በእስራኤል ጥቃት የወደመው የሊባኖሱ መኖሪያ ቤት

ከ 4 ሰአት በፊት

እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ባደረሰችው ጥቃት 6 ሴቶች እና 5 ሕፃናትን ጨምሮ 19 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ቴፋህታ በተሰኘችው መንደር ባለሶስት ሕንፃ መኖሪያ ቤት ላይ በደረሰ ጥቃት አሕመድ ኢዘዲን እና ሶስቱ ትውልድ ቤተሰቦቹ መገደላቸውን ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአካባቢው ኢማም ሼክ አብዶ አቦ ራያ እና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ጥቃቱ በደረሰበት ቤት አቅራቢያ እየተጓዙ ሳለ መገደላቸውም ተሰምቷል።

የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን ያለው ነገር የለም። ነገር ግን በተደጋጋሚ በሚሰጠው መግለጫ ሰላማዊ ዜጎችን ዒላማ አናደርግም ሲል ይደመጣል።

እስራኤል ባለፉት አራት ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ የአየር ድብደባዎች ሊባኖስ ላይ ስታደርስ ቆይታለች። ጥቃቱ የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ እና ቡድኑ የሚጠቀምባቸው መሠረተ ልማቶች እና የጦር መሣሪያዎችን ለማውደም ያለመ ነው ትላለች።

የቴህፋታ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት አሕመድ ኢዘዲን እና ቤተሰቦቹ ሰኞ ዕለት በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ዘመዶቻቸውን ቀብረው ከተመለሱ በኋላ ነው የተገደሉት።

የአካባቢው ነዋሪ የሆነችው ሱአድ ሐሞድ፤ ቤተሰብ እና ዘመድ የተገደለባቸው ሰዎች ለቅሶ መድረስ ስለማይችሉ ሐዘናቸውን ቤታቸው ሆነው ነው የሚገልፁት ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

“ቤቱ ውስጥ ነዋሪዎች ብቻ ነበሩ። ከቀብሩ ተመልሰው መጡ። ማንም ቤተሰብ ያልሆነ ሰው አልነበረም። የአካባቢው ሰው አሁን ባለው ሁኔታ ለቅሶ መቀመጥ እንደማይችል ያውቀዋል።”

አሕመድ ኢዘዲን፣ ሚስቱ፣ እሕቱ፣ ሴት ልጆቹ፣ የልጆቹ ሚስቶች፣ የሴት ልጆቹ ባሎች እና የልጅ ልጆቹ ነበሩ ስትል ሱአድ ትናገራለች።

ኢዘዲን በሕንፃው የታችኛው ወለል ላይ ይኖር ነበር። ሌሎች ቤተሰቦቹ ደግሞ ከላይ በሚገኙት ፎቆች ላይ ነበር የሚኖሩት። ነገር ግን ጥቃቱ ሲደርስ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ሰብሰብ ብለው ታችኛው ፎቅ እንደነበሩ ተሰምቷል።

ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች ቤቱ በአየር ጥቃት ከወደመ በኋላ ከፍተኛ መጠን ያለው ጭስ ወደላይ ሲወጣ ያሳያሉ።

ረቡዕ ጥዋት የሊባኖስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባሰራጨው ቪድዮ መኖሪያ ቤቱ ከሞላ ጎደል መውደሙን አሳይቷል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር በእስራኤል አየር ድብደባ ምክንያት ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ አልገለፀም። ነገር ግን የአካባቢው ባለሥልጣናት የሟቾች ቁጥር 19 ነው ይላሉ።

ሱአድ እንደምትለው ሕንፃው ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት የሥፍራው ኢማም የሆኑት ሼክ አቦ ራይ በአካባቢው በመገኘታቸው የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። ሌሎች ሁለት መንገደኞችም መገደላቸው ተሰምቷል።

የሼክ አቦ ራያ ዘመድ የሆነ ግለሰብ ጥቃቱ የደረሰው ከቀብሩ ከ15 ደቂቃ በኋላ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 11፡10 ገደማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ባለፈው ሳምንት አይቱ በተባለች የሰሜናዊ ሊባኖስ መንደር እስራኤል ባደረሰችው ጥቃት 12 ሴቶች እና 2 ሕፃናት መገደላቸውን የሚጠቁም ሪፖርት እንደደረሰው የተባበሩት መንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም አስታውቋል።

ተቋሙ እስራኤል ያደረሰችው ጥቃት ምርመራ እንዲደረግበት አሳስቦ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እየተከበረ አለመሆኑ እንዳሰጋው ገልጿል።

በጋዛ ከተቀሰቀሰው ጦርነት በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል ድንበር አካባቢ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ የነበሩት እስራኤል እና ሄዝቦላህ ወደለየለት ጦርነት ገብተዋል። እስራኤል በተለያዩ የሊባኖስ አካባቢዎች የአየር ጥቃት እና የመሬት ለመሬት ወረራ ጀምራለች።

እስካሁን ከ2500 በላይ ሊባኖሳዊያን መገለዳቸውን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የእስራኤል ባለሥልጣናት ደግሞ በሰሜናዊው የሀገሪቱ ክፍል 59 ሰዎች መገደላቸውን ገልፀዋል።