መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታ፣ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ የተደረጉ እና አስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁም በሚችል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች እና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በተመለከተ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና ፍትሕ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁሙ በሚችሉ እና ያሉበት ሳይገለጽ በተራዘመ እስር ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በተመለከተ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና ፍትሕ ሊሰጣቸው ይገባል ሲል አስታወቀ፡፡
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ ከ52 በላይ የሆኑ ሰዎችን የተመለከቱ አቤቱታዎችን መርምሮ እስካሁን ድረስ 44 ሰዎች ከ1 ወር እስከ 9 ወር በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከቆዩ በኋላ መለቀቃቸውን ማወቁን ገልጻል፡፡
በመሆኑም የሚደርሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎችን እንዲሁም የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዐይን ምስክሮችን እና የተለቀቁ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡን ኢሰመኮ አስታውቋል፡፡
ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተገቢውን የሕግ ሥነ ሥርዓት ባልተከተለ ሁኔታ በግዳጅ እንደሚያዙ ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም በእስር የቆዩበትን ቦታ የማያውቁ፣ በቂ ምግብና ውሃ የማይቀርብላቸው እና መሠረታዊ የመጸዳጃ፣ የመኝታ እና የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦቶች አለመኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሚለቀቁትም በምሽት ዐይናቸው ተሸፍኖ በተሽከርካሪ ከተጫኑ በኋላ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች እንዲወርዱ ተደርገው እና “ለመጓጓዣ” በሚል ከ300 እስከ 1000 ብር ተሰጥቷቸው እንደሚለቀቁ ማስረዳታቸው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ኢሰመኮ ጉዳዩን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምላሽ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ይህ መግለጫ እስከወጣበት ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተሳካ መሆኑን ገልጻል፡፡
ከሪፖርቱ ውስጥ የተገኘ ማሳያ ፦
(የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን ሊያቋቁም በሚችል ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ተጎጂዎች)
አቶ መንበረ ቸኮል ምስጋናው፣ የግንባታ ባለሙያ፣ የ7 እና የ4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 2 ሕፃናት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ግንቦት 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ “ሰፈራ” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በጸጥታ አካላት ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ የተወሰዱ ሲሆን፣ ያሉበት ቦታ እና ሁኔታ የማይታወቅ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ጭንቀትና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ተጋልጠው ይገኛሉ።
አቶ ዘላለም ግሩም ፍላቴ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባልና አሽከርካሪ ሲሆኑ፣ ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፣ ልዩ ስሙ “ዲቦራ ትምህርት ቤት” ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በጸጥታ አካላት ሰሌዳ ቁጥሩ ባልታወቀ ተሽከርካሪ ከተወሰዱ ጀምሮ፣ ያሉበት ቦታ እና ሁኔታ የማይታወቅ በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ጭንቀትና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ውስጥ ይገኛሉ።
(በተለያየ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ወይም ያሉበት ሳይታወቅ በተራዘመ እስር ሁኔታ ቆይተው የተለቀቁ)
አቶ አማረ ግዳፍ፣ ባለ3 እግር ተሽከርካሪ በተለምዶ “ባጃጅ” በማሽከርከር ሥራ ላይ የተሰማሩ ሲሆኑ መጋቢት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከረፋዱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ በአዲስ አበባ ከተማ፣ የካ ክፍለ ከተማ፣ በተለምዶ “ወሰን መስቀለኛ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 6 የሲቪል ልብስ እና 1 የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በለበሱ ሰዎች እና ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ተወስደው፣ ላለፉት 6 ወራት ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ ቆይተው በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም. ተለቀዋል።
አቶ ዓለማየሁ ከፈለ ተሰማ የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነሐሴ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 1 በተለምዶ “ፍላሚንጎ” በሚባለው አካባቢ ሲቪል ልብስ ለብሰው መታወቂያ በያዙ 6 የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተወስደው፣ በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
አቶ መቼምጌታ አንዱዓለም፣ ባለትዳርና የ2 ሕፃናት ልጆች አባት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ነሐሴ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት አካባቢ “ብስራተ ገብርኤል” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የታክሲ አገልግሎት ከሚሰጡበት አካባቢ ከነተሽከርካሪያቸው የሲቪል ልብስ በለበሱ የጸጥታ አካላት ተወስደው፣ በተለምዶ “ራሺያ ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖሪያ ለ7 ወራት ከቆዩ በኋላ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ተለቀዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ እና የልጆች አባት የሆኑ ተጎጂ፣ ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ገደማ ከግል የሥራ ቦታቸው ሲቪል እና የደንብ ልብስ ለብሰው ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አባላት ተይዘው፣ ሰሌዳ በሌለው ተሽከርካሪ ጦር ኃይሎች አካባቢ በተለምዶ “ራሺያ ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖሪያ እንደቆዩ አስረድተዋል። ከዚያ ቀን ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በርካታ የአዲስ አበባ ከተማ እና የፌዴራል ፖሊስ ጣቢያዎች ቢያፈላልጓቸውም በምን ምክንያት እንደተያዙ ለማወቅ ሳይቻል፣ ለ2 ወራት ከቆዩ በኋላ ጥቅምት 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው ተጎጂ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚሠሩበት አካባቢ ሲቪል እና የደንብ ልብስ ለብሰው ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አካላት በተለምዶ “ፓትሮል” በሚባል ተሽከርካሪ በግዳጅ ተወስደው ባልታወቀ ቦታ ከቆዩ በኋላ፣ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
ሌላ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ተጎጂ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እና ባለትዳር ሲሆኑ፣ ታኅሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ በተለምዶ “ስታዲየም” በሚባለው አካባቢ ከሚሠሩበት ቦታ ሲቪል በለበሱና ሽጉጥ በታጠቁ፣ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በለበሱና ቀይ ቦኔት ባደረጉ የጸጥታ አካላት ሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው ዳለቻ ቀለም እንደሆኑ በተገለጸና በተለምዶ “ሎንግቤዝ” እና “ፓትሮል” ተብለው በሚጠሩ መኪናዎች ተጭነው ተወስደው፣ ከ6 ወራት እስር በኋላ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ተለቀዋል።
በተመሳሳይ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ተጎጂ ከግል የሥራ ቦታቸው የተወሰኑት ሲቪል እና ሌሎች የደንብ ልብስ በለበሱና በታጠቁ የጸጥታ አካላት መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተያዙ በኋላ፣ ዐይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው ተወስደው ያሉበት ሳይታወቅ እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቆዩ በኋላ፣ በድጋሚ ዐይናቸውን በጨርቅ ተሸፍነው አዲስ አበባ ከተማ፣ “ኃይሌ ጋርመንት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንዲወርዱ መደረጋቸውን አስረድተዋል።