በአማራ ክልል ባለፉት 8 ወራት 66 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መሞታቸው ተገለጸ።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ቀደም ብሎ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ በሽታ ሥርጭቱ የመቀነስ አዝማማያ ቢያሳይም አሁንም በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች በቀን እስከ 4 ሰዎች በበሽታው ስለመያዛቸው ሪፖርት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል።
በክልሉ ከመጋቢት 27/2016 ዓም እስከ ጥቅምት 11/2017 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ 4,396 ሰዎች በኮሌራ ተይዘው 66 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን በአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የበሽታዎች እና የጤና ሁኔታዎች ምላሽ አሰጣጥ ባለሞያ የሆኑት ሲ/ር ሰፊ ደርብ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።
ስርጭቱ አሁን በመጠኑም ቢሆን መቀነሱን ያነሱት ባለሞያዋ ምዕራብ ጎንደር ላይ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ፣ሰሜን ወሎ ሃሩ ወረዳ እና ደቡብ ጎንደር ላይ ደራ አካባቢ እስካሁን በበሽታው የተጠቁ ሰዎችን ሪፖርት ማድረግ ቀጥለዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሪፖርት አድርገው የነበሩት ጎንደር ከተማ፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን፣ ምዕራብ ጎንደር ፣ ደቡብ ጎንደር ፣ሰሜን ጎጃም እና ወልዲያ ከተማ ከፍተኛ ሥርጭት የነበረባቸው ቢሆንም አሁን ስርጭቱን መቀነስ ተችሏል ብለዋል።
በመስከረም ወር ለአስር ቀን በተደረገ የክትባት ዘመቻም በጎንደር ከተማ እና ምዕራብ በለሳ እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በላይ ለሆኑ 293,405 ሰዎች ክትባት መከተብ መቻሉን አክለዋል።
በክትባት ዘመቻው ምዕራብ በለሳ 100 በመቶ ጎንደር ከተማ ደግሞ 86 በመቶ መሸፈን ተችሏል ተብሏል።
ሥርጭቱን ከመከላከል አኳያ ተግዳሮት ስለሆነ ጉዳዮች ጥያቄ ያቀረብንላቸው ባለሞያዋ የጸጥታ ችግር አንዱ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።
“ለኮሌራ አጋላጭ የሆኑ የስጋት ቦታዎች በዝተዋል በተለይም የቀን ሠራተኛ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ማለትም ማዕከላዊ ጎንደር፣ ወልቃይት ጠገዴ (ሰቲት ሁመራ) እና ምዕራብ ጎንደር ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች ስላሉ እዛ የሚሄድ የቀን ሰራተኛ በሚሊዮን የሚቆጠር ነው ነገር ግን በዛ በቂ የሆነ ውሃ ንጽህናው የተጠበቀ ምግብ ባለመኖሩ ወረርሽኙ እየተከሰተ ነበር” ብለዋል።
የኮሌራ በሽታ ሪፖርት በሚደረግባቸው አካባቢዎች የክትባት ዘመቻው ለምን አልቀጠለም ስንል ላቀረብንላችው ጥያቄም ባለሞያዋ ሲመልሱም :-
“ክትባቱ እኛ ስለፈለግን የምናገኘው አይደለም ይህንን የሚያቀርብ አለም አቀፍ ተቋም አለ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በድንገተኛ (Emergency) ጠይቆ ነው የሚያመጣው ብዙ ጊዜ ክትባቱ ውድ በመሆኑና በእርዳታም የሚመጣ በመሆኑ እኛ ስለፈለግን ብቻ መከተብ አንችልም” ብለዋል።
ነገር ግን አሁንም ክትባት የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ያነሱት ባለሞያዋ ክትባቱ በመጣ ጊዜ ለመስጠት ዝግጁ ነን ሲሉ አክለዋል።