የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ

ዜና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሽግግር ፍትሕ ማስረጃነት ያቆያቸውን  ምርኮኞች መልቀቁን ተናገረ

ናርዶስ ዮሴፍ

ቀን: October 23, 2024

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከእስር የለቀቃቸውን ከ400 በላይ ምርኮኛ ወታደሮችን ለመፍታት የተገደደው፣ በትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባል የሆኑና ጦርነቱን ተከትሎ እስር ላይ የነበሩ ወታደሮች ሕይወት ላይ የተደቀነ ሥጋት ስለነበረ መሆኑን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያስታወቁት እሑድ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ጋር በቪድዮ ባደረጉት ለሦስት ሰዓታት ያህል ቆይታ በነበረው ውይይት ላይ ነው።

አቶ ጌታቸው ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተፈቱ ምርኮኞችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ላይ፣ ከ400 በላይ የሚሆኑ ምርኮኛ ወታደሮችን የመፍታት ስምምነቱ ከመፈጸሙ በፊት፣ በርካታ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የኤርትራ ሠራዊት አባል የሆኑ ምርኮኛ ወታደሮችን መልቀቃቸውን አንስተው፣ ከስምምነቱ በኋላ ከፍተኛ መኮንኖችን ጨምሮ 447 ወታደሮች እንደቀሩና በተደጋጋሚ ከፌዴራል መንግሥት በቀረበው ጥያቄ መሠረት ሕግን ማዕከል ባደረገ መልኩ መልቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡  

ፕሬዚዳንቱ በገለጻቸው ‹‹የፌዴራል መንግሥት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦልን ነበር፡፡ እኛ ግን አልተቀበልነውም ነበር፡፡ ምክንያቱም የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅት እንደ ማስረጃ ስለምንጠቀምባቸው ነው፤›› ብለዋል።

ይሁንና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ዓላማ በተቃርኖ የሚቆም ውሳኔ ያስፈጸሙበትን ምክንያት ሲያስረዱም ‹‹ሰላም እንዲመጣ ከፈለጋችሁ እንዲሁም የእናንተን ወታደሮች እንድንለቅላችሁ ከፈለጋችሁ የያዛችኋቸውን ልቀቁ ተባልን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት አባል የሆኑና ጦርነቱን ተከትሎ እስር ላይ የነበሩ ወታደሮች ለሞት እንዳይዳረጉም ሥጋት ስለነበረን፣ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ ጄኔራል ታደሰ ወረደ እንዲሁም ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሣኤ ባሉበት በጋራ ነው እንዲለቀቁ የወሰንነው፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ለሽግግር ጊዜ ፍትሕ ወቅት የሚሆን ማስረጃ ማሰባሰብን በተመለከተ ‹‹በእኔ እምነት በጣም ብዙ ማስረጃዎችን ሰብስበናል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የወንጀል ጉዳይ የፌዴራሉን መንግሥት ነው የሚመለከተው፡፡ ይህን እውነታ መጋፈጥ ያስፈልጋል›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡  

በተለያዩ ክልላዊ ጉዳዩች ላይ ትኩረቱን ባደረገው የፕሬዚዳንቱና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ውይይት ወቅት፣ የምሁራን ስደት ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል ይገኝበታል።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተረጋጋና አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ባለመቻሉ የሰሜኑን ጦርነት ከቋጨው የፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ 400 የሕክምና ባለሙያዎች አገር ጥለው መሰደዳቸው ተገልጿል።

አቶ ጌታቸው ‹‹በክልሉ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ምላሽ መስጠት አዳጋች በመሆኑ የተማሩ ወጣቶች ተስፋ እያጡ ነው፡፡ የተረጋጋና አስተማማኝ ሁኔታን ባለመፍጠራችን፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ 400 የሕክምና ባለሙያዎች  ከአገር ወጥተዋል፡፡ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሄደዋል ቢባል ጥሩ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ወደ ሌሎች አጎራባች አገሮች፣ ሲልም የከፋ ሁኔታ ላይ ወደሚገኙ አገሮች ጭምር ባህር አቋርጠው እየሄዱ ነው፤›› ብለዋል።

በተጨማሪም ‹‹በውስጣችን የተፈጠረው ችግር፣ ያሉንን ጥቂት ምሁራን ወደ ውጭ እየገፋናቸው ነው፡፡ ትግራይም ከእነሱ እንዳትጠቀም ሆናለች፡፡ ይህ የሆነው የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮች ያሉበት ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ‹መንግሥትም መንግሥት ሆኖ እንዲሠራ፣ ፓርቲም በፓርቲ ሥራ ላይ ብቻ እንዲሰማራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡› ያሉ ሲሆን፣ ነገር ግን በአሁን ወቅት ያለው ሁኔታ ይህ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

የሕክምና ባለሙያዎችን ስደት በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የመቀሌ አይደር ሪፈራል ሆስፒታልና የጤና ኮሌጅ ባለሙያ፣ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ የሕክምና ባለሙያዎች ስደት እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና የሕክምና ተቋሙ የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በየቀኑ የሠራተኞች ስንብት ማሳወቂያ በመለጠፍ እንደሚያሳልፍ ገልጸው፣ ለዚህ ፍልሰት መነሻ ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጠዋል።

በቀዳሚነት ያነሱትም የሕክምና ባለሙያዎቹ በጦርነት ጊዜ ያሳለፉት፣ በአገልግሎት ቆይታቸው የተመለከቷቸው አሰቃቂ ሁኔታዎች ከፍተኛ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ያደረሰባቸውና በሥራቸው ላይ ከመቆየት መሰደድን የመረጡ ብዙዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

አስከትለውም በክልሉ የነበረው የተራዘመ የጦርነት ሒደት ከግንዛቤ በማስገባት አሁን ላይ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ አስተማማኝ ያልሆነላቸው ባለሙያዎችም መልቀቃቸውን አንስተዋል።

በሌላ በኩል ‹‹ብዙዎቹ ዶክተሮች በኪራይ ቤት ነበር የሚኖሩት። በጦርነቱ ወቅት ያልተከፈላቸው የ17 ወራት ደመወዝ ሲመጣ ይከፈላል በሚል በዕዳ ነበር የሠሩት፡፡ ነገር ግን ደመወዙ እስካሁን አልተከፈለም። ከስምምነቱ በኋላ አከራዮች ገንዘባቸውን እንዲሰጡ ያቀርቡት የነበረው ጥያቄ የተሻለ የገንዘብ ምንጭ አማራጭ እንዲፈልጉ የገፋቸው ብዙዎች ተሰደዋል፤›› ብለዋል።

ሆስፒታሉ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ሥር የሚተዳደር በመሆኑ በጀት የሚመደብለት ከፌዴራል መንግሥት እንደሆነ ገልጸው፣ ነገር ግን ‹‹ለአንድ ዓመት የምግብ በጀት ተብሎ የተሰጠው ገንዘብ ለአንድ ወር የማይበቃን ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል።

የበጀት እጥረቱ ለዶክተሮችና የሕክምና ባለሙያዎች የሚከፈሉ የደመወዝና የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ይህም ሥራቸውን እንዲለቁ እያደረጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሕክምና ባለሙያዎች ስደት ከሪፈራል ሆስፒታሉ ባሻገር በጤና ሳይንስ ኮሌጁ የትምህርት አሰጣጥ ሒደት ላይም ጫና መፍጠሩ ተገልጿል።