መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ

ማኅበራዊ መርካቶ ሸማ ተራ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው የተረፈ ነጋዴዎች መዘረፋቸውን ተናገሩ

ተመስገን ተጋፋው

ቀን: October 23, 2024

ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ከ12፡30 ሰዓት ገደማ በመርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ በደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ ንብረታቸው የተረፈላቸው ነጋዴዎች ዝርፊያ እንደተፈጸመባቸው ተናገሩ፡፡

የእሳት አደጋው በተከሰተ ወቅት ግርግሩን በመጠቀም በርካታ ሰዎች የተለያዩ ንብረቶችን መዘረፋቸውንና በወቅቱም የፀጥታ አካላት የደረሰውን አደጋ ለመቆጣጠር ከአቅማቸው በላይ እንደነበር ቦታው ላይ የነበሩ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መርካቶ ሸማ ተራ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው የተረፈ ነጋዴዎች መዘረፋቸውን ተናገሩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ

የእሳት አደጋው የደረሰበት ሰዓት በጊዜ ስለነበር አደጋውን መቆጣጠር ይቻል ነበር የሚሉት ነጋዴዎቹ፣ አብዛኛውን የተቃጠለው ንብረት ጫማ፣  ልብስና እንዲሁም ከፕላስቲክ የተሠሩ ዕቃዎች በመሆናቸው እሳቱን እንዲባባስ ማድረጋቸውንና መቆጣጠር አልተቻሉንም ብለዋል፡፡

በወቅቱ የእሳት አደጋው በደረሰበት ወቅት አብዛኛው ነጋዴ የራሱን ንብረት ለማሸሽ ጥረት ቢያደርግም፣ የእሳት አደጋው ከፍተኛ ስለነበር ብዙ ንብረት መውደሙን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ በመርካቶ ሸማ ተራ የተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ያስከተለው ጉዳትና የውድመት መጠን ተጣርቶ የሚገለጽ ይሆናል ብለዋል፡፡

በእሳት አደጋው የሞተ ሰው እንደሌለ ነገር ግን የኮሚሽኑ የአደጋ ሥራ ሠራተኞች ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው አምስት ሰዎች መኖራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መርካቶ ሸማ ተራ ከደረሰው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው የተረፈ ነጋዴዎች መዘረፋቸውን ተናገሩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ አደጋ

እሳቱን ለማጥፋት ከ22 በላይ የእሳት አደጋ መቆጣጠሪያ ተሽከርካሪዎችና የውኃ ቦቴዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የእሳት አደጋ መከላከል ቡድን መሳተፉን፣ የውኃና ፍሳሽ፣ ባለሥልጣንን ጨምሮ ሌሎች ተቋማትም መረባረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

እሳት አደጋው የተከሰተበት ቦታ ለድንገተኛ አደጋ የተጋለጡ ተብለው ተለይተው ከሚጠቀሱት እንደሚገኝበት ገልጸው፣ በቀጣይ በአካባቢው ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ለመገንባት ዕቅድ መያዙን አክለዋል፡፡

የገበያ ማዕከሉ የተሠራበት ግብዓት ለእሳት የሚያጋልጥ መሆኑን፣ በገበያውም ነዳጅ፣ ዘይት፣ ሽቶና የእሳት አደጋን የሚያባብሱ ነገሮች የሚሸጡበት ቦታ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

አደጋው ከደረሰ በኋላ የእሳት አጥፊ ተሽከርካሪዎች እንደ ልብ መግባት የማይችሉበት ሁኔታ በመፈጠሩ፣ እሳቱ በፍጥነት ሊዛመት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደማምረው ኮሚሽኑ በአፋጣኝ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር መቸገሩን በመግለጽ ነገር ግን በተደረገው ርብርብ እሳቱን ማጥፋት መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በእሳት አደጋውም የደረሰው ውድመት፣ የገንዘብ መጠንና የአደጋው ምክንያት እየተጣራ ሲሆን፣ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውም ሰዎች በፍጥነት በኮሚሽኑ በኩል የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

የንብረት ውድመቱን ለማወቅ ገና ነጋዴዎችን ማግኘት እንደሚያስፈልግና ዝርዝር መረጃውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እያጣራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል አደጋውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ 33 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንና ከአደጋው ጋር በተያያዘ በሰባት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

አደጋውን ለመከላከል የፀጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ኅብረተሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የአደጋውን  መንስዔ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩ ታውቋል፡፡

አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈጸም እንዲሁም የአደጋ መከላከል ሠራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም የመከላከያ ሠራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እርብርብ ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡