ፖለቲካ

ዮናስ አማረ

October 23, 2024

‹‹የኮንዲሚኒየም ቤቶች የሚገነቡት ሕዝብ በቆጠበው ገንዘብ ነው የምትሉ ሰዎች ከየት አምጥታችሁ ነው ይህን የምትሉት? እነ ንግድ ባንክ ናቸው ብሩን የሚያቀርቡት፡፡ ወደ ተጨበጠው መረጃ ጠጋ ብላችሁ ብናወራ ምን አለበት፡፡ በብድር ነው የምንሠራው፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በጀቱን አስይዞ ነው የሚበደረው፡፡ ተመዝጋቢዎች የሚቆጥቡት ዕጣው የደረሳቸው ዕለት የሚከፍሉት እንዳያጡ ነው እንጂ መገንቢያ አይደለም፤›› በማለት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የከንቲባዋ ንግግር በዚህ ብቻ ግን የቆመ አልነበረም፡፡ ሲቀጥሉ፣ ‹‹ቤት ሳያዘጋጅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የመዘገበ አካል እያለ እንዴት ነው እኛ ብቻችንን የምንጠየቀው፡፡ ዜጎችን ለማታለል ቤት ሳይሠራ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ቆጥቡ ብሎ የመዘገበ አካል እያለ እኛ የምንጠየቀው ለምንድነው? እስካሁን የተገነባው እኮ ብዙ ቢመስልም 300 ሺሕ ቤት ነው፡፡ እኛ የደረስንበት ሳያሰልስ የሚቆጥብ ሕዝብ 600 ሺሕ ነው፡፡ የቆጠቡ ዜጎች ቤት ማግኘት አለባቸው፡፡ ካለቁት ኮንዲሚኒየሞች ብራቸው ተዘርፎ ነገር ግን ያልተጠናቀቁ ብዙ ናቸው፡፡ ወደ 80 ሕንፃ ጥለው ሄደዋል፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ነው 139 ሺሕ ቤቶችን የጨረስነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ዕዳ እየከፈለ ነው ሥራውን የቀጠለው፡፡ ወደ 56 ቢሊዮን ብር ዕዳ ነው የከተማ አስተዳደሩ በኮንዲሚኒየም የተረከበው፡፡ ወደ 30 ምናምን ቢሊዮን ብር ከፍለናል፡፡ በከፍተኛ ድጎማ የሚሠራ፣ ሳይሠራ የተከፈለበት በመኖሩና ሳይሠራ ሲሸጥ የቆየ ቤት በመኖሩ ነው ችግሩ የተፈጠረው፡፡ ጉዳዩን መነገጃ አታድርጉት፣ መነገጃ አይሆንምና፡፡ የ97 የሚባል የለም፣ እኛ እስከምናውቀው የ97 ዘግተናል፡፡ ባለፈው ያስጨረስናቸውን ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሳያሰልሱ ለቆጠቡ የ97 ቆጣቢዎች ዕጣ አውጥተንላቸዋል፡፡ እነሱ ዕጣ ከወጣላቸው በኋላ ቁጠባውን ዳግም የቀጠለ ካለ እሱ በሚቀጥለው ጊዜ ይታያል እንጂ ጉዳዩ በዚህ መንገድ ሊታይ አይገባም፤›› በማለት ነው ያብራሩት፡፡

ይህ የከንቲባዋ ንግግር ለብዙ ዜጎች ልክ እንደ መርዶ የሆነ ዱብ ዕዳ ነበር፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት ባዘጋጀው የ10/90፣ የ20/80 እና የ40/60 የቤት መርሐ ግብሮች ተመዝግበው ሳያቋርጡ በየወሩ የሚጠበቅበቸውን ቁጠባ ሲከፍሉ የቆዩ ዜጎች ዛሬም ድረስ በርካታ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ኮንዶሚኒየም ወይም በአነስተኛ ወጪ ለሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚነት በ2005 ዓ.ም. የተመዘገቡትን ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሚሊዮን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቤት ሲጠባበቁ መቆየታቸው ይነገራል፡፡

ይህ በአንድ ወቅት መንግሥት፣ ‹‹አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን በሰፊው የቤት ባለቤት አደረግኩበት›› እያለ ሲኩራራበት የቆየ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ‹‹የደሃዋ ኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎቹን የቤት ባለቤት እያደረገ ነው፤›› ተብሎ እስኪዘገብለት ድስ ለገጽታ መገንቢያነት ያዋለው ፕሮጀክት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ የኮንዲሚኒየም ግንባታ መርሐ ግብር ለኢትዮጵያ መንግሥት ምርጫ በመጣና የፖለቲካ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር የፖለቲካ መጠቀሚያና ተቀናቃኞቹን አፍ ማዘጊያ ፕሮጀክት ሆኖ ሲቀርብ የቆየ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይህ ሁሉ አልፎ ግን ተገነቡ የተባሉት ቤቶች በተጠበቀው ጊዜ ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች ሳይደርሱ መቅረታቸው ይታወቃል፡፡

ይህ ጉዳይ በሒደት በኢትዮጵያ ለተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ ጥያቄ መጠናከር አንዱ አቀጣጣይ ክብሪት እንደነበር ይነገራል፡፡ ከ2007 ምርጫ ማግሥት ጀምሮ በመንግሥት ላይ ይስተጋባ ለነበረው ቅሬታና ብሶት በሒደትም ወደ ተቃውሞነት ለተቀየረ ሕዝባዊ ንቅናቄ ይጠቀሱ ከነበሩ የብሶት ምንጮች አንዱ መነሻ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹በአንድ የኮንዲሚኒየም ሳይት ሁለት የኮንዲሚኒየም ብሎክች ጠፉ›› የሚል ቅሬታ መቅረቡ በወቅቱ በነበረው መንግሥት ላይ ከፍተኛ ቁጣ እንዲስተጋባ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በሌላ ወቅት ደግሞ ‹‹በጀሞ ኮንዲሚኒየም ሳይት የተገነቡ የኮንዲሚኒየም ብሎኮች የመስመጥና የመፈራረስ አደጋ ተከሰተባቸው፤›› መባሉም የጊዜውን መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ሲያስወቅስው ቆይቷል፡፡

ከኮንዶሚኒየም ፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ የቀደመው የኢሕአዴግ መንግሥት ሲሞገስ የኖረውን ያህል በተቃራኒው ከፍተኛ ወቀሳም ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡ ይህ ደግሞ የነበረው መንግሥት በመውደቂያ ዋዜማው ወቅት በቀረቡ የመንግሥት ሰነዶች ጭምር ተደግፎ ሲቀርብ ይታይ ነበር፡፡ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምት ማዕከል በ2009 ያቀረበው አንድ ጥናት የቤቶች ልማት ፕሮጀክቶችን ጉድለቶች በሰፊው ዘርዝሮ ነበር፡፡

መንግሥት በሰፋፊ የቤቶች ግንባታዎች ላይ መግባት አለበት/የለበትም የሚለው ጉዳይ አከራካሪ መሆኑን የሚያነሳው ሰነዱ፣ ኢትዮጵያ የዜጎች አቅምን ያገናዘቡ ቤቶችን መገንባት አዋጪ መሆኑን በማመን እንደጀመረች ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ይህ የቤቶች ግንባታ መርሐ ግብር ከፍተኛ የሆነ የፕሮኽት መጓተት፣ የሀብት ብክነት፣ የጥራት መጓደል ችግሮች ያለበት ነው፤›› ይላል ሰነዱ፡፡ ይህን በምሳሌዎች የሚያቀርበው ሰነዱ የቦሌ አራብሳ ሳይት ከተያዘለት ጊዜ አሥር ወራት ተጨምሮለትም በአጠቃላይ በ20 ወራት ውስጥ ከ83 በመቶ በላይ ማጠናቀቅ አልተቻለም ይላል፡፡

በልደታ መልሶ ማልማት ሳይትም በተመሳሳይ ጊዜው ተራዝሞ በአጠቃላይ በ20 ወራት ከ88 በመቶ በላይ የቤቶች ግንባታ አላለቀም፡፡ በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎትም የሚገነቡ ቤቶችም ቢሆን ጊዜ ተጨምሮ በአጠቃላይ በ20 ወራት መጠናቀቅ አልቻሉም ይላል ሰነዱ፡፡ የኮንዲሚኒየም ፕሮጀክቶች ይህን መሰሉ የግንባታ መጓተት ችግር ደግሞ ብዙ ችግሮችን ደራርቦ ይዞ እንደሚመጣ ያረጋገጠው ጥናቱ በጊዜው ከውሉ ውጪ ለተሠሩ ሥራዎች ለአምስት አማካሪ ድርጅቶች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉን በአኃዝ ያስቀምጣል፡፡ ለገንቢዎችና ለሌሎችም ብዙ ክፍያዎች መከፈላቸውን በመዘርዘር የግንባታ ጥራት መጓደልና የሀብት ብክነቱ አገሪቱን ከባድ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

እንዲህ ባለው ውስብስብ ችግር ውስጥ ያለፈው የኮንዲሚኒም ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በመጣና አዲስ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣ ማግሥት ደግሞ የቀደመው አስተዳደር መወቀሻና መረገሚያ ሲሆን መታየት ጀመረ፡፡ ብልፅግና መራሹ የለውጡ መንግሥት የኮንዲሚኒየም ፕሮጀክቶች ላይ የተደቀኑ ችግሮችን በመፍታት ለዓመታት ገንዘባቸውን እየቆጠቡ ቤት ሲጠባበቁ የቆዩ ዜጎችን ጥያቄ ይፈታል ተብሎ ቢታመንም፣ ነገር ግን ጉዳዩ ከቀደመው የመንግሥት የተወረሰ የመንግሥትና የሕዝብ መወዛገቢያ አጀንዳ መልሶ ሲሆን ነው የታየው፡፡

የቀደመው መንግሥት ለገባው ውልና ለተረከበው የሕዝብ አደራ እሱ መጠየቅ እንደማይገባው ሲሞግት የቆየው የአሁኑ መንግሥት፣ ከሰሞኑ ደግሞ የ97 ቤት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ጠንከር ያለ አቋም አንፀባርቋል፡፡ የ97 ተመዝጋቢዎች ጉዳይ መዘጋቱን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ይህን አጀንዳ አንዳንድ ወገኖች ደጋግመው እያነሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳያደርጉት አሳስበዋል፡፡ ከንቲባዋ አክለውም ኮንዲሚኒየም የተባለው የቤት ልማት መርሐ ግብር መንግሥትን ያከሰረና ዕዳ ተሸካሚ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ይህን መርሐ ግብር ማስቀጠል የማይችል መሆኑን በመጠቆም፣ ዜጎች በሚቆጥቡት የሚካሄድ ፕሮጀክት መባሉን ኮንነውታል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያናገራቸው የ97 ቆጣቢዎች ኮሚቴ አባላት ግን የከንቲባዋ ንግግር በአገራቸው ላይ ያላቸውን ተስፋ የሚያከስም፣ በመንግሥት ላይ ያላቸውን አመኔታ የሚያጨልም እንደሆነባቸው ነው የገለጹት፡፡

በ2015 ኅዳር 14ኛው ዙር የቤቶች ዕጣ አወጣጥ መርሐ ግብር ሲካሄድ የ97 ተመዝጋቢዎች ጉዳይ እልባት ያገኛል ብለው ጠብቀው እንደነበር ስማችን አይገለጽ ያሉት እነዚህ ተመዝጋቢዎች ጠቅሰዋል፡፡ በዚያ መርሐ ግብር 25 ሺሕ የሚሆኑ የ97 ተመዝጋቢዎች የዕጣ ተካፋይ ሆኑ፡፡ ለ17 ሺሕዎቹ ዕጣው ወጣ የሚሉት እነዚህ ተመዝጋቢዎች በመርሐ ግብሩ ያልደረሳቸው ቀሪዎቹ ቆጣቢዎችም በቀጣይ በሚደረጉ ዕጣዎች እንደሚካተቱ ጠብቀው እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ራሳቸው ከንቲባዋ በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተሠራጨ ቃለ መጠይቅ ላይ የ97 ተመዝጋቢዎች እስከ ዛሬ ቤት ያልደረሳቸው አላግባብ ነው ብለው መናገራቸውን ቆጣቢዎቹ አስታውሰዋል፡፡ ከንቲባዋ፣ በዚሁ ጊዜ እጃችን ላይ 30 ሺሕ ቤቶች ያሉ በመሆኑ፣ ለ25 ሺዎቹ ዕጣ አውጥተን ቀሪዎቹ በቀጣይ መርሐ ግብሮች እንደሚካተቱ ቃል ገብተው እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን የ2015 መርሐ ግብር ሲወጣ የ97ን እንግዲህ በዚህ ጨርሰናል የሚል ንግግር ጠቀስ ማድረጋቸውን ተመዝጋቢዎቹ ሥጋት እንዲያድርባቸውና ጥያቄ እንዲያነሱ መነሻ እንደ መሆናቸው አመልክተዋል፡፡

ከ2015ቱ ወይም ከ14ኛው የዕጣ መርሐ ግብር መካሄድ ማግሥት ጀምሮ ቤት ያላገኙ የ97 ተመዝጋቢዎች ራሳቸውን አደራጅተውና ኮሚቴ መሥርተው ባለፈው አንድ ዓመት ከስድስት ወር በላይ መንግሥትን ሲጠይቁ መቆየታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከቤቶች ልማት ጀምሮ እስከ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ድረስ መመላለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በስተመጨረሻ በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በኩል ጉዳዩ መጠየቁን ያመለከቱት ተመዝጋቢዎቹ፣ በዚህ ጊዜም በቀጣይ በሚደረጉ የዕጣ መርሐ ግብሮች ትካተታላችሁ የሚል ተስፋ ሰጪ መልስ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

ይህን ምላሽ ይዘው በተስፋ ሲጠባበቁ የቆዩት እነዚህ ቆጣቢዎች ራሱ መንግሥት በገለጸው አኃዝ መሠረት ከ25 ሺሕ ዕጣ ተሳታፊ 17 ሺሕ ሲወጣለት 8,000 ያህል የ97 ተመዝጋቢዎች አሁንም ቤት ጠባቂ መሆናቸውን የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡ ራሳቸውን በኮሚቴ  አደራጅተውና ግብረ ኃይል ፈጥረው እነዚህን የ97 ተመዝጋቢዎችን መረጃ ለመገምገም መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡ ለናሙና 951 ቆጣቢዎችን መረጃ መሰብሰባቸውን ያመለከቱ ሲሆን፣ ከ15 ሺሕ ብር ጀምሮ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የቆጠቡ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ 8,000 ሺሕ ቆጣቢዎች ምን ያህል እንደቆጠቡ ግምታዊ አኃዝ መሠራቱን ያመለከቱ ሲሆን፣ በዚህ ግምገማ መሠረት 144 ሚሊዮን ብር ቆጥበዋል የሚል አኃዝ ላይ መድረሳቸውን ነው የጠቀሱት፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ የ97 ተመዝጋቢዎች በከንቲባዋ ንግግር ክፉኛ ማዘናቸውንና ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸዋል፡፡ እንባ ባቀረረ ስሜትም በመንግሥት ላይ ያለን አመኔታ በእጅጉ ተሸርሽሯል ሲሉም ነው ቅሬታቸውን ያንፀባረቁት፡፡

የሰሞኑ የከንቲባዋ ንግግር በ97 ቤት ተመዝጋቢዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በብዙ ዜጎች ውስጥ የተለያየ ስሜት እንዲፈጠር ያደረገ ነበር፡፡ መንግሥት የተረከበውን የሕዝብ አደራ በዚህ ደረጃ መብላት የለበትም የሚል አስተያየት የሰጡ አሉ፡፡ መንግሥት ለሕዝብ የሚገባቸውን ቃሎች የሚሸመጥጥ ከሆነ መሠረታዊ የመንግሥትነት ባህሪውን እንደሚያጣ አንዳንዶች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለተጀመሩ ሥራዎች ወይም ለተወሰዱ ብድሮች የፈለገ በመፈንቅለ መንግሥት ቢመጣም የደርግ መንግሥት ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት አንዳንድ ወገኖች ጠቅሰዋል፡፡ ደርግ ሥልጣን እንደያዘ የሶማሊያ ወረራ ከማጋጣሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ንጉሡ ለመሣሪያ ግዥ 100 ሚሊዮን ዶላር ከፍለዋልና መሣሪያውን ስጡኝ ብሎ አሜሪካኖችን መጠየቁን እንደ ምሳሌ አንስተዋል፡፡

ደርግን የገለበጠው ኢሕአዴግም ቢሆን የቀደመው መንግሥት ለጦርነት ያፈሰሰው፣ ለመሣሪያ ግዥ ያባከነው ነው እኔን አትጠይቁኝ ብሎ ከዕዳ አለመሸሹን ይገልጻሉ፡፡ የአገር ዕዳ፣ በሕዝብ ስም የተወሰደ ገንዘብም ሆነ አደራ በመንግሥታት ልውውጥ ከአንዱ ወደሌላው እንደሚሸጋገር ነው እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የሞገቱት፡፡ ከዚህ ተነስተውም የብልፅግና መንግሥት የኮንዲሚኒየም ፕሮጀክት በኢሕአዴግ የተበላና የባከነ ስለሆነ እኔን አትጠይቁኝ ሊል የሚችልበት መሠረት አለመኖሩንም አመልክተዋል፡፡

በሌላ በኩል የኮንዲሚኒየም ፕሮጀክት አክስሮኛል፣ ባለዕዳ አድርጎኛል ብሎ መንግሥት ያቀረበበትን መንገድ በተመለከተ የኢኮኖሚ ትንተና እንዲሰጡ የተጋበዙ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ይህ አገላለጽ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ኮንዲሚኒየም ቤቶች ሲገነቡ መኖሪያ ብቻ ሳይሆን የንግድ ሱቆችም እንዲኖራቸው ተደርጎ መሠራቱን ባለሙያው ይጠቅሳሉ፡፡ ይህን የበለጠ ለማስረዳት የ40/60 ኮንዲሚኒየም ብሎክ ሱቆችንና ሽያጫቸውን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

‹‹እያንዳንዱ 40/60 ኮንዲሚኒየም ሕንፃ ላይ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያሉት ወለሎች ለንግድ የሚሆኑ ሱቆች ናቸው የተገነቡት፡፡ በአንድ ወለል ላይ ከአራት አስከ አምስት ሱቆች ሲኖሩ በሦስት ወለሎች ላይ በአጠቃላይ ከአሥር እስከ 12 ሱቆች ይኖራሉ እንደ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የሱቆቹ ሽያጭ ለጨረታ በወጣበት ወቅት አንድ ባለ 40 ካሬ ሜትር ሱቅ በ3.8 ሚሊዮን ብር ሲቸበቸብ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አንድ ባለ 40/60 ብሎክ አሥር ሱቆችን በ3.8 ሚሊዮን ብር ቢሸጥለት 38 ሚሊዮን ብር ገቢ መንግሥት ከአንድ ሕንፃ አገኘ እንደማለት ነው፤›› በማለት ባለሙያው አስረድተዋል፡፡

ከአንዱ ሕንፃ ሱቆች ሽያጭ እስከ 40 ሚሊዮን ብር ቢገኝ ይህ ገቢ በጊዜው በነበረው የግንባታ ዋጋ አንድ የ40/60 ሕንፃ ለመገንባት እንደማያስችል ግምታቸውን የተናገሩት፣ ባለሙያው፣ ሆኖም ከሁለት ብሎክ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው 80 ሚሊዮን ብር ግን የአንድ ሕንፃ መገንቢያ እንደሚሆን ነው የተናገሩት፡፡ መንግሥት በ40/60 ብሎኮች ላይ ብቻ ሳይሆን ተገነቡ ባላቸው የ20/80ም ሆነ የ10/90 ቤቶች በየብሎኮቻቸው ላይ ተያይዘው የተሠሩ የንግድ ቤቶችን (ሱቆች) ሲቸበችብ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹መንግሥት ከእነዚህ የሱቆች ሽያጭ ወጪውን ባይችልም ጠቀም ያለ ገንዘብ ያገኛል፡፡ የቤት ተመዝጋቢዎችን ቁጠባ እዚህ ላይ እንጨምርበት፡፡ በአነስተኛ ወለድ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቱ ያበድረዋል፡፡ ይህ ሁሉ እያለ የሚገነባቸው ኮንዲሚኒየሞች ባለዕዳ አድርገውኛል ወይም አከሰሩኝ ማለቱ በኢኮኖሚ ግምገማ ነውር ነው አይሆንም፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

መንግሥት በአገር ስም የወሰደውን ዕዳ አልከፍልም የሚልበት ዕድል እንደሌለ ሁሉ፣ የሚያስተዳድራቸውን ዜጎች አደራም አላውቅላችሁም ብሎ ወደ ጎን የሚልበት ዕድል እንደሌለው ነው ብዙዎች የሚናገሩት፡፡