

አይደር ሆስፒታል
ማኅበራዊ አይደር ሆስፒታል ለሕሙማን ምግብ ማቅረብ አለመቻሉን አስታወቀ
ቀን: October 23, 2024
በአብርሃም ተክሌ
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ የሚገኘው አይደር ሆስፒታል በገጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት በሆስፒታሉ ተኝተው የሕክምና ክትትል ለሚያደርጉ ሕሙማን ምግብ ማቅረብ አለመቻሉን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጻፈው ደብዳቤ አስታወቀ።
አይደር ሆስፒታል ‹‹አስቸኳይ የሰብአዊ ዕርዳታ ጥሪ ለአይደር ሆስፒታል›› በሚል ርዕስ ያጋጠመውን የበጀት እጥረትን አሳሳቢነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያስታወቀው ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. ባሰረጨው ደብዳቤ ሲሆን፣ ሆስፒታሉ ደብዳቤውን የጻፈው እያጋጠመው ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ለማሳወቅ መሆኑን አስታውቋል።
ሆስፒታሉ ያጋጠመው የምግብ እጥረት በሕክምና እንክብካቤ ላይ ያሉ ወገኖች ደኅንነትና ማገገም ላይ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን በመግለጽ፣ ‹‹ሆስፒታሉ ለታካሚዎች የሚያቀርበው ምግብ በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት እያጋጠመው በመሆኑ፣ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ሕሙማንን መመገብ እንድናቆም አስገድዶናል፤›› ብሏል፡፡
የሆስፒታሉ ደብዳቤ በማከል ሁኔታዎች በሙሉ ‹‹የቀውስ ደረጃ ላይ ደርሰዋል›› በማለት፣ ‹‹ሊከሰት የሚችለውን ሰብዓዊ አደጋ ለመከላከል አፋጣኝ ዕርምጃ ያስፈልጋል፤›› ሲል ችግሩን ጠቁሟል፡፡
ሆስፒታሉ ከ600 በላይ አልጋዎች የመያዝ አቅም እንዳለው፣ ረጅም ጊዜ በአጠቃላይ ለትግራይ ክልልና ለአካባቢው ማኅበረሰብም ወሳኝ የጤና እንክብካቤ አቅራቢ ሆኖ መቆየቱን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ከፍተኛ የሆነ የፋይናንስ ችግር እንደገጠመው ይጠቅሳል፡፡
‹‹በአሁኑ ጊዜ ሆስፒታሉ በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ ይገኛል፣ ይህም በጦርነቱ ጊዜ ተባብሶ የታየ ነው፤›› ያለው ሆስፒታሉ፣ ‹‹በዚህ ዓመት የተመደበው በጀት እጅግ በጣም ዝቅተኛ ሲሆን፣ የሆስፒታሉን የአንድ ወር የምግብ ወጪን እንኳን ለመሸፈን በቂ አይደለም፤›› በማለት አስረድቷል።
አፋጣኝ ጣልቃ ገብነት ከሌለ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎች ጤና እና ሕይወት ለአደጋ ተጋላጭ እንደሆነ የሚያስነብበው የአይደር ሆስፒታል ደብዳቤ፣ ‹‹ዓለም አቀፍ አጋሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ጊዜ ያጋጠመንን ችግር በመረዳት በአፋጣኝ እንዲረዱን እንጠይቃለን፤›› ብሏል፡፡
የዕርዳታ ለጋሾች ድጋፍ ‹‹የታካሚዎችን እንክብካቤ ለመጠበቅና የሆስፒታሉን ሥራዎች ለመደገፍ ወሳኝ የሆኑትን የምግብ፣ የሕክምና ቁሳቁሶችና የገንዘብ ዕርዳታን ጨምሮ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ ሊታገዝ ይገባል፤›› በማለት ጥሪውን አስተላልፏል።
የችግሩን አሳሳቢነት በማስመልከት ከሪፖርተር ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ቢሮ ባልደረባ እንዳሉት ከሆነ፣ ለአይደር ሆስፒታል በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የሕክምና መስጫ ተቋማት ትልቁ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ተከስቶ የነበረው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎች ከአጎራባች ክልሎችም ይመጡ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ እንደ ቃል አቀባዩ ከሆነ፣ አይደር ሆስፒታል ከሕክምና አገልግሎት ባሻገር በዓመት ከ3,000 በላይ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም እንደነበር ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አሁን ተቋሙ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት ከዚህ በፊት የሚታወቅበትን አስፈላጊ አገልግሎቶች ለመስጠት እንደተቸገረ አክለዋል፡፡
ሆስፒታሉ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሥር የተቋቋመ በመሆኑና ዓመታዊ በጀት የሚያገኘው ቀጥታ ከፌዴራል መንግሥት ነው ብለው፣ ሆኖም ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ከቆመ በኋላ ግን የሚያገኘው በጀት በግማሽ በመቀነሱ አሁን ላለበት ችግር ተዳርጓል ብለዋል፡፡
‹‹አሁን ለተቋሙ የሚሰጠው በጀት በግማሽ ቀንሷል፣ በአሁኑ ጊዜ ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ ከሌሎች ድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚደረግለት ድጋፍ የለም፤›› ብለው፣ ባጋጠመው ችግር ምክንያት ሠራተኞች ሥራቸውን እያቆሙ ሕክምና ፈላጊዎች እየተጉላሉ እንደሆነና ሕሙማንንም መመገብ ስለተሳነው ቀድሞ የሚሰጠውን የምግብ አገልግሎት ማቋረጡን ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ ችግር ያጋጠመው የምገባ አገልግሎቱ ላይ ብቻ ሳይሆን የበጀት እጥረቱ በፈጠረው ችግር ምክንያት የመድኃኒት አቅርቦት፣ የላቦራቶሪ ዕቃዎች እጥረትና የሕክምና መሣሪያ መለዋወጫዎች አቅርቦት ላይም ችግር እንደገጠመው ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአይደር ሆስፒታል የአስተዳደርና ልማት ዋና ዳይሬክተር ኃይለ ሥላሴ በርኸ (ዶ/ር) ተቋሙ ያጋጠመውን የበጀት እጥረት አረጋግጠው፣ ‹‹ችግሩ ያጋጠመው ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በተከሰተው የበጀት እጥረት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥት በፊት ከሚሰጠው ዓመታዊ በጀት ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነውን በመቀነሱ ችግሩ አጋጥሟል ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ለመድኃኒት ግዥ መንግሥት ወደ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በዓመት ይመድብ ነበር፡፡ ሆኖም ካለፈው ዓመት ጀምሮ 18 ሚሊዮን ብር በቻ ነው የመደበው፤›› ብለው፣ በጀት መቀነሱ በሌሎች ዘርፎች ላይም ተመሳሳይ መሆኑን በማስታወስ፣ ‹‹ባለፈው ዓመት ለምግብ አገልግሎት የተሰጠን በጀት ሁለት ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን፣ በፊት ይቀርብልን ከነበረው በግማሽ ቀንሷል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡
ሆስፒታሉ በዓመት ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት የሚመደብለት በጀት በግማሽ ስለቀነሰ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት እንደተቸገረ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት በሚነገርለት በአይደር ሆስፒታል፣ በሌሎች ሆስፒታሎችና በጤና ተቋማትና በሕክምና ግብዓቶች ላይ የሁለት ዓመቱ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን በቅርቡ የወጣው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ በትግራይ ክልል ከሚገኙት 853 የጤና አገልግሎት መስጫዎች 86 በመቶ ያህሉ መዋቅራዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ 71 በመቶ የሚሆኑት የሕክምና መሣሪያዎች በከፊል እንደማይሠሩና 28 የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡