የፖሊዮ ጠብታ የሚወስድ ልጅ

ከ 5 ሰአት በፊት

ምንም አንንኳ በዚህ ዓመት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቢኖሩም የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2025 ፖሊዮን ከምድራችን ላይ እንደሚጠፋ እርግጠኛ ነው።

ፖሊዮን ከዓለም ላይ ለማጥፋት ዘመቻ የተጀመረው እኤአ በ1988 በ125 አገራት ዋይልድ ፖሊዮ ባተባለው ቫይረስ 350 ሺህ ሰዎች በተያዙበት ወቅት ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2023 በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን ብቻ ስድስት በዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ተገኝተው ነበር።

በዚህ ዓመት በፓኪስታን 39 በአፍጋኒስታን ደግሞ 22 ሰዎች መያዛቸው ተመዝግቧል።

እነዚህ አዳዲስ ተጠቂዎች ዓለም ከፖሊዮ ነጻ ለመሆን የምታደርገውን ትግል ያደናቅፉ ይሆን?

ሕጻናት ታማሚዎች

በፓኪስታን ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ኩዌታ ከተማ ነዋሪ የሆነው ጃዋድ የሰባት ወር ከሁለት ሳምንት ሕጻን ነው።

ጃዋድ በቅርቡ በዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ከተጠቁ ሰዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ከፍተኛ ትኩሳት እና የደረት ሕመም ነበረው።

“ልጄ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ አንድ እግሩ እንደማይታዘዘው አስተዋልን። መቆም አይችልም ነበር” ሲል ያስታውሳል የጃዋድ አባት ጃሌል አህመድ።

የሕክምና ባለሙያዎች ጃዋድ በልጅነት ልምሻ መጠቃቱን አረጋግጠዋል። “ለባለቤቴ እና ለእኔ በጣም አስጨናቂ ነው። ወደ ሌሎች ሐኪሞች ዘንድ ወስጄው ነበር፤ ነገር ግን ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ነገሩኝ።”

ፖሊዮ መድኃኒት የሌለው ቢሆንም፣ በክትባት ግን መከላከል ይቻላል።

“ሲወለድ ምንም ዓይነት የክትባት ጠብታ አልሰጠነውም ነበር። ከሦስት ወር በኋላ ግን ወስዷል።”

ጃሌል አህመድ አልፎ አልፎ ልጁን ወደ ሚሠራበት ሱቅ እየወሰደ ለማዝናናት ይሞክራል። ነገር ግን የልጁን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ባሰበ ቁጥር ይቆዝማል።

“ለመራመድ ሲሞክር እግሮቹ ቀጥ አይሉለትም። ተጣመዋል።”

ያልመከነ ተስፋ

ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በፖሊዮ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ግን ስጋት አልገባውም።

በዓለም ጤና ድርጅት የምሥራቅ ሜዲትራንያን ፖሊዮ የማጥፋት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሃሚድ ጃፋሪ “ፖሊዮ ቫይረስ ሥርጭቱ እስኪገታ ድረስ በየጊዜው ሊከሰት ይችላል” ይላል።

በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን ፖሊዮን የማጥፋት ዘመቻው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን በየጊዜው ሁለት ጠብታ ክትባት መስጠትን ያካትታል።

ጃፋሪ “የአካባቢው የክትባት ባለሙያዎች ቡድን በተደጋጋሚ የፖሊዮ እና ሌሎች ክትባቶች የሚያመልጣቸውን አርብቶ አደሮች ይከታተላል፣ ይለያል እንዲሁም ባሉበት ለማግኘት ይጥራል” ይላል።

ክትባት የሚሰጡ ባለሙያዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት ለመጓጓዣ አገልግሎት ምቹ ባልሆኑ ቦታዎች በሞተር ሳይክል ይሄዳሉ።

ጃፋሪ እንደሚለው ምንም እንኳ በፖሊዮ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም “በ2020 ከነበሩት 12 የበሽታው ዝርያዎች ጋር ሲነጻጸር፣ ቫይረሱ ያሉት ዝርያዎች እየቀነሱ ሁለት ዓይነት ብቻ በአንድነት ሰብሰብ ብለው ይገኛሉ።”

የፖሊዮ ክትባት ለታዳጊ ሕጻን ሲሰጥ

ፖሊዮ ምንድን ነው? እንዴትስ ይስፋፋል?

ፖሊዮ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ቫይረስ ነው። በአብዛኛው የሚተላለፈው በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ አማካኝነት ነው።

ቫይረሱ የነርቭ ሥርዓትን በማጥቃት ለአካል ጉዳት ይዳርጋል።

በቫይረሱ ከተጠቃ ሰው ዓይነ ምድር ጋር በሚኖር ንክኪ፣ አልያም በሚያስልበት እና በሚያስነጥስበት ወቅት በሚረጩ ጠብታዎች ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል።

ብዙ ጊዜ ፖሊዮ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ያጠቃል።

“ከ200 አንድ ሰው ነው ለማይቀለበስ የልጅነት ልምሻ የሚጋለጠው። በልጅነት ልምሻ ከተያዙ መካከል ደግሞ ከ5 እስከ 10 በመቶ ያህል የሚሆኑት የመተንፈሻ አካል ችግር ገጥሟቸው ለሞት ይዳረጋሉ” ይላል የዓለም ጤና ድርጅት።

ፖሊዮ ሦስት ዓይነት ዝርያ እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከእነዚህም መካከል ሁለቱ በተከታታይ በተደረጉ የክትባት ዘመቻዎች መጥፋታቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።

ነገር ግን አሁንም ፖሊዮን ከዓለማችን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል እንደቀጠለ ነው።

“አንድ ሕጻን እንኳ በቫይረሱ እስከተያዘ ድረስ፣ በሁሉም አገራት የሚገኙ ሕጻናት ፖሊዮ የመያዝ ዕድል አላቸው” ይላል የጤና ድርጅቱ።

ነገር ግን ፖሊዮ ራሱ በክትባት የሚመራ ነው። ክትባቱ ደካማ የፖሊዮ ቫይረስ ሲሆን፣ በክትባት መልክ ከተወሰደ በኋላ በሆድ ውስጥ ጉዳት ሳያደርስ ተራብቶ በዓይነ ምድር በኩል ይወጣል።

ከዚህ በኋላ ንጽህናው ባልተጠበቀ ውሃ በኩል ወዳልተከተቡ ሰዎች ይተላለፋል።

የአሜሪካ መንግሥት በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (ሲዲኤስ) በአፍሪካ በርካታ የፖሊዮ ወረርሽኞች የተከሰቱት ከክትባት ጋር በተያያዘ ነው ሲል ገልጿል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጥር ወር እስከ ሰኔ 2024 ድረስ በ39 አገራት 672 ሰዎች ላይ የተከሰቱ 74 ከክትባት ጋር በተያያዘ የተከሰቱ የፖሊዮ ወረርሽኞች ነበሩ።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ በጦርነት በፈራረሰችው ጋዛ በክትባት የተሰጠ የፖሊዮ ቫይረስ የ10 ዓመት ወንድ ሕጻን ልጅን በከፊል በልምሻ እንዲጠቃ አድርጓል።

ይህንንም ተከትሎ ወዲያውኑ የክትባት ዘመቻ በአካባቢው ተጀምሯል።

ክትባት

ፖሊዮን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተጀመረው ዘመቻ “ባለፉት አስር ዓመታት ከ10 ቢሊዮን በላይ የፖሊዮ ክትባት ጠብታዎች ሦስት ቢሊዮን ለሚሆኑ የዓለማችን ሕጻናት ተሰጥተዋል” ይላል።

ፓኪስታን በየጊዜው የቤት ለቤት ክትባት ዘመቻ ታካሄዳለች።

ለመጨረሻ ጊዜ ዘመቻውን ያካሄደችው በመስከረም ወር ላይ ነው።

በአፍጋኒስታን ከአምስት ዓመታት በኋላ በ2024 ሰኔ ወር ላይ የቤት ለቤት ክትባት ዘመቻ ተካሄዷል።

ለመስከረም ወር ተይዞ የነበረው የክትባት ፕሮግራም ግን በታሊባን ባለሥልጣናት ምክንያት ተሰርዟል።

የታሊባን ጤና ሚኒስትር ቢቢሲ በቀጣይ ስለሚኖሩ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻዎች ላቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በአፍጋኒስታን የታሊባን ባለስልጣናት የቤት ለቤት የፖሊዮ ክትባት እንዳይሰጥ ከልክለዋል
የምስሉ መግለጫ,በአፍጋኒስታን የታሊባን ባለስልጣናት የቤት ለቤት የፖሊዮ ክትባት እንዳይሰጥ ከልክለዋል

የሚከትቡ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች

ፍርሃት፣ ጥርጣሬ እና የተሳሳተ መረጃ በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን የሚካሄዱ የክትባት ዘመቻዎችን እንዳይሳኩ እንቅፋት መሆን ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎም ለጥቃት ምክንያት ይሆናሉ።

በፓኪስታን የፖሊዮ ክትባት ፕሮግራም በዚህ ዓመት ብቻ በክትባት ዘመቻ ላይ የተሰማሩ 22 ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

በአፍጋኒስታን አስከፊ የተባለው ጥቃት የደረሰው በአውሮፓውያኑ 2004 የካቲት ወር ላይ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ቀን በአራት የተለያዩ ጥቃቶች ስምንት የፖሊዮ ክትባት ለመስጠት የተሰማሩ ሠራተኞች ላይ ግድያ ተፈጽሟል።

እንደ ጉላንዝ ሺራዚ እና አሚር አሊ ያሉ ጠንካራ የክትባት ሠራተኞች መኖራቸው ዘመቻው እንዲቀጥል አድርጎታል።

ሺራዚ በፓኪስታኗ ካሽሚር ከ2011 ጀምሮ በፖሊዮ ዘመቻ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች። አራት የቤተሰብ አባላቷም እንዲሁ በዘመቻው ላይ ተሳታፊዎች የነበሩ ሲሆን፣ ሁለቱ ተገድለዋል።

“የእህቴን ልጅ እና የወንድሜን ሚስት የሆስፒታል አልጋ ላይ ተኝተው አይቻቸዋለሁ። የ18 ዓመቷ መዲሀ የተኛች ነበር የሚመስለው፤ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነበረች። የወንድሜ ሚስት ደግሞ በሌላ የሆስፒታል አልጋ ላይ ነበረች። ብዙ ደም ፈሷቸው፣ እዚያው ነው የሞቱት።”

“በጣም ጭካኔ የተሞላበት ነበር፤ በሐዘን ስብርብር እንድል ነው ያደረገኝ።”

ሺራዚ ፖሊዮ መከላከል ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ለምን ጥቃት እንደሚደርስባቸው አይገባትም። ምንም እንኳ ለጥቃት ዒላማ የተጋለጠች መሆኑን ብታውቅም የክትባት ዘመቻውን ማቋረጥ አታስብም።

አሚር አሊ በፖሊዮ ቫይረስ ተጠቅቶ አንድ እግሩ ሽባ የሆነው የ4 ዓመት ሕጻን እያለ ነው።

ከስዋት ሸለቆ አካባቢ ወደ ካራቺ መጥቶ አሁን በክትባት ባለሙያነት እየሠራ ይገኛል።

“ገና ልጅ እያለሁ ስምንት ያህል ቀዶ ሕክምናዎችን አድርጌያለሁ፤ ነገር ግን አንዱም ለውጥ አላመጣልኝም። ከጉዳቴ ጋር መኖር ነበረብኝ።”

አሚር ለመንቀሳቀስ ስለሚቸገር ከስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ታቅቦ ነው የኖረው። እናቱም ስሜቷ ተጎድቷል።

“አንድ ቀን፣ በፖሊዮ ክትባት ላይ መሥራት ለሚፈልጉ ሰዎች የቀረበ ማስታወቂያ አየሁና ለማመልከት ወሰንኩ። ፍላጎቴ ፖሊዮን ማጥፋት ነው።”

የ36 ዓመቱ አሚር ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ክራች የሚጠቀም ሲሆን፣ የራሱን የሕይወት ገጠመኝም ሰዎች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ለማነሳሳት ይጠቀምበታል።

“ልጆቻቸውን ካላስከተቡ እንደእኔ ሆነው አንደሚቀሩ እነግራቸዋለሁ” የሚለው አሚር በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ለሚካሄደው የክትባት ዘመቻም እየተዘጋጀ መሆኑን ይናገራል።

ከፖሊዮ ነጻ ዓለም

የዓለም ጤና ድርጅት ሰዎች ክትባቱን አሻፈረኝ የሚሉበት ዋና ምክንያትን ለመመለስ እየሰራ ነው።

ስለክትባቱ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ዋነኛ ችግሮች ሆነው ተለይተዋል።

ስለ ፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ትክክለኛ መረጃን ለመስጠት በየአካባቢው ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ለመጠቀም፣ ታዋቂ ሰዎችን አምባሳደር በማድረግ ትክክለኛ መረጃን ለማሰራጨት እየሰራ ነው።

ጃፋሪ “የሁለቱም አገራት መንግሥታት እኤአ በ2025 የፖሊዮ ወረርሽኝን ለማቆም የፖለቲካ ቁርጠኝነት አላቸው፤ በሁለቱም አገራት ለሚገኙ ሕጻናት ውጤታማ ዘመቻዎችን በማድረግ ፖሊዮን ታሪክ ማድረግ እንችላለን” ይላል።

በዚህ ውጤታማ መሆን ከተቻለ ፖሊዮ ከፈንጣጣ ቀጥሎ በሰው ልጅ ጥረት ከዓለማችን ላይ የጠፋ ሁለተኛው በሽታ ይሆናል ማለት ነው።