

የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር)
ማኅበራዊ መሻሻሎችን የሚፈልገው የጤና መድን አገልግሎት
ቀን: October 23, 2024
አቶ እንግዳ ወርቁ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የጤና መድን አባል ከሆኑ ወዲህ በመንግሥት የጤና ተቋማት ነፃ የሕክምና አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸውንና በመድኃኒት አቅርቦት ላይ ግን ችግር መኖሩን ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ እንግዳ፣ የጤና መድን አባልና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በሕክምናው ዙሪያ ይህ ነው የሚባል የጎላ ችግር ባይገጥማቸውም፣ በሐኪሞች የታዘዙ መድኃኒቶችን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ከመድኃኒት አንፃር በአገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ካልሆነ ከውጭ አገሮች የሚመጡ መድኃኒቶችን ማግኘት ከባድ መሆኑን ያክላሉ፡፡
‹‹እንደ ስኳር፣ ደም ግፊትና መሰል ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ያሉባቸው ሰዎች የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንደሌለባቸው ሲናገሩ አደምጣለሁ፤›› የሚሉት ግለሰቡ፣ አንዳንድ የላቦራቶሪ ምርመራዎች በሆስፒታል የማይሰጡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የግል የጤና ተቋማት ሄደው ለማሠራት የሚገደዱ ሰዎች ስለመኖራቸው ይገልጻሉ፡፡
በአንዳንድ የመንግሥት ሆስፒታሎች የሚፈለጉ ሕክምና መሣሪያዎች ባለመኖራቸው ምክንያት በጤና መድን ሊሸፈኑ የሚገባቸው ምርመራዎችን በግል የጤና ተቋማት በከፍተኛ ወጪ ማሠራት ግድ የሚሆንበት ጊዜ መኖሩን ይናገራሉ፡፡
እሳቸውም፣ በአንድ ወቅት ለዓይን ሕክምና የታዘዘላቸውን መድኃኒት ከመንግሥት መድኃኒት ቤቶች ማግኘት ባለመቻላቸው ከግል ፋርማሲዎች ለመግዛት ተገደዋል፡፡
ለጤና መድን አገልግሎት በዓመት 1,700 ብር እየከፈሉ እንደሚገኙ የተናገሩት ግለሰቡ፣ ‹‹የጤና መድን አባል የሆንኩት እኔና ቤተሰቤ እንታመማለን በሚል ሥጋት ብቻ ሳይሆን የምናዋጣት ሳንቲም ከፍለው የመታከም አቅም የሌላቸውን ወገኖች ሕይወት ቢታደግ በሚል ዕሳቤ ነው፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ ጫላ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፣ የጤና አገልግሎትን ለከተማው ነዋሪ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት ቀዳሚው ነው፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል፣ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በተሠራው ሥራም በ2016 ዓ.ም. ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የጤና መድን አባል ለመሆን ችለዋል፡፡ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ አባላትና ቤተሰቦቻቸው በተመላላሽና በተኝቶ ሕክምና ከጤና ጣቢያ እስከ ፌዴራል ሆስፒታሎች ባሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት ያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን መርሑ መደጋገፍን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ ራሱንና ቤተሰቡን ካልታሰበ ድንገተኛ ወጪ ለመጠበቅ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ከጥቅምት 1 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የነባር አባላት እድሳትና የአዲስ አባላት ምዝገባ እያካሄደ ይገኛል፡፡ የአባላት መደበኛ መወጮ መጠን 1,500 ብር ሲሆን፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚቀርብ ማስረጃ መሠረት የጤና መድን ክፍያቸው በከተማ አስተዳደሩ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ለነባርና ለአዲስ አባል መዋጮ 1,500 ብርና የመመዝገቢያ 200 ብር፣ አጠቃላይ 1,700 ብር ዓመታዊ መዋጮ የሚከፈል ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆችና የጤና መድን አባል በሆነ ግለሰብ ጥላ ሥር ለሚኖሩ ተጨማሪ 750 ብር በነፍስ ወከፍ የሚከፈል መሆኑንም አክለዋል፡፡ ‹‹መደበኛ ባልሆነ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተቀመጠውን መዋጮ በመክፈል፣ ዓመቱን ሙሉ ውል በተገባባቸው የጤና ተቋማት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፤›› ያሉት ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ ኅብረተሰቡም ይህንን በመረዳት በሚኖርበት ወረዳ በሚገኝ ጤና ጣቢያ በመሄድ የነባር አባላት ዕድሳትና አዲስ ምዝገባ ማካሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ዘንድሮም ከ2.5 ሚሊዮን በላይ የከተማ ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዷልም ብለዋል፡፡
ከጤና መድን ሥርዓት ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከልም በጤና ጣቢያና በሆስፒታሎች የጤና መድን አገልግሎት አሰጣጡን በቋሚነት የሚከታተሉና የሚያስተባብሩ ባለሙያዎችን መመደብ ተችሏል፡፡ ይህ በመሆኑም ቀደም ሲል የጤና መድን ካርድ ይዘው የሚመጡ አባላት ያጋጥሟቸው የነበረውን መጉላላትና ውጣ ውረድ ለማስቀረት የተቻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሆስፒታሎች አንዳንድ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደማይቻልና የመድን ተጠቃሚዎች ወደ ግል ተቋም ለመሄድ የሚገደዱ መሆኑን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም፣ ባሉት የመንግሥት ላቦራቶሪዎች እየተሠራ መሆኑን፣ ሆስፒታሎች እየዘመኑ በመሆናቸው ችግሩ በሒደት እንደሚቀረፍና ባሉት የሕክምና ቁሳቁሶች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዮሐንስ (ዶ/ር)፣ የከተማ አስተዳደሩ በመድኃኒት ዙሪያ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል፡፡ ከቢሮ ጀምሮ እስከ ታች ጤና ተቋም ድረስ መድኃኒቶች ለታለመላቸው አገልግሎት መዋላቸውን የሚያረጋግጡ ሥርዓትና አሠራሮች ተዘርግተዋል፡፡ በመሆኑም የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚዎች በፍትሐዊነት መድኃኒት በሚያገኙበት ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡
የመድኃኒት አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ በሆስፒታል ደረጃ የማኅበረሰብ ፋርማሲዎች እየተቋቋሙና በከነማ መድኃኒት ቤቶች የመድኃኒት አቅርቦቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የከነማ መድኃኒት ቤት ቁጥር በሦስት ዓመታት ውስጥ ቀድሞ ከነበረው 20 አካባቢ ወደ 52 ለማሳደግ መቻሉንና የከተማ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በየዓመቱ ክፍያ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
