በሸራተን አዲስ በተካሄደው ውይይት ላይ

ዜና ብልፅግና የቻይናን ኮሙዩኒስት ፓርቲ ጥንካሬዎች ወስዶ መተግበር እንደሚፈልግ ተገለጸ

በጋዜጣዉ ሪፓርተር

ቀን: October 23, 2024

በኢሳያስ ኃይሉ

የብልፅግና ፓርቲም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የቻይናውን ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጥንካሬዎች መማርና መተግበር ያስፈልጋል ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ ገለጹ።

የቀድሞው የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ዋና ዳይሬክተርና በአሁኑ ሰዓት የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት  ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይና የቻይናው ምክትል ትምህርት ሚኒስትርና የኮሙዩኒስት ፓርቲ ተወካይ ትናንት ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በሁለትዮሽ አገራዊ ትብብር ላይ ያተኮረ  ውይይት አካሂደዋል።

ኃላፊው አቶ ተስፋሁን በውይይቱ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ የአንድ ቻይና ፖሊሲን እንደምትደግፍና ቻይና የኢትዮጵያ ትልቋ የውጭ ገበያ መዳረሻና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ግንባር ቀደም መሆኗን ጠቅሰዋል።

የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲም ከመቶ ዓመታት በላይ ራሱን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ ሕዝቡን ለለውጥ ዝግጁ አድርጎ መዝለቁን ገልጸዋል።

‹‹የምዕራቡ ዓለምን ነፃ ገበያን በትንሽ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መምራት›› የሚለውን ዕሳቤ፣ የቻይና የዕድገት መንገድ አንድና ወጥ አለመሆኑን የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ ማሳያ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የቻይናው ኮሚዩኒስት ዕሳቤ ቻይናን በቻይናውያን መንገድ ማሳደጉን ጠቅሰው ብልፅግና ፓርቲም የኢትዮጵያውያንን ችግር በመረዳት፣ መደመር በሚል ርዕዮተ ዓለም የተመሠረተ ፓርቲ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

‹‹የብልፅግና ፓርቲና የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ በርካታ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ አለ›› ያሉት አቶ ተስፋሁን፣ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ብልፅግና ከሌሎች ፓርቲዎች በርካታ ትምህርቶችን መማሩን ይቀጥላል ብለዋል።

ስምንት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ሊወጣ የቻለው፣ የሕዝቡን ችግር የተረዳና ቁርጠኛ  የሆነ መንግሥት በመኖሩ እንደሆነ ገልጸው፣ ብዙ ሊወሰዱ የሚገባቸው ትምህርቶች ስለመኖራቸውም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ1,800 በላይ የቻይና ኢንቨስተሮች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የሁለቱ አገሮች የንግድ ግንኙነት በቻይና የበላይነት የሚመራ ነው።

የቻይናው ምክትል የትምህርት ሚኒስትርና የኮሙዩኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን በበኩላቸው፣ መንግሥታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያንን የማሠልጠንና ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት ስለመኖሩ ተናግረዋል።