
ከ 2 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት የዓለማችን ቁጥር አንድ ሀብታም ለመራጮች በሎተሪ መልክ እየሰጠ ያለው 1 ሚሊዮን ዶላር ሕጋዊነቱ አጠራጣሪ ነው የሚል ደብዳቤ ለኢላን መስክ ላከ።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ኢላን መስክ ባቋቋመው የፖለቲካ ኮሚቴ አማካይነት እየሰጠ ያለው ገንዘብ የምርጫ ሕግን ሊጥስ ይችላል።
ቴስላ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ እና የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ በዘንድሮው ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ በሰፊው እየቀሰቀሰ ይገኛል።
መስክ ባለፍነው ቅዳሜ እና እሑድ ነው ሕገ-መንግሥቱን በተለመከተ የሕዝብ ድምፅ ላይ ፊርማቸውን ለሚያሰፍሩ መራጮች 1 ሚሊዮን ዶላር መሸለም የጀመረው።
ፍትሕ ሚኒስቴሩ አሜሪካ ፓክ ለተሰኘው የኢላን መስክ ድርጅት ደብዳቤውን መቼ እንደፃፈ ግልጽ አይደለም። የፍትሕ ነሥሪያ ቤቱ መርማሪዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ነገር ግን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙኃን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው የመስክ ድርጊት የፌዴራል ምርጫ ሕጉን የሚጥስ ነው ይላል ሲሉ ዘግበዋል።
- ‘የኢትዮጵያ ሠራዊት ስምሪት የአል ሻባብ እንቅስቃሴ እንዲጨምር አድርጓል’ – ሶማሊያከ 5 ሰአት በፊት
- ሩሲያን ለመነጠል የምዕራባውያኑ ጫና እየሠራ እንዳልሆነ በብሪክስ እያሳዩ ያሉት ፑቲንከ 5 ሰአት በፊት
- እስራኤል በአንድ ቤተሰብ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 5 ሕፃናትን ጨምሮ19 ሊባኖሳዊያን ተገደሉከ 4 ሰአት በፊት
ዲሞክራቶች ኢላን መስክ በገንዘብ አማካኝነት ምርጫው ላይ ጫና እያሳደረ ነው የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ፍትሕ ነሥሪያ ቤቱ ማስጠንቀቂያ የፃፈው።
በአሜሪካ ሕግ መሠረት ዜጎች ተመዝግበው ድምፃቸውን እንዲሰጡ ገንዘብ መስጠት ያስቀጣል። ነገር ግን የኢላን ድርጊት ሕግ የሚጥስ ነው የሚለው ግልፅ አይደለም።
“ወሳኝ በሚባሉ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ አንድ ወይም ሁለት ሚሊዮን አሜሪካዊያን የሕገ-መንግሥቱን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ አንቀፅ ደግፈው ፊርማ እንዲፈርሙ እንሻለን” ሲል መስክ ተናግሯል።
የገንዘብ ሽልማቱ እንደሚለው ፊርማቸውን የሚያሳርፉ ዜጎች የተመዘገቡ መራጮች መሆን አለባቸው። ነገር ግን የትኛውንም ፓርቲ መደገፍ ይችላሉ።
መስክ “የሕዝብ ድምፅ ማሰባሰቢያው ላይ ፊርማቸውን ለሚያሰፍሩ መራጮች በየቀኑ በዕጣ 1 ሚሊዮን ዶላር እንሸልማለን። ይህ ዕጣ እስከምርጫው ቀን ይቆያል” ሲል አክሏል።
በርካታ የሕግ ባለሙያዎች የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ኢላን መስክ እያደረገ ያለው ድርጊት ሕጋዊ ላይሆን ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ኢላን ምናልባት ሕጋዊ የሚሆንበት ቀዳዳ አግኝቶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።
አሜሪካ ፓክ የተባለው የኢላን መስክ የፖለቲካ ክንፍ በድረ-ገፁ እንዳመመለከተው የፊርማው ዓላማ የሕገ-መንግሥቱን የመጀመሪያ ሁለት አንቀፆች መደገፍ ነው። ሁለቱ አንቀፆች የመናገር ነፃነት እና የጦር መሣሪያ የመያዝ ነፃነት ናቸው።
የገንዘብ ሽልማቱ በአሜሪካ ቁልፍ በሚባሉት ሰባት ግዛቶች ለሚኖሩ ነዋሪዎች የሚሰጥ ነው። ፔንሲልቬኒያ፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ሚሺጋን፣ ዊስኮንሲን እና ኖርዝ ካሮላይና በአሜሪካ ምርጫ ቁልፍ የሚባሉ ግዛቶች ናቸው።
የአሜሪካ ምርጫ ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም. ይካሄዳል።