
ልናገር የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሦስቱ አገራዊ ጥያቄዎቻቸው ትውስታ
ቀን: October 23, 2024
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
የዲፕሎማሲውን ዓለም እንደ እጃቸው መዳፍ አሳምረው፣ አብጠርጥረውና አንጥረው ያውቁታል የሚባሉትና ከአፍሪካ እስከ አውሮፓና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስካሁኑ አፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድረስ የዘለቀ ብስለትንና ትልቅ ኃላፊነት በሚጠይቅ የዲፕሎማሲ ሥራ ያከናወኑት የቀድሞ የአገራችን ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን፣ በአንድ መልካም አጋጣሚ ለማግኘትና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት ከሆኑ ሊቀ ጳጳስ ጋር ያደረጉትን ውይይት ለመስማት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡
ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅና የቤተ ክርስቲያናችን አባት ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ ጋር ያደረጉትን ውይይታቸውን ለመካፈልና የቻልኩበት አጋጣሚ ይህን መሳይ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅን ያገኘኋቸው በቅርብ ከሚያውቋቸው አንድ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ሊቀ ጳጳስ ጋር በመሆን ሲሆን፣ እኚህ አባት በአንድ ወቅት በሀገረ ስብከታቸው አብሬያቸው ሠርቼ ነበር፡፡ ብፁዕነታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመላው አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኮንፈረንስ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ናቸው፡፡
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ከእኚህ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረቱበት አጋጣሚ የተፈጠረው፣ ብፁዕነታቸው የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስና በተለይም ደግሞ በአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ውስጥ በነበራቸው የሥራ ኃላፊነት፣ እንዲሁም በኢጋድ አገሮች የሃይማኖት መሪዎች/አባቶች የሰላም ተልዕኮ ጋር በተያያዘ ነበር፡፡
በወቅቱ የአገራችን ፕሬዚዳንት የሆኑት ክብርት አምባሳደር ሳህለወርቅ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አባት ጋር በነበራቸው ቆይታቸው ካነሷቸው ሐሳቦች መካካል ሦስቱን የውይይት ሐሳብ/አጀንዳዎች ላስታውስ ወደድኩ፡፡ እነሱም ዕርቀ ሰላምን፣ ልመና/ተረጂነትንና የድምፅ ብክለትን የተመለከቱ ጉዳዮች ነበሩ፡፡
ከክብርት ፕሬዚዳንት ጋር በጽሕፈት ቤታቸው የነበረን ቆይታ የፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት በጦርነት ውስጥ የነበሩበት ጊዜ ነበር። በመሆኑም ክብርት ፕሬዚዳንቷ ለሊቀ ጳጳሱ በቀዳሚነት ያነሱት ጉዳይ ስለአገራችን ሰላም ነበር፡፡
የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም፣ ስለዕርቅ አብዝተው ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ሐሳብ የሰነዘሩት፣ በአገራችን የሰላም ዕጦትንና የእርስ በርስ ጦርነት በስፋት ያነሱበትና የተወያዩበት የሰላማችን ነገር ሰፊውን የውይይት ጊዜ የወሰደ አንገብጋቢና ወቅታዊ አጀንዳ ነበር፡፡
የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በጥልቅ ኢትዮጵያዊ የእናትነት ስሜት፣ ትካዜና ቁጭት ውስጥ በሆነው ለቤተ ክርስቲያን (ለሊቀ ጳጳሱ) ይህን ሐሳብ አንስተው ነበር፡፡
- ስለምንድን ነው ከእርስ በርስ የመገዳደል፣ የጥላቻና የመገፋፋት አባዜ መውጣት ያቃተን…?
- የሐሳብ ልዩነቶቻችንና አለመግባባቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍተታ ይልቅ ውረድ እንወረድ ከሚል የጦርነት አባዜ ለመላቀቅ ስለምን ተሳነን…?
- ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሰላምና አንድነት አብዝተን የደከምን ሕዝቦች ለራሳችን ዕርቀ-ሰላምን ለማውረድ ስለምን ተሳነን…?
- የሃይማኖት፣ የባህል፣ የታሪክና የሰው ልጆች ሥልጣኔ እምብርት የተባልን እኛ ኢትዮጵያውያን ሰላም የራቀንና ፍቅርን የተራቆትን ስለምን ሆነን… የሚለው ቁጭትና ሐዘን የወለደው የፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ጋር ያነሱት ጥያቄ/የውይይት አጀንዳ የአገራችንን የጦርነት ታሪክ ሰበዞች እየተመዘዙ ሰፋ ያለ ውይይት የተደረገበት ቁልፍ ጉዳይ ነበር፡፡
- በእርግጥም የክብርት ፕሬዚደንቷ ጥያቄያቸውና ቁጭታቸው፣ አሁን በዚህች ቅፅበትም የሁላችን የኢትዮጵያውያን ጥያቄ/እንቆቅልሽ እንደሆነ ዘልቋል፡፡
- የአንድነታችን፣ የሰላማችን ጉዳይ፣ በፍቅርና በአብሮነት የመዝለቃችን ነገር የታሪክ ስብራት ሆኖብናል፡፡ ነገርዬው፣ ነፍሰ ኄር ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን እንዳለው ነው፡፡
‹‹… ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን፣
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን፣
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን፣
እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን፣
ፈራን…
ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሠራን ብቸኝነት ጠራን
በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሠራን፣
ናቅን…
በልዩነት ደምቀን ያልኖርን ያህል አንድም ቀን
እልህ ተናነቅን፣
ናቅን…
መቻቻልን ናቅን ለፀብ አሟሟቅን
ለዓመፅ ስንነሣ ለሰላም ወደቅን
አገር ስትቃጠል ከዳር ሆነን ሞቅን…፡፡
ክብርት ፕሬዚደንቷ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ ጋር በተያያዘ ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ፣ በየቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ወድቀው የሰው እጅ የሚጠብቁ አረጋውያን፣ እናቶችና ሕፃናትን ቤተ ክርስቲያን በአንድ ማዕከል አሰባስባ በዘላቂነት የሚረዱበትና በሒደትም ራሳቸውን ከተረጂነት በማውጣት የሥልጠና ድጋፍ አግኝተው የሚቋቋሙበት መንገድ በተመለከተ በሲኖዶስ ስብሰባ ስትገናኙ ለምን አትመክሩበትም?
ከመከራችሁበትስ ስለምን በስፋትና በተደራጀ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ አልተቻለም?
በምእመን ብዛት፣ በልጆቿ ዕውቀትና የኢኮኖሚ አቅም ከፍ ያለ ደረጃ ያላት ቤተ ክርስቲያን ስለምን ይኼንን በስፋትና በተጠናከረ ሁኔታ ለማድረግ አልተቻላችሁም የሚል ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሌላው ያነሱት ከድምፅ ብክለት ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ መንግሥታቸው አካባቢ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ካቴድራል ቅድስት ሥላሴ፣ መንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንና ታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም በመንፈሳዊ አገልግሎት ጊዜ በድምፅ ማጉያ የሚወጣው ድምፅ ስለምን የተመጠነ አይሆንም የሚል ነበር፡፡
ይህን ጉዳይ አሁን አሁን የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ መምጣቱን ልብ ይሏል… በተለይ ከተለያዩ ከቤተ እምነቶች የሚወጠው ድምፅ በአፍአም ሆነ በውጭ አምልኮተ ሥርዓትን ለሚፈጽሙ ሰዎች የተመጠነ ቢሆን፣ የሌሎችን ስሜትና መብት የሚጋፋ ባይሆን የሚል አጀንዳ ተደጋግሞ እየተነሳ ነው፡፡
በግሌ ይህ ጉዳይ ቤተ እምነቶችና አማኞች በአንድነትና በጋራ ሆነው ምክክርና ስምምነት ሊያደርጉበት የሚገባቸው ጉዳይ መሆን እንዳለበት እስማማለሁ፡፡
ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአገርዎ፣ ለአፍሪካና ለመላው ሰው ልጆች ሰላምና ዕድገት ላበረከቱት ሥራዎና በጎ አስተዋፅኦ ምሥጋና ይገባዎታል!!
ሰላም ለአገራችን!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡