
ከ 3 ሰአት በፊት
ግዙፉ አውሮፕላን አምራች ተቋም ቦይንግ ሠራተኞች የመቱትን የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ የቀረበላቸውን 35 በመቶ የደመወዝ ጭማሪን ያካተተ ጥቅማጥቅም ውድቅ አድረጉ።
64 በመቶ የሚሆኑት የኩባንያው ሠራተኞች የቀረበውን የደመወዝ ጭማሪ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው ጭማሪ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ካለፈው መስከረም ወር መባቻ ጀምሮ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቦይንግ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማውን ተቀላቅለውታል።
ሠራተኞቹ የቀረበላቸውን ጭማሪ ውድቅ ያደረጉት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬሊ ኦርትበርግ ኩባንያው “መስቀልኛ መንገድ ላይ ነው” በማለት ካስጠነቀቁ በኋላ ነው።
ኩባንያው በግርድፉ ከ4 እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር ሊከስር ይችላል ተብሏል።
የቦይንግ የሠራተኞች ማኅበር ባወጣው መግለጫ “10 ዓመት መስዋትነት ከከፈልን በኋላም ቢሆን ነገሮችን ለማስተካከል ምክንያት አለን፣ ድርድሩን በፍጥነት በመቀጠል እንደምንፈታውም ተስፋ አለን” ብሏል።
“ይህ የሥራ ቦታ ዲሞክራሲ ነው። ኩባንያው በየዓመቱ ሠራተኞችን በአግባቡ ካልያዘ ደግሞ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖራል” በማለት ሠራተኛ ማኅበሩ አክሏል።
- ‘የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል’ – ሶማሊያከ 5 ሰአት በፊት
- ሩሲያን ለመነጠል የምዕራባውያኑ ጫና እየሠራ እንዳልሆነ በብሪክስ እያሳዩ ያሉት ፑቲንከ 5 ሰአት በፊት
- እስራኤል በአንድ ቤተሰብ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 5 ሕፃናትን ጨምሮ19 ሊባኖሳዊያን ተገደሉከ 4 ሰአት በፊት

ያቀረበው የደመወዝ ጭማሪ በሠራተኞቹ ዘንድ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ቦይንግ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ሥራ ያቆሙት ሠራተኞቹ መደበኛ በሆነ ምርጫ የቀረበላቸውን የደመወዝ ጭማሪ ውድቅ ሲያደርጉ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የመጀመሪያው ጭማሪ ባለፈው ወር ቢያንስ 95 በመቶ በሚሆኑ ሠራተኞች ውድቅ ተደርጓል።
ባለፈው ነሐሴ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ኬሊ ኦርትበርግ ከደኅንነት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ስሙ የጎደፈውን ቦይንግ ክብሩን ለመመለስ እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር።
“ለማስተካከል ትንሽ ጊዜ ይወስዳል፤ ሲመለስ ግን እንደገና ግዙፍ ለመሆን አቅሙ አለው” ነበር ያሉት ሥራ አስፈጻሚው።
ቦይንግ አሁን የገጠመው ችግር የተከሰተው ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ነው። በወቅቱ አንድ አውሮፕላኑ ብልሽት ገጥሞት የተዓማኒነቱ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ነበር።
በዚህም ምክንያት የማምረት አቅሙን ለመቀነስ ተገዷል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኩባንያው በብድር ታንቆ መያዙንና ደንበኞችም ደስተኛ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የቦይንግ ኩባንያ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 4 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ከስሯል።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ቦይንግ በማምረቱም ሆነ ፋይናንሱን በመጠገን ረገድ ብዙ ጊዜ ሊወስድበት ይችላል።
ዋና ሥራ አስፈጸማዊ ኦርትበርግ ግን ኩባንያው በጥሩ አቋም ላይ ነው ባይ ናቸው። አሁንም በግምት 5 ሺህ 4 መቶ ትዕዛዞች መቀበላቸውን በመግለጽ ጠንካራ ተቋም እንዳላቸው ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሥራ ማስጀመር ከባድ መሆኑን አምነዋል።
ቢሆንም ግን ሠራተኞች ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ዕቅድ መዘጋጀቱን እና በዕቅዱ መሠረትም እንደሚመለሱ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።
ኩባንያው ከአንድ ወር በፊት በአማካይ 10 በመቶ የሚሆኑትን ሠራተኞቹን እንደሚቀንስ አስታውቋል።
ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ደግሞ በሥራ ማቆም አድማው ምክንያት ከሥራ ውጭ ሆነዋል።
በዚህም ምክንያት በኩባንያው ብቻ ሳይሆን ለኩባንያው ግብዓት በሚያቀርቡ ሌሎች ኩባንያዎች እና ኢንቨስተሮች ላይም ተጽዕኖ አሳርፏል።