የሚሸሹባት፣ መንግሥታዊ ሽብር በመስፋፋቱ ሰላም የሌለባት፣ ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ተስፋ ቆርጦ ጥቂቶች ለጊዜው የሚፈነጩባትና ዘመነ መሣፍንትን ለመመለስ በቋፍ ላይ እንደምትገኝ የገለጸው ፓርቲው፣ ለሪፖርተር በላከው የቅድመ ምሥረታ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን በማደራጀት የግሉንና የአገሩን ህልውና ማስቀጠል ግዴታ የሆነበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ የገለጸው ፓርቲው፣ ‹‹ብልፅግና ፓርቲ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ስብስብ ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶች በማራቅ በጋራ በመቆም ሊታገለው ይገባል፤›› ብሏል፡፡
ለዚህም እውነተኛ የሲቪል ማኅበራት፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተባበርና በመከባበር ለጋራ ህልውናና ለትውልዱ ቀጣይነት በጋራ እንዲቆሙ ፓርቲው ጥሪ አስተላልፏል፡፡
አገሪቱ ከተጋረጠባት ብሔራዊ አደጋ እንድትወጣ ዜጎች በአጠቃላይ ከንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ ጎን እንዲቆሙና በጋራ እንዲሠሩ የትግል ጥሪ ማቅረቡን በመግለጫው ተገልጿል፡፡
የፈረሰው የኢሕአዴግ አገዛዝ ድክመቶች ካስከተሉት ያደሩ ችግሮች በተጨማሪ፣ ብልፅግና በሚፈለፍላቸው ችግሮች የተነሳ፣ ኢኮኖሚው ከቀን ወደ ቀን እየተዳከመ በመምጣቱ፣ ዜጎች ሠርተው ለመለወጥ ሕልም እንደሆነባቸውና የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸውን ፓርቲው በመግለጫው ዘርዝሯል፡፡
ገዥው ፓርቲ ወጥ የሆነ ዕቅድና የተጠና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሌለው በመሆኑ፣ በተለያዩ ጊዜያት እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች ዘለቄታዊ መፍትሔ አለመሆናቸውን፣ ለጊዜያዊ የፓሮፓጋንዳ ፍጆታ ብቻ የሚውሉ ብልጭልጭ ድርጊቶች መሆናቸውን ፓርቲው ገልጿል፡፡
የገዥው ፓርቲ ድርጊቶችና አካሄዶች ኢትዮጵያን ተመልሳ ለመነሳት በሚያስቸግር አርንቋ ውስጥ እንድትዘፈቅ ምክንያት ሆነዋል ሲልም ፓርቲው አስታውቋል፡፡
በብልፅግና ዲፕሎማሲያዊ ስህተቶች ኢትዮጵያ በጎረቤቶቿ የተገለለች፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ በንቀትና በጥርጣሬ የሚመለከታት፣ ታሪካዊ ጠላቶቿ ከጎረቤት መንግሥታት ጋር በመሆን ካራ እየሳሉባት ያለ ቀጣና ውስጥ ትገኛለች ያለው የፓርቲው መግለጫ፣ በዲፕሎማሲም ሆነ በኢኮኖሚ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ማኅረበሰቡ የነበራት ሚና እየደበዘዘና ተሰሚነቷ በፍጥነት እየተሸረሸረ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዚህ ወቅት ዜጎች በማንነታቸው ብቻ የሚገደሉበት፣ የሚሰደዱበትና የሚታሰሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ ህልውናቸውን ለማስቀጠል የደም መስዋዕትነት እየገበሩ የሚገኙበት ትግል ውስጥ በመሆናቸው፣ ኢትዮጵያ የበለጠ አደጋ ውስጥ እንደወደቀች ፓርቲው አስታውቋል፡፡
ገዥው ፓርቲ በሰላማዊ ትግል መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ‹‹የአገራችን ሰላማዊ ትግል አብቅቶለታል›› ብለው የሚያምኑ ዜጎች ቢኖሩም፣ ሰላማዊ ትግል አስፈላጊ መሆኑንና የሚከፈለውን መስዋዕትነት ተከፍሎ በማስቀጠል እንደሚያምን ፓርቲው ገልጿል፡፡
በዚህም ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለውን ዋጋ በመቀበል፣ የሰላማዊ ትግል አስተባባሪና ተባባሪ በመሆን፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሆን የፖለቲካ ሥርዓት ለማምጣት በጊዜያዊነት ‹‹የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ አገራዊ ፓርቲ ለማቋቋም ኢትዮጵያውያንን ለማሰባሰብ መወሰኑን ገልጿል፡፡
ፓርቲው በቀጣይ ጊዜያት ጠቅላላ ጉባዔ በማዘጋጀት አቋሞቹንና የትግል አቅጣጫውን ለጉባዔ ተሳታፊዎች ግልጽ በማድረግና በማፀደቅ በሚያደርገው ጥረት፣ በአባልነት በመመዝገብና ሁለገብ ዕገዛ በማድረግ፣ ለሁሉም ዜጎች የምትሆን ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከኢዜማ በተለያዩ ምክንያቶች የለቀቁ ከፍተኛ አመራሮች አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ አቶ ሀብታሙ ኪታባ፣ አቶ ተክሌ በቀለ፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ ወ/ሮ ናንሲ ውድነህ፣ አቶ የጁአልጋው ጀመረ፣ አቶ ኑሪ ሙደሲርና አቶ አንዱዓለም አራጌ መሆናቸው ይታወቃል፡፡