የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር)

ዜና በጦርነት ሳቢያ ሥራ ያቆሙ መምህራንን ማዘዋወር ካልተቻለ ባሉበት ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው ጥያቄ ቀረበ

ሲሳይ ሳህሉ

ቀን: October 23, 2024

ግጭቶችና  ጦርነቶች ባሉባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች ማስተማር ያልቻሉ መምህራንን ቢቻል ወደ ሌሎች ሥፍራዎች ማዘዋወር፣ ካልተቻለ ደግሞ ሰላም ሰፍኖ ወደ ሥራቸው እስኪመለሱ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጥያቄ አቀረበ፡፡

መምህራን ለማስተማር ትምህርት ቤት ሲሄዱ አደጋ እንደሚደርሰባቸው፣ አደጋውን ፈርተው ሥራ ሲያቆሙ ደግሞ ካልሠራችሁ ተብለው ደመወዛቸው እንደሚቆረጥባቸው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር 37ኛ መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔውን ከጥቅምት 7 እስከ ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ በአዳማ ከተማ ያካሄደ ሲሆን፣ መምህራንን እያጋጠሙ ያሉ መጠነ ሰፊ ችግሮች እንዲፈቱ የመምህራን ተወካዮች ማሰባሰባቸውን በጉባዔው የተሳተፉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ባወጣው መግለጫ፣ መምህራን የኑሮ ውድነት በከፍተኛ መጠን እየፈተናቸው መሆኑን፣ የረዥም ጊዜ አገልግሎት ያላቸው መምህራን የደረጃ ዕድገት ወይም ዕርከን እያገኙ አለመሆናቸውን፣ በአንዳንድ ክልሎች የመምህራን ደመወዝ በጊዜ አለመከፈልና በፐርሰንት መቆራረጥ፣ ያለ መምህራን ፈቃድ በተለያዩ ምክንያቶች የደመወዝ መቆረጥና ይህንን ድርጊት የሚቃወሙትን ደግሞ ማዋከብና ማንገላታት እንዳለ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ከዓመታት በፊት የተጀመረው የመምህራን የመኖሪያ ቤትና የመሥሪያ ቦታ በሚፈለገው ፍጥነት እየተከናወነ አለመሆኑን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ደግሞ ጭራሽ አለመጀመሩን፣ በትርፍ ሰዓት ክፍያ ላይ ተደራራቢ ግብር መቆረጥ፣ የመጻሕፍትና ሌሎች ግብዓቶች እጥረት፣ የክረምት መምህራን ሥልጠናና ያጋጠሙ ችግሮች በመግለጫው ተዳሰዋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ (ዶ/ር) ለሪፖርተር፣ ‹‹ማኅበሩ እንደ አገር ሰላም እንዲመጣ ይፈልጋል፣ ለዚህም ጥረት ያደርጋል፡፡ መምህራን ደግሞ ክፍል ውስጥ ገብተው እንዲያስተምሩ ይፈለጋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ ባልቻሉበት ወቅት አላሰተማሩም ተብሎ ደመወዛቸው ሊቆረጥባቸው አይገባም፤›› ብለዋል።

ከወራት በፊት የ18 ወራት ውዝፍ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ለችግር መጋለጣቸውን የትግራይ ክልል መምህራን መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት በአጠቃላይ የመንግሥት ሥራ በመቋረጡ መምህራን አላስተማሩም፣ ባለመስተማራቸው አይከፈልም የሚል ክርክር መምጣቱን የተናገሩት ፕሬዚዳቱ፣ ‹‹እኛ እያል ያለነው አዎ አላስተማሩም፣ ነገር ግን ሁኔታው ስላልፈቀደላቸው እንጂ አናስተምርም ብለው ባለመሆኑ ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው የነበረውን ችግር እየተነጋገርንበት ነው፤›› ብለዋል። በዚህም በቅርቡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአምስት ወራት እንደሚከፍል ቢናገርም፣ የቀሪው የአንድ ዓመት ውዝፍ ክፍያ ግን አሁንም መፍትሔ እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በቀጠለው ጦርነት እስከ መስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በክልሉ መመዝገብ የተቻለው በ89 በመቶ ወረዳዎች፣ 55 በመቶ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች 2.2 ሚሊዮን ተማሪዎችን ብቻ መሆኑን የክልሉ የትምህርት ቢሮ    ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ከፍተኛ የተማሪ ቁጥር እንዳላቸው በሚታመንባቸው ሰሜን፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች፣ ደቡብ ጎንደር ዞንና ከፊል አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የተማሪ ምዝገባው ዝቅተኛ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን በሰሜን፣ ምዕራብና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ደግሞ 10 በመቶ እንኳ ምዝገባ ማካሄድ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

በበርካታ አካባቢዎች ትምህርት ያልተጀመረ በመሆኑ ሰባት ሚሊዮን ተማሪዎች ለመመዝገብ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ሁለት ሚሊዮን ብቻ ሲመዘገቡ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉት እስካሁን ወደ ትምርት ቤት አለመመለሳቸውን ክልሉ አስታውቋል፡፡ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ባለመመለሳቸው በርካታ መምህራንም አልተመለሱም ተብሏል፡፡

‹‹እነዚህ መምህራን ልጆች ያሏቸው በመሆናቸው ሠርተው ቤተሰብ ማስተዳደር አለባቸው፡፡ ስለዚህ ባሉበት አካባቢ መሥራት ካልቻሉ መሥራት ወደ የሚችሉባቸው አካባቢዎች እንዲዘዋወሩ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፤›› ሲሉ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል። መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የመምህራኑን ችግር ሊረዱና መፍትሔ ሊሰጡት ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚንዳቱ በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተዛውረው እንዲሠሩ ሲደረግ እንደነበር አውስተው፣ ማኅበሩ አሁንም የሚጠብቀው በታችኛው ደረጃ ያሉ መምህራን ተንቀሳቅሰው ማስተማር የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡ አክለውም ‹‹ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት መምጣት አለባቸው፣ መምህራንም ሚናቸውን እንዲወጡ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ሁኔታው ባልተመቻቸበት ለመምህራን ደመወዝ አይከፈልም ከተባለ እኛ አንስማማም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎች ክልሎች እስከ ሦስት ወራት ደመወዝ ያልተለከፈላቸው በተለይም በቀድሞው ደቡብ ክልል ውስጥ የነበሩ ትምህርት ተቋማትም እንደሚገኙ የገለጹት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል በሚካሄደው ጦርነት ደመወዝ ያልተከፈላቸውና ሥራ ያቆሙ መምህራን መረጃ ተጠናቅሮ አልደረሰም ብለዋል።

በአዳማ በነበረው የመምህራን ማኅበር ጉባዔ በቅርቡ ለመንግሥት ሠራተኞች ተብሎ በወጣው ሰነድ የታየው የደመወዝ ጭማሪ፣ በጣም ዝቅተኛና የመምህራንን ችግርና ጥያቄ የሚመልስ አለመሆኑን  አስተያየት እንደተሰጠበት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጊዜ የተጀመረው ለመምህራን የመኖሪያ ቤትና የቤት መገንቢያ ቦታ አቅርቦት ወጥ በሆነ መንገድ እንዲፈጸምና የመምህራንን የፍትሐዊነት ጥያቄ እንዲመለስ፣ የትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ እንዲሰጥበት ሐሳብ መቅረቡ ተሰምቷል፡፡

የመምህራንን ችግር ይፈታል ተብሎ የነበረው የመምህራን ባንክ የማቋቋም ዕቅድ በተመለከተ፣ እስካሁን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለምን እንዳልተጀመረ ጥያቄ መቅረቡም ታውቋል፡፡